Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

አስቴር 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ሃማን አይሁድን ለማጥፋት ሤራ መጠንሰሱ

1 ከዚህም በኋላ ንጉሥ አርጤክስስ የሃመዳታ ልጅ የሆነውን አጋጋዊውን ሐማንን ከሌሎቹ መኳንንት ሁሉ በላይ ክብሩን በማስበለጥ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሾመው።

2 ንጉሡም በግዛቱ ሥር ያሉ ባለሥልጣኖች ሁሉ በጒልበታቸው ተንበርክከው እየሰገዱ እጅ በመንሣት ያከብሩት ዘንድ አዘዘ፤ እነርሱም ሁሉ እንደ ታዘዙት አደረጉ፤ ይህን ለማድረግ እምቢ ያለ መርዶክዮስ ብቻ ነበር።

3 በቤተ መንግሥት ሥራ ላይ የተመደቡ ሌሎች ባለሥልጣኖች መርዶክዮስን “የንጉሡን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋለህ?” እያሉ፥

4 ከቀን ወደ ቀን ሐሳቡን ለማስቀየር ይጥሩ ነበር፤ እርሱ ግን ሊሰማቸው አልወደደም፤ እንዲያውም እኔ አይሁዳዊ ስለ ሆንኩ ለሃማን መስገድ አይገባኝም በማለት ቊርጥ ውሳኔውን ገለጠላቸው ከዚህ በኋላ የመርዶክዮስን ትዕቢት እንዴት መታገሥ ይቻላል? እያሉ በመገረም ጉዳዩን ለሃማን ነገሩት።

5 ሃማንም መርዶክዮስ ተንበርክኮ የማይሰግድለት መሆኑን ባየ ጊዜ እጅግ ተቈጣ።

6 በተለይም መርዶክዮስ አይሁዳዊ መሆኑን በተረዳ ጊዜ መርዶክዮስን ብቻ መግደል በቂ እንዳልሆነ ተገነዘበ፤ ስለዚህም በመላው የፋርስ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ግዛት ውስጥ ያሉትን የመርዶክዮስ ወገን የሆኑትን አይሁድን ሁሉ ለማጥፋት ዕቅድ አወጣ።

7 አርጤክስስ በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፥ ኒሳን ተብሎ በሚጠራው የመጀመሪያው ወር ፑሪም ተብሎ የተሠየመው ዕጣ መጣል እንዲጀመርና አይሁድን ለማጥፋት የተጠነሰሰውን ሤራ በሥራ ላይ ለማዋል አመቺ የሚሆነው ወርና ቀን የትኛው እንደ ሆነ ተለይቶ እንዲታወቅ ትእዛዝ ሰጠ፤ በዕጣውም መሠረት አዳር ተብሎ የሚጠራው ዐሥራ ሁለተኛው ወር በገባ በዐሥራ ሦስተኛው ቀን እንዲሆን ተወሰነ።

8 ስለዚህም ሃማን ለንጉሥ አርጤክስስ እንዲህ ሲል አስረዳው፦ “በንጉሠ ነገሥት መንግሥትህ ግዛት ውስጥ በየአገሩ ተበታትኖ የሚኖር አንድ ሕዝብ አለ፤ ይህም ሕዝብ ከሌሎች አሕዛብ የተለየ ሕግ አለው፤ ከዚህም በላይ ለንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ሕግ ታዛዥ ሆኖ አልተገኘም፤ ታዲያ፥ ይህን ዐይነቱን ሕዝብ ዝም ብለህ ብትታገሥ ለአንተ አደገኛ ነገር ይሆንብሃል፤

9 ንጉሥ ሆይ! ይህ ሕዝብ በሞት የሚቀጣበትን ዐዋጅ ለማስተላለፍ መልካም ፈቃድህ ይሁን፤ ይህን ብታደርግ እኔ ለንጉሠ ነገሥት መንግሥትህ አስተዳደር መርጃ ይሆን ዘንድ ሦስት መቶ አርባ ሺህ ኪሎ የሚመዝን ብር ወደ መንግሥት ግምጃ ቤት ገቢ እንደማደርግ ቃል እገባለሁ።”

10 ንጉሡም ዐዋጆችን ሁሉ ይፋ የሚያደርግበትን የቀለበት ማኅተም ወስዶ ለአጋጋዊው ለሃመዳታ ልጅ የአይሁድ ጠላት ለሆነው ለሃማን ሰጠው።

11 ንጉሡም “እነሆ ሕዝቡ ከነንብረታቸው የአንተ ስለ ሆኑ በእነርሱ ላይ የወደድከውን አድርግ” ሲል ፈቀደለት።

12 ስለዚህ የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ ሦስተኛው ቀን ሃማን የንጉሡን ጸሐፊዎች ጠርቶ ዐዋጁ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተተርጒሞ፥ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በሚገኘው የአጻጻፍ ሥርዓት ሁሉ በመዘጋጀት፥ ወደ አገረ ገዢዎችና ወደ ባለሥልጣኖች ሁሉ እንዲላክ ያደርጉ ዘንድ አዘዘ፤ ዐዋጁም በንጉሥ አርጤክስስ ስም ተጽፎ የቀለበቱ ማኅተም ተደርጎበት ተላለፈ።

13 ፈጣኖች የሆኑ ሯጮችም ይህን ዐዋጅ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ወደሚገኙት አገሮች ሁሉ እንዲያደርሱ ተላኩ፤ በዐዋጁም ውስጥ አዳር ተብሎ በሚጠራው በዐሥራ ሁለተኛው ወር፥ በዐሥራ ሦስተኛው ቀን መላውን የአይሁድ ወጣት፥ ሽማግሌ፥ ሴት፥ ወንድ ሳይቀር ሕፃናትንም ጭምር እንዲገድሉ፥ እንዲያጠፉና እንዲደመሰሱ የሚያዝ ቃል ነበረበት፤ ንብረታቸውም ሁሉ እንዲዘረፍ ትእዛዝ ወጥቶ ነበር።

14 ያ የተቀጠረው ቀን ሲደርስ ሰው ሁሉ ይዘጋጅ ዘንድ ደብዳቤዎቹ ሰው ሁሉ ሊያይ በሚችልበት ቦታ በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ሁሉ እንዲለጠፉ ንጉሡ አዘዘ።

15 በንጉሡም ትእዛዝ ዐዋጁ ሱሳ ተብላ በምትጠራው መናገሻ ከተማ በይፋ ተገልጦ እንዲታይ ተደረገ፤ ፈጣኖች የሆኑ ሯጮችም ወደየአገሩ መልእክቱን አደረሱ፤ መናገሻ ከተማይቱ ሱሳ ታውካ ሳለች፥ ንጉሡና ሃማን በአንድነት ተቀምጠው የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告