አስቴር 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምአስቴር ንግሥት እንደ ሆነች 1 ዘግየት ብሎም የንጉሡ ቊጣ ከበረደ በኋላ እንኳ፥ ንግሥት አስጢን ስላደረገችው ነገርና በእርስዋም ላይ ስለ ተላለፈው ዐዋጅ ማሰላሰሉን ቀጠለ። 2 ስለዚህም የንጉሡ የቅርብ አማካሪዎች ከዚህ የሚከተለውን ሐሳብ አቀረቡለት፤ “ውብ የሆኑ ወጣት ልጃገረዶች ለአንተ ይፈለጉልህ፤ 3 በንጉሠ ነገሥትህ ግዛት በየአገሩ ባለ ሥልጣኖችን በመሾም ውብ የሆኑትን ልጃገረዶች እየመረጡ መናገሻ ከተማ በሆነችው በሱሳ ውስጥ ለአንተ የተመረጡ ሴቶች መኖሪያ ወደ ሆነው ቤት እንዲያመጡአቸው ይደረግ፤ የዚህም ቤት ኀላፊ ባደረግኸው በጃንደረባው ሄጋይ ቊጥጥር ሥር ይጠበቁ፤ የቊንጅናም እንክብካቤ ይደረግላቸው። 4 ከእነርሱም መካከል በይበልጥ የምትወዳትን መርጠህ በአስጢን እግር ተተክታ ንግሥት እንድትሆን አድርግ።” ንጉሡም ይህ ምክር መልካም መሆኑን ተመልክቶ በሥራ ላይ አዋለው። 5 እዚያም በሱሳ ከተማ የሚኖር መርዶክዮስ ተብሎ የሚጠራ አንድ አይሁዳዊ ነበር፤ እርሱ የያኢር ልጅ ሲሆን ከብንያም ነገድ የቂስና የሺምዒ ዘር ነበር። 6 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ ኢኮንያንን ከሌሎች ብዙ ሰዎች ጋር ከኢየሩሳሌም ማርኮ በወሰደው ጊዜ ከእነርሱ አንዱ መርዶክዮስ ተብሎ የሚጠራ ሰው ነበር። 7 እርሱም በዕብራይስጥ ሀዳሳ የተባለችውን የአጐቱን ልጅ አስቴርን ያሳድግ ነበር፤ እርስዋም ቁመናዋ የተስተካከለ እጅግ ውብ ልጃገረድ ነበረች፤ ወላጆችዋም ከሞቱበት ጊዜ ጀምሮ መርዶክዮስ ወደ ቤቱ በመውሰድ ልክ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ በመንከባከብ አሳደጋት። 8 ንጉሡ ዐዋጁን ባስተላለፈ ጊዜ ወደ ሱሳ ከተማ ከመጡት ብዙ ልጃገረዶች መካከል አንድዋ አስቴር ነበረች፤ እርስዋም ወደ ቤተ መንግሥት ተወስዳ የምርጥ ሴቶች መኖሪያ ቤት ኀላፊ በሆነው በሄጋይ ቊጥጥር ሥር እንድትሆን ተደረገ። 9 አስቴርም ሄጋይን ደስ አሰኘችው፤ በፊቱም ሞገስ አገኘች፤ ጊዜም ሳያባክን ወዲያውኑ ጥሩ ምግብ እንዲሰጣትና የሰውነትዋ ቅርጽ በመታሸት እንዲስተካከል በማድረግ በቊንጅና እንክብካቤ እንድትጠበቅ ወሰነ፤ ከምርጥ ሴቶችም መኖሪያ ቤት ከሁሉ የተሻለውን ክፍል መርጦ በመስጠት ከቤተ መንግሥት የተመረጡ ሰባት ደንገጡሮች ያገለግሉአት ዘንድ መደበላት። 10 መርዶክዮስ አስቀድሞ ባሳሰባት መሠረት አስቴር አይሁዳዊት መሆንዋን በምሥጢር ትጠብቀው ነበር፤ 11 መርዶክዮስም አስቴር በምን ሁኔታ እንዳለችና ወደ ፊት የሚገጥማት ዕድል ምን እንደሆን ለማወቅ በየቀኑ በምርጥ ሴቶች መኖሪያ ቤት አደባባይ ፊት ለፊት ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ነበር። 12 ሴቶቹ የቊንጅና እንክብካቤ እየተደረገላቸው የሚቆዩት እስከ አንድ ዓመት ነበር፤ ይኸውም የሰውነታቸው ቅርጽ እንዲስተካከል ለመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት በከርቤና በዘይት፥ እንደገናም ለቀሪዎቹ ስድስት ወራት ባልሳም በተባለ ጣፋጭ ሽቶ ይታሻሉ፤ ከዚያም በኋላ እያንዳንድዋ ልጃገረድ በየተራ ወደ ንጉሥ አርጤክስስ ዘንድ እንድትገባ ይደረጋል። 13 ምርጥ ሴቶች ከሚኖሩበት ቤት ወጥታ ወደ ቤተ መንግሥት በምትገባበትም ጊዜ ልትለብስ የምትፈልገው ልብስ ይሰጣት ነበር። 14 እርስዋም ሌሊቱን ከንጉሡ ጋር ዐድራ በማግስቱ ወደ ሌላ የምርጥ ሴቶች መኖሪያ ቤት ትወሰዳለች፤ እዚያም የንጉሡ ቊባቶች ኀላፊ በሆነው በጃንደረባው በሻዕሸጋዝ ቊጥጥር ሥር ትሆናለች፤ በንጉሡ ዘንድ ተወዳጅነትን አግኝታ እርሱ ስምዋን ጠርቶ እንደገና እንድትመጣለት ካልጠየቀ በቀር ዳግመኛ ወደ እርሱ አትቀርብም። 15 በዚህ ዐይነት አስቴር ወደ ንጉሡ ፊት የምትቀርብበት ጊዜ ደረሰ፤ ይህችም አስቴር የአቢኀይል ልጅ፥ እንደ ልጁ አድርጎ ያሳደጋት የመርዶክዮስ የአጐት ልጅ የነበረችውና ባያት ሁሉ ዘንድ ሞገስን ያገኘች ነበረች፤ እርስዋም ወደ ንጉሡ ፊት የመቅረብ ተራዋ በደረሰ ጊዜ የለበሰችው፥ የምርጥ ሴቶች መኖሪያ ቤት ኀላፊ የነበረው ጃንደረባው ሄጋይ እንድትለብስ የመከራትን እንጂ እርስዋ የጠየቀችውን ልብስ አልነበረም። 16 ስለዚህም አርጤክስስ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ቴቤት ተብሎ በሚጠራው በዐሥረኛው ወር አስቴር ወደ ቤተ መንግሥቱ ተወሰደች። 17 ንጉሡም ከሌሎቹ ልጃገረዶች ሁሉ አስበልጦ ወደዳት፤ ከሌሎቹም ሁሉ ይበልጥ በፊቱ ሞገስንና መወደድን አገኘች፤ እርሱም መንግሥታዊውን ዘውድ አንሥቶ በራስዋ ላይ ደፋላትና በአስጢን ቦታ አነገሣት። 18 ከዚህም በኋላ ንጉሡ ስለ አስቴር ክብር ታላቅ ግብዣ አዘጋጅቶ ባለሟሎቹ የሆኑትን ባለሥልጣኖችና አስተዳዳሪዎች ሁሉ ጠራ፤ በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት በሚገኙት አገሮች ሁሉ የደስታ በዓል እንዲደረግ ዐወጀ፤ ለጋስነት የተሞላበት ንጉሣዊ ስጦታም አደረገ። መርዶክዮስ የንጉሡን ሕይወት እንዳዳነ 19 ደናግሉ ዳግመኛ በተሰበሰቡ ጊዜ መርዶክዮስ በንጉሡ ቤተ መንግሥት በር ላይ ሥልጣን ተሰጥቶት ነበር። 20 አስቴርም አይሁዳዊት መሆንዋን ገና አላስታወቀችም ነበር፤ መርዶክዮስም ይህን ለማንም እንዳትናገር በጥብቅ አስጠንቅቆአት ነበር፤ እርስዋም በሕፃንነትዋ ጊዜ በእርሱ ኀላፊነት ሥር ሳለች በሁሉ ነገር ትታዘዘው እንደ ነበር አሁንም በዚህ ነገር ታዘዘችለት። 21 መርዶክዮስ በቤተ መንግሥቱ በር ተቀምጦ በነበረበት ጊዜ ወደ ንጉሡ መኖሪያ ክፍሎች የሚያስገቡትን በሮች ይጠብቁ የነበሩት ቢግታንና ቴሬሽ ተብለው የሚጠሩት ሁለቱ የቤተ መንግሥት ጃንደረቦች በንጉሥ አርጤክስስ ላይ በጠላትነት ተነሣሥተው ሊገድሉት ዐድመው ነበር። 22 መርዶክዮስ ይህን ዐድማ በሰማ ጊዜ ለንግሥት አስቴር ነገራት፤ አስቴርም በመርዶክዮስ ስም ምሥጢሩን ለንጉሡ ነገረች። 23 ምርመራም በተደረገ ጊዜ የቀረበው መረጃ እውነት ሆኖ ተገኘ፤ ስለዚህም ሁለቱ ዐመፀኞች በስቅላት ሞት ተቀጡ፤ ንጉሡም ይህ ሁኔታ በንጉሠ ነገሥቱ የታሪክ መዝገብ ተጽፎ እንዲቀመጥ ትእዛዝ አስተላለፈ። |