ዘፀአት 18 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየትሮ ሙሴን ጐበኘ 1 የምድያም ካህን የሆነው የሙሴ ዐማት የትሮ፥ እግዚአብሔር ከግብጽ ምድር መርቶ ባወጣቸው ጊዜ ለሙሴና ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገላቸውን ነገር ሁሉ ሰማ፤ 2 ስለዚህም በእርሱ ዘንድ ትቶአት ሄዶ የነበረችውን የሙሴን ሚስት ጺጳራን፥ 3 እንዲሁም ከሙሴ የተወለዱትን ሁለቱን ልጆችዋን ይዞለት መጣ፤ ሙሴ “በባዕድ አገር መጻተኛ ነኝ” በማለት የመጀመሪያ ልጁን ጌርሾም ብሎ ጠራው፤ 4 እንዲሁም “የአባቴ አምላክ እግዚአብሔር ረዳኝ፤ በግብጽ ንጉሥም እጅ እንዳልገደል አዳነኝ” በማለት ሁለተኛውን ልጁን ኤሊዔዘር ብሎ ሰይሞት ነበር። 5 የትሮ የሙሴ ዐማት ከሙሴ ሚስትና ከሁለቱ ልጆችዋ ጋር ሆኖ በበረሓ ሙሴ ወደ ሰፈረበት ወደ ተቀደሰው ተራራ መጣ፤ 6 መምጣታቸውንም ለማሳወቅ ለሙሴ መልእክት ልኮ ነበር፤ 7 ስለዚህም ሙሴ ዐማቱን ሊቀበለው ወጣ፤ ራሱን ዝቅ አድርጎ እጅ በመንሣት ሳመው፤ ስለ ግል ጤንነታቸው ተጠያይቀው ወደ ሙሴ ድንኳን ገቡ፤ 8 ሙሴም እስራኤልን ለመታደግ እግዚአብሔር በግብጽ ንጉሥና በሕዝቡም ላይ ያደረገውን ድንቅ ነገር ሁሉ ለዐማቱ ተረከለት። እንዲሁም ሕዝቡ በመንገድ ላይ ሳሉ ምን ያኽል ብርቱ ፈተና እንደ ገጠማቸውና እግዚአብሔርም እንዴት እንዳዳናቸው ነገረው። 9 የትሮም ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ እግዚአብሔር ከግብጻውያን እጅ እስራኤልን ለማዳን ስላደረጋቸው መልካም ነገሮች ደስ ተሰኘ። 10 እንዲህም አለ፥ “ከግብጽ ንጉሥና ከሕዝቡም እጅ ያዳናችሁ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን! ሕዝቡንም ከባርነት ነጻ ያወጣ እግዚአብሔር ይመስገን! 11 ግብጻውያን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ታብየው ያን ያኽል አሳፋሪ ድርጊት በመፈጸማቸው ይህን ሁሉ አስደናቂ ነገር ስላደረገ እነሆ፥ እኔም እግዚአብሔር ከአማልክት ሁሉ የሚበልጥ መሆኑን አሁን ዐወቅሁ።” 12 ከዚህም በኋላ የትሮ የሙሴ ዐማት በሙሉ የሚቃጠል ቊርባንና ሌላም ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት አመጣ፤ አሮንና የእስራኤል አለቆችም ሁሉ የተቀደሰውን ምግብ በአምልኮት ሥርዓት በእግዚአብሔር ፊት ለመመገብ ከሙሴ ዐማት ጋር መጡ። የዳኞች መሾም ( ዘዳ. 1፥9-18 ) 13 በማግስቱም ሙሴ ሕዝቡን በዳኝነት ለማገልገል ተቀመጠ፤ ሕዝቡም በዙሪያው በመቆም አጨናንቀውት ከጠዋት እስከ ማታ ቈየ። 14 የሙሴ ዐማት የትሮም ለሕዝቡ ያደርገው የነበረውን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ እንዲህ ሲል ጠየቀው “ይህ ሁሉ ለሕዝቡ የምታደርገው ነገር ምንድን ነው? ሕዝቡ አንተን ለማነጋገር በመፈለግ ከጠዋት እስከ ማታ በዙሪያህ በመቆም እንደዚህ የሚያጨናንቅህና አንተም ይህን ሁሉ ጉዳይ በዳኝነት ለማየት ብቻህን የምትቀመጠው ለምንድነው?” 15 ሙሴም ለዐማቱ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እኔ ይህን ሁሉ የማደርግበት ምክንያት ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ ወደ እኔ ስለሚመጣ ነው፤ 16 ሁለት ሰዎች ተጣልተውም ወደ እኔ ቢመጡ የትኛው ወገን ትክክል እንደሆን ለማሳወቅ የእግዚአብሔርን ሕግና ሥርዓት እነግራቸዋለሁ።” 17 ከዚህም በኋላ የትሮ እንዲህ አለ፦ “ይህ የምታደርገው ነገር ሁሉ ትክክል አይደለም፤ 18 አንተን ራስህንም ሆነ ሕዝቡን በከንቱ ታደክማለህ፤ ብቻህን ሆነህ ይህን ሁሉ ለመሥራት ይከብድብሃል፤ 19 እነሆ፥ እኔ አንድ ነገር ልምከርህ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አንተ ሕዝቡን ወክለህ በእግዚአብሔር ፊት ጉዳያቸውን አቅርብ፤ 20 አንተ የእግዚአብሔርን ሥርዓትና ሕግ ልታስተምራቸው፥ እንዲሁም እንዴት መኖርና ምን ማድረግ እንደሚገባቸውም ልትገልጥላቸው ይገባል፤ 21 በተጨማሪ ግን ችሎታ ያላቸውን ሰዎች መርጠህ በሕዝቡ ላይ የሺህ አለቆች፥ የመቶ አለቆች፥ የኀምሳ አለቆችና የዐሥር አለቆች አድርገህ ሹም። እነርሱ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፥ እምነት የሚጣልባቸውና በጉቦም የማይደለሉ ሰዎች መሆን አለባቸው። 22 እነርሱ ሁልጊዜ ተገኝተው ከባድ ያልሆኑ ጉዳዮችን በማየት በዳኝነት ሕዝቡን ያገልግሉ፤ ከአቅማቸው በላይ የሆነውን ከባድ ጉዳይ ወደ አንተ ያምጡት፤ እነርሱ በዚህ ዐይነት ሸክምህን ቢካፈሉልህ ሥራው ይቀልልሃል። 23 በዚህ ዐይነት ብትሠራና ይህም የእግዚአብሔር ፈቃድ ቢሆን ራስህን በከንቱ አታደክምም፤ ሕዝቡም በቀላሉ ጉዳዩ እየተፈጸመለት ወደየቤቱ ይሄዳል።” 24 ሙሴም የዐማቱን ምክር ሁሉ ተቀብሎ በሥራ ላይ አዋለው። 25 ከእስራኤላውያንም ሁሉ መካከል ችሎታ ያላቸውን ሰዎች መረጠ፤ እነርሱንም የሺህ አለቆች፥ የመቶ አለቆች፥ የኀምሳ አለቆችና የዐሥር አለቆች አድርጎ በሕዝቡ ላይ ሾማቸው። 26 እነርሱም ከባድ ያልሆኑ ጉዳዮችን በማየት ሕዝቡን ሁልጊዜ በዳኝነት ያገለግሉ ጀመር፤ አስቸጋሪ የሆኑትን ጉዳዮች ብቻ ወደ ሙሴ ሲያቀርቡ፥ ቀላል የሆነውን ጠብና ክርክር ሁሉ ራሳቸው ይወስኑ ነበር። 27 ሙሴም ዐማቱን በሰላም አሰናብቶት፤ ወደ አገሩ ተመለሰ። |