ዘፀአት 17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበተአምር ከአለት የፈለቀ ውሃ ( ዘዳ. 20፥1-13 ) 1 መላው የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወር “ሲን” ተብሎ የሚጠራውን ምድረ በዳ ትተው በረፊዲም ሰፈሩ፤ ነገር ግን በዚያ የሚጠጣ ውሃ አልነበረም። 2 ስለዚህም “የምንጠጣው ውሃ ስጠን” ብለው በሙሴ ላይ አጒረመረሙ። ሙሴም “ስለምን ትወቅሱኛላችሁ? ስለምንስ እግዚአብሔርን ትፈታተናላችሁ?” አላቸው። 3 ሕዝቡ ግን እጅግ ተጠምተው ስለ ነበር “ከግብጽ ምድር ያወጣኸን ለምንድን ነው? እኛንና ልጆቻችንን እንስሶቻችንንም ጭምር በውሃ ጥም ለመፍጀት ነውን?” እያሉ በሙሴ ላይ ማጒረምረማቸውን ቀጠሉ። 4 ሙሴም “ከቶ ይህን ሕዝብ ምን ባደርገው ይሻላል? እነሆ፥ በድንጋይ ሊወግሩኝ ተዘጋጅተዋል” እያለ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 5 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከእስራኤል ሕዝብ አለቆች፥ ጥቂቶቹን ውሰድ፤ ከሕዝቡም ቀድመህ ወደ ፊት ሂድ፤ የዐባይን ወንዝ የመታህበትንም በትር በእጅህ ያዝ፤ 6 እነሆ፥ እኔ በሲና ተራራ በአለት ላይ በፊትህ እቆማለሁ፤ አንተም አለቱን ምታው፤ ሕዝቡም የሚጠጡት ውሃ ከውስጡ ይፈልቃል፤” ሙሴም በእስራኤል አለቆች ፊት እንደዚሁ አደረገ። 7 እስራኤላውያን “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው ወይስ አይደለም?” በማለት በማጒረምረማቸውና እግዚአብሔርን በመፈታተናቸው ያ ስፍራ ማሳህና እና መሪባ ተብሎ ተጠራ። በዐማሌቃውያን ላይ የተደረገ ጦርነት 8 እስራኤላውያን በረፊዲም ሳሉ ዐማሌቃውያን መጥተው አደጋ ጣሉባቸው፤ 9 ሙሴም ኢያሱን “ጥቂት ሰዎች ምረጥና በነገው ዕለት ዐማሌቃውያንን ውጋ፤ እኔም ተአምራት እንድፈጽምባት እግዚአብሔር የሰጠኝን በትር ይዤ በኮረብታው ጫፍ ላይ እቆማለሁ” አለው። 10 ኢያሱም የሙሴን ትእዛዝ በመፈጸም ዐማሌቃውያንን ለመውጋት ወጣ፤ ሙሴ፥ አሮንና ሑር ወደ ኮረብታው ጫፍ ወጡ፤ 11 ሙሴ እጆቹን ወደ ሰማይ በዘረጋ ጊዜ እስራኤላውያን ድል ያደርጉ ነበር፤ እጆቹን ባጠፈ ጊዜ ግን ዐማሌቃውያን እንደገና አንሰራርተው ያሸንፉ ነበር። 12 የሙሴ እጆች ስለ ዛሉ አሮንና ሑር ድንጋይ አምጥተው ሙሴ እንዲቀመጥበት አደረጉ፤ በግራና በቀኝ ክንዶቹን ደግፈው በመቆም ፀሐይ እስከምትጠልቅበት ጊዜ ድረስ ቈዩ። 13 በዚህ ሁኔታ ኢያሱ ዐማሌቃውያንን በሰይፍ ጠራርጎ አጠፋ። 14 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን “ዘወትር ሲታወስ እንዲኖር የዚህን ድል ታሪክ ጻፈው፤ ለኢያሱም ዐማሌቃውያንን ከምድር ጨርሼ የማጠፋቸው መሆኔን ንገረው” አለው። 15 ሙሴም መሠዊያ ሠርቶ “እግዚአብሔር የድል ሰንደቅ ዓላማዬ ነው” ብሎ ሰየመው፤ 16 እንዲህም አለ “የእግዚአብሔርን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጋችሁ ያዙ! እግዚአብሔር ዐማሌቃውያንን ለዘለዓለም ይዋጋቸዋል።” |