ዘፀአት 10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሸ. የአንበጣ መንጋ 1 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እነሆ እንደገና ወደ ፈርዖን ተመልሰህ ግባ፤ እኔ የእርሱንና የመኳንንቱን ልብ ያደነደንኩት በመካከላቸው እነዚህን ተአምራት ለማድረግ ዐቅጄ ነው፤ 2 እንዲሁም እነዚህን ተአምራት ባደረግሁ ጊዜ ግብጻውያንን እንዴት እንደቀጣሁ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ መንገር ትችሉ ዘንድ ነው፤ በዚህም ዐይነት ሁላችሁም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።” 3 ስለዚህ ሙሴና አሮን ወደ ንጉሡ ሄደው እንዲህ አሉት፤ “የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ለእኔ መታዘዝን እምቢ የምትለው እስከ መቼ ነው? አሁንም ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ፤ 4 በእምቢተኛነትህ ብትጸና ግን እነሆ፥ በነገው ቀን የአንበጣ መንጋ በአገርህ ላይ እንዲመጣ አደርጋለሁ። 5 የአንበጣውም መንጋ እጅግ ብዙ ከመሆኑ የተነሣ ምድሪቱን በመላ ይሸፍናል፤ ከበረዶው የተረፈውን ነገር፥ ዛፉን ሁሉ ምንም ሳይቀር ይበላዋል። 6 ቤተ መንግሥትህን፥ የመኳንንትህንና የሕዝብህን ቤቶች ሁሉ የአንበጣ መንጋ ይሞላዋል፤ ይህም ሁኔታ ከቀድሞ አባቶችህ ዘመን እስከ አሁን ከታየው መከራ ሁሉ የከፋ ይሆናል።’ ” ሙሴም ከፈርዖን ፊት ወጥቶ ሄደ። 7 መኳንንቱም ንጉሡን እንዲህ አሉት፤ “ይህ ሰው ለእኛ ወጥመድ ሆኖ የሚያስቸግረን እስከ መቼ ነው? አምላካቸውን እግዚአብሔርን ያገለግሉ ዘንድ ከእስራኤላውያን ወገን ወንዶቹ ይሂዱ፤ አገሪቱ በመጥፋት ላይ መሆንዋ አይታወቅህምን?” 8 ስለዚህ ሙሴና አሮን ተጠርተው ወደ ንጉሡ ቀረቡ፤ ንጉሡም “ሄዳችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁን ማገልገል ትችላላችሁ፤ ነገር ግን መሄድ የሚገባቸው የትኞቹ ናቸው?” አላቸው። 9 ሙሴም “ሕፃን ልጆቻችንና ሽማግሌዎቻችን ሳይቀሩ ሁላችንም እንሄዳለን፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንን፥ በጎቻችንንና ፍየሎቻችንን፥ የቀንድ ከብቶቻችንንም ሁሉ እንወስዳለን፤ በምንሄድበት ስፍራ ለእግዚአብሔር በዓል እናደርጋለን” ሲል መለሰ። 10 ንጉሡም እንዲህ አለ፦ “እስቲ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፤ የዐመፅ ሤራ ማቀዳችሁ ግልጥ ስለ ሆነ ሴቶቻችሁንና ልጆቻችሁን ይዛችሁ እንድትሄዱ አልፈቅድላችሁም! 11 እንግዲህ እግዚአብሔርን ማገልገል ከፈለጋችሁ ወንዶቹ ብቻ መሄድ ትችላላችሁ”። ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን ተባረው ወጡ። 12 እግዚአብሔርም ሙሴን “አንበጦችን ለማምጣት እጅህን በግብጽ ምድር ላይ ዘርጋ፤ እነርሱም መጥተው ቡቃያውን ሁሉና ከበረዶ የተረፈውን ተክል ሁሉ ይበላሉ” አለው። 13 ስለዚህ ሙሴ በግብጽ ምድር ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም በዚያን ቀንና ሌሊት የምሥራቅ ነፋስ አስነሣ፤ በነጋም ጊዜ ያ የምሥራቅ ነፋስ አንበጦችን አመጣ። 14 እነርሱም በመርመስመስ መጥተው አገሪቱን ወረሩ፤ ይህን ያኽል ብዛት ያለው የአንበጣ መንጋ ከዚያ በፊት ታይቶ አይታወቅም፤ ወደ ፊትም ሊታይ አይችልም። 15 አገሪቱ ጠቊራ ጨለማ እስክትመስል ድረስ የአንበጣ መንጋ ሸፈናት፤ አንድም ነገር ሳያስቀር ከበረዶ የተረፈውን በየዛፉ ላይ የሚገኘውን ፍሬና ሌላውንም ተክል ሁሉ ግጦ በላው፤ በግብጽ ምድር ከሚገኘው ከማንኛውም ዛፍና ተክል ለምለም የሆነውን ቅጠል ሁሉ መድምዶ በላ። 16 ንጉሡም ሙሴንና አሮንን በፍጥነት አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “አምላካችሁን እግዚአብሔርንና እናንተን በድያለሁ፤ 17 እንግዲህስ እነሆ፥ አንድ ጊዜ ብቻ በደሌን ይቅር እንድትሉኝ እለምናችኋለሁ፤ ይህን ከባድ ቅጣት ከእኔ እንዲያስወግድም አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለምኑልኝ።” 18 ሙሴም ከንጉሡ ፊት ወጥቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። 19 እግዚአብሔርም የምሥራቁን ነፋስ የሚቋቋምና አንበጦቹንም ጠራርጎ ወደ ቀይ ባሕር የሚነዳ ብርቱ ነፋስ ከምዕራብ በኩል አስነሣ፤ በዚህ ዐይነት በመላው የግብጽ ምድር አንድ አንበጣ እንኳ አልቀረም። 20 ነገር ግን እግዚአብሔር የንጉሡን ልብ ስላደነደነ አሁንም እስራኤላውያንን አለቀቀም። ቀ. ጨለማ 21 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን “እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋው፤ በእጅ እስከሚዳሰስ ድረስ ጥቅጥቅ ያለ ጨለማ የግብጽን ምድር ይሸፍናል” አለው። 22 ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ በመላውም የግብጽ ምድር ለሦስት ቀን ጨለማ ሆነ። 23 ግብጻውያን እርስ በርሳቸው ስለማይተያዩ ማንም ሰው እስከ ሦስት ቀን ከቤቱ መውጣት አልቻለም ነበር፤ እስራኤላውያን በሚኖሩበት ስፍራ ግን ብርሃን ነበር። 24 ንጉሡም ሙሴን ጠርቶ “ሄዳችሁ እግዚአብሔርን አገልግሉ፤ ሴቶቻችሁና ልጆቻችሁም ከእናንተ ጋር መሄድ ይችላሉ፤ ነገር ግን በጎቻችሁና ፍየሎቻችሁ የቀንድ ከብቶቻችሁም እዚህ መቅረት ይኖርባቸዋል።” 25 ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እንዲህ ከሆነማ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላም መሥዋዕት የምናቀርባቸው እንስሶች አንተ ትሰጠናለህ ማለት ነዋ? 26 ከቶ ይህ ሊሆን አይችልም፤ እንስሶቻችንን ሁሉ እንወስዳለን፤ አንዲት ሰኮና እንኳ ወደ ኋላ አትቀርም፤ አምላካችንን እግዚአብሔርን የምናገለግልባቸውን እንስሶች መርጠን ማቅረብ ያለብን እኛው ራሳችን ነን፤ እዚያም ከመድረሳችን በፊት ለእርሱ የምንሠዋቸው እንስሶች ምን ዐይነት እንደ ሆኑ ማወቅ አንችልም።” 27 እግዚአብሔርም የንጉሡን ልብ ስላደነደነ ሕዝቡን መልቀቅ አልፈለገም፤ 28 ስለዚህ ሙሴን “ዳግመኛ እንዳላይህ ከፊቴ ወዲያ ሂድ! እኔን በምታይበት ጊዜ እንደምትሞት ዕወቅ!” አለው። 29 ሙሴም “እውነት ነው፤ አንተ እንዳልከው ዳግመኛ አላይህም” አለው። |