ዘፀአት 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየሞት መቅሠፍት አልፎ መሄድ 1 እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን በግብጽ ምድር እንዲህ ሲል ተናገራቸው፤ 2 “ይህ ወር ለእናንተ የዓመቱ መጀመሪያ ወር ይሁንላችሁ፤ 3 ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ይህን ሥርዓት አስተምሩ፤ ይህ ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው በቤተሰቡ ደረጃ አንድ ጠቦት ይምረጥ። 4 ቤተሰቡ አነስተኛ ከመሆኑ የተነሣ እንስሳውን በልቶ ለመጨረስ የማይችል ከሆነ ግን እርሱና የቅርብ ጐረቤቱ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ሊመገበው የሚችለውን ያኽል ተመጥኖ እንስሳውን በአንድነት አብረው ይብሉት። 5 የምትመርጡት እንስሳ በግ ወይም ፍየል መሆን ይችላል፤ ነገር ግን ምንም ነውር የሌለበትና አንድ ዓመት የሞላው ተባዕት ይሁን። 6 እነዚህንም እስከ ዐሥራ አራተኛው ቀን ጠብቁአቸው። በዐሥራ አራተኛው ቀን ምሽት ላይ የእስራኤል ኅብረተሰብ ሁሉ እንስሶቹን ይረዱ። 7 ሕዝቡም ከደሙ ወስደው የእንስሶቹ ሥጋ የሚበላበትንም እያንዳንዱን ቤት ደጃፍ መቃኑንና ጉበኑን ሁሉ ይቀቡት፤ 8 ሥጋውንም በዚያኑ ሌሊት እየጠበሱ ከመራር ቅጠልና ካልቦካ ቂጣ ጋር ይብሉት። 9 ከሥጋውም ጥሬውን ወይም ቅቅሉን አትብሉ፤ ራሱን፥ እግሮቹን የሆድ ዕቃውንም ጭምር በሙሉ ጠብሳችሁ ሥጋውን ብሉት። 10 እስከሚነጋም ድረስ ከሥጋው ምንም ነገር አታስተርፉ፤ የተረፈ ነገር ቢኖር ሁሉንም በእሳት አቃጥሉት። 11 ለጒዞ እንደ ተዘጋጀ ሰው ሆናችሁ ወገባችሁን በመታጠቅ ጫማችሁን አድርጋችሁ፥ በትራችሁን በእጃችሁ ይዛችሁ በችኰላ ብሉት፤ እርሱም እኔን እግዚአብሔርን የምታከብሩበት የፋሲካ በዓል ይሁንላችሁ። 12 “በዚያችም ሌሊት እኔ በግብጽ ምድር ሁሉ እየተላለፍኩ እያንዳንዱን የሰውም ሆነ የእንስሳ ዘር የሆነውን የበኲር ልጅ ሁሉ እገድላለሁ፤ የግብጽንም አማልክት ሁሉ እቀጣለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 13 በደጃፎቻችሁ መቃኖች ላይ የሚታየው ደም እናንተ የምትኖሩባቸውን ቤቶች ለይቶ የሚያሳይ ምልክት ይሆናል፤ እኔም ደሙን በማይበት ጊዜ አልፌአችሁ እሄዳለሁ፤ በዚህም ዐይነት ግብጻውያንን በመቅሠፍት በምመታበት ጊዜ፥ በእናንተ ላይ ምንም ዐይነት መቅሠፍት አይደርስባችሁም። 14 እኔ እግዚአብሔር ያደረግኹላችሁን ሁሉ በማስታወስ ይህ ቀን መንፈሳዊ ክብረ በዓል ይሁንላችሁ፤ እርሱንም በሚመጡት ዘመናት ሁሉ እንድታከብሩት ቋሚ ሥርዓት ይሁንላችሁ።” የቂጣ በዓል 15 እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “ሰባት ቀን ሙሉ እርሾ ያልነካውና ፈጽሞ ያልቦካ ቂጣ ብቻ ትበላላችሁ፤ በመጀመሪያው ቀን እርሾውን ሁሉ ከየቤታችሁ ታስወግዳላችሁ፤ ማንም ሰው በነዚያ ሰባት ቀኖች እርሾ ያለበትን እንጀራ ቢበላ ከእስራኤል ሕዝብ መካከል ይወገዳል። 16 ከዚያም ሰባት ቀኖች በመጀመሪያውና በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ታደርጋላችሁ፤ በነዚያም ቀኖች ምግባችሁን ከማዘጋጀት በቀር ምንም ሥራ አትሠሩም። 17 መላውን የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር መርቼ ያወጣሁት በዚህ ቀን ስለ ሆነ ይህን የቂጣ በዓል ትጠብቃላችሁ፤ በሚመጡትም ዘመናት ሁሉ ይህን በዓል ማክበር ቋሚ ሥርዓት ይሁንላችሁ። 18 ከመጀመሪያው ወር ከዐሥራ አራተኛው ቀን ዋዜማ ምሽት ጀምሮ እስከ ኻያ አንደኛው ቀን ምሽት ድረስ ያልቦካ እንጀራ ትበላላችሁ። 19 እስከ ሰባት ቀን ምንም እርሾ በቤታችሁ መገኘት የለበትም፤ የአገር ተወላጅም ሆነ ወይም መጻተኛ ማንኛውም ሰው የቦካ እንጀራ ቢበላ፥ ከእስራኤል ሕዝብ መካከል ይወገዳል፤ 20 በማንኛውም ስፍራ ብትሆኑ እርሾ የሌለበት ቂጣ ብሉ እንጂ እርሾ ያለበት ምንም ነገር አትብሉ።” የመጀመሪያው ፋሲካ 21 ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች ሁሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ቤተሰባችሁ ሁሉ የፋሲካን በዓል እንዲያከብር ከእናንተ እያንዳንዱ ጠቦት መርጦ ይረድ፤ 22 ጭብጥ የሚሞላ የሂሶጵ ቅጠል ውሰዱ፤ በሳሕን ያለውንም ደም በቅጠሉ እየነከራችሁ የቤታችሁን በር መቃኖችና በላይ በኩል ያለውን ጉበን ቀቡ፤ እስከ ማግስቱ ጠዋት ድረስ ማንም ሰው ከቤቱ አይውጣ። 23 እግዚአብሔር ግብጻውያንን በሞት ለመቅጣት በግብጽ ምድር ያልፋል፤ በጉበንና በመቃኖቹ ላይ ያለውንም ደም በሚያይበት ጊዜ አልፎ ይሄዳል፤ የሞት መልአክም ወደየቤታችሁ ገብቶ እናንተን እንዳይገድል ያደርጋል፤ 24 እናንተና ልጆቻችሁ ይህን ሥርዓት ለዘለዓለም ትጠብቁታላችሁ፤ 25 እግዚአብሔር ሊያወርሳችሁ ተስፋ ወደ ሰጣችሁ ምድር ስትገቡም ይህን ሥርዓት ትፈጽማላችሁ። 26 ልጆቻችሁ ‘ይህ ሥርዓት ምንድን ነው?’ ብለው በሚጠይቁአችሁ ጊዜ፥ 27 እናንተም እንዲህ ብላችሁ ትመልሱላቸዋላችሁ፤ ‘ይህ እግዚአብሔርን ለማክበር የሚደረግ የፋሲካ መሥዋዕት ነው፤ እግዚአብሔር በግብጽ ምድር የእስራኤላውያንን መኖሪያ ቤቶች አልፎ በመሄድ ግብጻውያንን ሲገድል እኛን አድኖናል።’ ” እስራኤላውያንም ይህን በሰሙ ጊዜ ተንበርክከው ሰገዱ፤ 28 ሄደውም በሙሴና በአሮን አማካይነት እግዚአብሔር ያዘዛቸውን ሁሉ አደረጉ። የግብጻውያን የበኲር ልጆች በሞት መቀሠፍ 29 እኩለ ሌሊት ሲሆን እግዚአብሔር ከንጉሡ አልጋ ወራሽ ጀምሮ ከምድር በታች ባለ እስር ቤት ውስጥ እስከ ተጣለው የእስረኛ ልጅ ድረስ በግብጽ ምድር በኲር የሆነውን ወንድ ልጅ ሁሉ በሞት ቀጣ፤ በኲር ሆነው የተወለዱ እንስሶችም ተገደሉ። 30 በዚያኑ ሌሊት ንጉሡና መኳንንቱ፥ መላውም የግብጽ ሕዝብ ሁሉ ከእንቅልፋቸው ነቁ፤ ወንድ ልጅ ያልሞተበት አንድ ቤት እንኳ ስላልነበረ በግብጽ ምድር ሁሉ ታላቅ የለቅሶ ጩኸት አስተጋባ። 31 በዚያኑ ሌሊት ንጉሡ ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተና እስራኤላውያን ወገኖቻችሁ ሁሉ ከዚህ ውጡ! አገሬን ለቃችሁ ሂዱ! በጠየቃችሁትም መሠረት ለእግዚአብሔር ስገዱ! 32 የበግ፥ የፍየልና የቀንድ ከብት መንጋችሁን ሁሉ ይዛችሁ ሂዱ፤ እኔንም ባርኩኝ።” 33 አገሪቱን ለቀውላቸው እንዲወጡ ግብጻውያን ራሳቸውም ሕዝቡን በማጣደፍ “በአስቸኳይ ለቃችሁ ካልወጣችሁልን እነሆ ሁላችንም ማለቃችን ነው” አሉአቸው። 34 ስለዚህም ሕዝቡ ያልቦካውን ሊጥ በቡሆ ዕቃ ሞልተው በልብስ በመጠቅለል በትከሻቸው ተሸከሙ፤ 35 እስራኤላውያን ሙሴ እንዳዘዛቸውም አደረጉ፤ ይኸውም የወርቅና የብር ጌጣጌጥ እንዲሁም ልብስ እንዲሰጡአቸው ግብጻውያንን ጠየቁ። 36 እግዚአብሔርም እስራኤላውያን በግብጻውያን ዘንድ ሞገስ እንዲያገኙና የጠየቁትንም ሁሉ ማግኘት እንዲችሉ አደረገ፤ በዚህም ዐይነት እስራኤላውያን የግብጽን ሀብት በዝብዘው ሄዱ። የእስራኤላውያን ከግብጽ መውጣት 37 እስራኤላውያንም ከራምሴ ተነሥተው ወደ ሱኮት ለመሄድ በእግር ጒዞ ጀመሩ፤ የሰዎቹም ብዛት ሴቶችና ልጆች ሳይቈጠሩ ስድስት መቶ ሺህ ነበር። 38 ከእነርሱ ጋር ቊጥሩ የበዛ ሌላ ድብልቅ ሕዝብ ብዙ የበግ፥ የፍየልና የቀንድ ከብት መንጋ እየነዳ ወጣ። 39 ከግብጽ በድንገት ተጣድፈው ስለ ወጡ ምግባቸውን ለማዘጋጀትም ሆነ በእርሾ የቦካ እንጀራ ለመጋገር ጊዜ ስላልነበራቸው ከግብጽ ይዘው ካወጡትም ሊጥ ቂጣ ጋገሩ። 40 እስራኤላውያን በግብጽ ምድር የኖሩት አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ነበር፤ 41 አራት መቶ ሠላሳው ዓመት በተፈጸመበትም ቀን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ የግብጽን ምድር ለቆ ወጣ። 42 እግዚአብሔር ሕዝቡን እየጠበቀ ከግብጽ ምድር ባወጣቸው ዕለት ጊዜው ሌሊት ነበር፤ ያም ሌሊት እስራኤላውያን በመጠባበቅ ተግተው የሚያድሩበት ለሚመጣው ትውልድ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሌሊት ነው። የፋሲካ በዓል አከባበር ሥርዓት 43 እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “የፋሲካ በዓል አከባበር ሥርዓት ይህ ነው፤ ማንኛውም የባዕድ አገር ሰው የፋሲካን ራት አይብላ፤ 44 ባሪያ እንዲሆናችሁ በገንዘባችሁ የገዛችሁት ሰው ግን አስቀድማችሁ ከገረዛችሁት በኋላ መብላት ይችላል። 45 በዚያን ጊዜ በሀገር ውስጥ የሚኖር እንግዳ ሰው ወይም አዲስ ቅጥር ሠራተኛ አይብላ። 46 ምግቡ በሙሉ በዚያው በተዘጋጀበት ቤት ውስጥ መበላት ስላለበት ወደ ውጪ አይውጣ፤ ከጠቦቱም አጥንቶቹን አትስበሩ። 47 መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ይህን በዓል ያክብረው። 48 ነገር ግን ያልተገረዘ ማንም ሰው አይብላ፤ የውጪ አገር ሰው በመካከላችሁ ቢኖርና የእግዚአብሔርን የፋሲካ በዓል ማክበር ቢፈልግ፥ አስቀድማችሁ በቤተሰቡ ያሉትን ወንዶች ሁሉ ግረዙ፤ ከዚያም በኋላ የሀገር ተወላጅ እስራኤላዊ እንደ ሆነ ተቈጥሮ የፋሲካን በዓል ለማክበር ከእናንተ ጋር ይተባበር። 49 እንግዲህ ይህ ሕግ ለእናንተ ለእስራኤላውያኑም ሆነ በመካከላችሁ ለሚኖሩት መጻተኞች በተመሳሳይ ሁኔታ ይፈጸም።” 50 እስራኤላውያን ሁሉ ታዛዦች በመሆን እግዚአብሔር በሙሴና በአሮን አማካይነት ያዘዘውን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁዎች ሆኑ፤ 51 በዚያን ቀን እግዚአብሔር መላውን የእስራኤል ሕዝብ በክፍል በክፍል ከግብጽ ምድር መርቶ አወጣ። |