አስቴር 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምአስቴር ንጉሡንና ሃማንን ግብዣ እንደ ጠራች 1 ጾም በጀመረች በሦስተኛውም ቀን አስቴር ልብሰ መንግሥትዋን ለብሳ በዙፋኑ ክፍል ፊት ለፊት ወደሚገኘው ወደ ውስጠኛው የቤተ መንግሥት አደባባይ ገብታ ቆመች፤ ንጉሡም በዚያው ክፍል ውስጥ ከመግቢያው በር ፊት ለፊት በተዘረጋ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ነበር። 2 ንጉሡ፥ ንግሥት አስቴር በስተ ውጪ በኩል መቆምዋን በተመለከተ ጊዜ በፊቱ ሞገስን አግኝታ ስለ ነበር የወርቅ በትሩን ዘረጋላት፤ እርስዋም ቀረብ ብላ የወርቁን በትር ጫፍ ነካች። 3 ንጉሡም “አስቴር ሆይ፥ ስለምን መጣሽ? ምን እንደምትፈልጊ ንገሪኝ፤ የንጉሠ ነገሥት መንግሥቴን እኩሌታ እንኳ ቢሆን እሰጥሻለሁ” አላት። 4 አስቴርም “ንጉሥ ሆይ! መልካም ፈቃድህ ቢሆን ለዛሬ ማታ ባዘጋጀሁት ግብዣ ላይ አንተና ሃማን ብትገኙልኝ እወዳለሁ” አለችው። 5 ከዚህም በኋላ ንጉሡ ሃማንን በፍጥነት አስጠርቶ በአስቴር ግብዣ ላይ መገኘት እንዳለባቸው ነገረው፤ ስለዚህም ንጉሡና ሃማን ወደ አስቴር ግብዣ አመሩ። 6 የወይን ጠጅ በመጠጣት ላይ ሳሉም ንጉሡ አስቴርን “ማናቸውንም የምትፈልጊውን ነገር ጠይቂኝ፤ ይፈጸምልሻል፤ የመንግሥቴን እኩሌታ እንኳ ብትጠይቂ ልሰጥሽ ዝግጁ ነኝ!” አላት። 7-8 አስቴርም እንዲህ ስትል መለሰችለት፦ “በግርማዊነትዎ ፊት ሞገስ አግኝቼ ግርማዊነትዎ የጠየቅሁትን ነገር ሊፈጽምልኝ ፈቃደኛ ከሆነ ነገ በማዘጋጀው ግብዣ ላይ እርስዎና ሃማን በድጋሚ እንድትገኙልኝ በአክብሮት እለምናለሁ፤ በዚያም ሰዓት የምፈልገውን ነገር እገልጥልዎታለሁ።” ሃማን መርዶክዮስን ለመግደል መወሰኑ 9 ሃማን ከግብዣው ወጥቶ ሲሄድ እጅግ ተደስቶ በልቡም ሐሴት ያደርግ ነበር፤ ነገር ግን ወደ ቤተ መንግሥቱ በሚያስገባው በር አጠገብ መርዶክዮስን ተቀምጦ አየው፤ አልፎም ሲሄድ መርዶክዮስ ከተቀመጠበት ስፍራ እንዳልተነሣለትና ምንም ዐይነት አክብሮት እንዳላሳየው በተመለከተ ጊዜ ሃማን መርዶክዮስን እጅግ ተቈጣው፤ 10 ሆኖም እንደምንም ራሱን ተቈጣጥሮ በመታገሥ ወደ ቤቱ ደረሰ፤ ከዚህ በኋላ ወዳጆቹን ወደ ቤቱ ጠርቶ ሚስቱ ዜሬሽም አብራ እንድትገኝ አደረገ። 11 ምን ያኽል ሀብታም እንደ ሆነና ምን ያኽል ልጆች እንዳሉት፥ ንጉሡም ሥልጣኑን ከፍ በማድረግና በመሾም የቱን ያኽል እንዳከበረው፥ ከሌሎቹ የመንግሥት ባለሥልጣኖች ይበልጥ የተከበረ ሰው መሆኑንም በትምክሕት ገለጠላቸው፤ 12 ሃማን ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “ከዚህም ሁሉ በላይ ንግሥት አስቴር ባዘጋጀችው ግብዣ ላይ ከንጉሡና ከእኔ በቀር ማንንም አልጠራችም፤ ለነገ በምታዘጋጀው ግብዣም ላይ እንደገና ተጠርተናል፤ 13 ነገር ግን ያን አይሁዳዊ መርዶክዮስን በቤተ መንግሥቱ መግቢያ በር አጠገብ ተቀምጦ በማየቴ ይህ ሁሉ ክብር ለእኔ ምንም ትርጒም ሊሰጠኝ አልቻለም።” 14 ስለዚህ ሚስቱና ወዳጆቹ ሁሉ “ርዝመቱ ኻያ ሁለት ሜትር የሆነ መስቀያ እንጨት አዘጋጅተህ ነገ ጠዋት መርዶክዮስን ለመስቀል የንጉሡን ፈቃድ መጠየቅ ትችላለህ፤ ከዚያም በኋላ ደስ ብሎህ ወደ ግብዣው ትሄዳለህ” ሲሉ ሐሳብ አቀረቡለት። ሃማንም ሐሳቡ መልካም እንደ ሆነ ተቀብሎ የመስቀያውን እንጨት አዘጋጀ። |