Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


በ. ሙሴ የግብጻውያን የበኲር ልጆች እንደሚሞቱ አስታወቀ

1 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በግብጽ ንጉሥና በሕዝቡም ሁሉ ላይ ሌላ መቅሠፍት እልካለሁ፤ ከዚያም በኋላ ከዚህች ምድር እንድትወጡ ይለቃችኋል፤ እንዲያውም አንድ ሳይቀር ሁላችሁንም ያባርራችኋል።

2 አሁንም የእስራኤል ሕዝብ ወንዶቹም ሴቶቹም ጐረቤቶቻቸውን ሁሉ የወርቅና የብር ጌጣጌጥ እንዲሰጡአቸው ይጠይቁ ዘንድ ንገራቸው።”

3 እግዚአብሔርም እስራኤላውያን በግብጻውያን ዘንድ ሞገስ እንዲያገኙ አደረገ፤ በእርግጥም የንጉሡ ባለሟሎችና ሕዝቡ ሁሉ ሙሴን በግብጽ ምድር ታላቅ ሰው አድርገው ተመለከቱት።

4 ሙሴም ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘በእኩለ ሌሊት በግብጽ ምድር እዘዋወራለሁ፤

5 የዙፋኑ ወራሽ ከሆነው ከንጉሡ ልጅ ጀምሮ እህል በመፍጨት ከምታገለግል ድኻ ሴት እስከ ተወለደው ልጅ ድረስ በግብጽ ምድር በኲር የሆነ ወንድ ልጅ ሁሉ ይሞታል፤ እንዲሁም የእንስሶች በኲር ሁሉ ይሞታል።

6 በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ከዚህ በፊት ያልነበረ ወደ ፊትም የማይኖር ታላቅ ለቅሶ ይሆናል።

7 ነገር ግን በእስራኤላውያንም ሆነ በእንስሶቻቸው ላይ ውሻ እንኳ አይጮኽባቸውም፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር በግብጻውያንና በእስራኤላውያን መካከል ልዩነት የማደርግ መሆኔን ታውቃላችሁ።’ ”

8 ሙሴም “መኳንንትህ ሁሉ ወደ እኔ መጥተው እጅ ይነሡኛል፤ ሕዝቤንም ይዤ እንድወጣ ይለምኑኛል፤ ከዚያም በኋላ እሄዳለሁ” በማለት ንግግሩን አበቃ፤ ይህንንም ከተናገረ በኋላ በታላቅ ቊጣ ከንጉሡ ፊት ወጥቶ ሄደ።

9 እግዚአብሔር ሙሴን “በግብጽ ምድር ላይ ብዙ ተአምራት አደርግ ዘንድ ንጉሡ እናንተን አይሰማም” ብሎት ነበር፤

10 ሙሴና አሮንም እነዚህን ተአምራት በንጉሡ ፊት አደረጉ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የንጉሡን ልብ ስላደነደነ እስራኤላውያን ከምድሪቱ እንዲወጡ አልፈቀደላቸውም።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告