Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

አስቴር 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ንግሥት አስጢን ለንጉሥ አርጤክስስ ትእዛዝ ያሳየችው እምቢተኛነት

1 ንጉሥ አርጤክስስ ከሕንድ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ያሉትን መቶ ኻያ ሰባት አገሮችን ይገዛ ነበር።

2 በዚያን ጊዜ ንጉሡ አርጤክስስ ሱሳ በምትገኘው ቤተ መንግሥቱ ይኖር ነበር።

3 አርጤክስስ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ባለሟሎቹ ለሆኑት ባለሥልጣኖችና አስተዳዳሪዎች ሁሉ ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ በግብዣውም ላይ የፋርስና የሜዶን ጦር አዛዦች፥ አገረ ገዢዎችና የክፍላተ ሀገር አስተዳዳሪዎች ተገኝተው ነበር።

4 ንጉሡም ለስድስት ወራት ያኽል የመንግሥቱን የሀብት ብዛትና የንጉሣዊውን ግርማ ሞገስና ክብር በይፋ እንዲታይ አደረገ።

5 ከዚህም በኋላ ንጉሥ አርጤክስስ የመናገሻ ከተማ በሆነችው በሱሳ ለሚኖሩ ሁሉ ለሀብታሞችም፥ ለድኾችም፥ እንደገና ሌላ ግብዣ አደረገ፤ በቤተ መንግሥቱ የአትክልት ቦታ ውስጥ የተደረገውም ያ ግብዣ አንድ ሳምንት ሙሉ ቈየ።

6 የአትክልት ቦታውም ከነጭ ጥጥ በፍታ በተሠሩ ሰማያዊ ቀለም ባላቸው መጋረጃዎች የተጌጠ ነበር፤ መጋረጃዎቹም ከሐምራዊ በፍታ በተሠሩና የብር ቀለበት በተበጀላቸው ገመዶች በዕብነ በረድ ምሰሶዎች ላይ ተንጠልጥለው ነበር፤ ከወርቅና ከብር የተሠሩ ድንክ አልጋዎችም ነጭና ቀይ፥ ቢጫና ሰማያዊ ቀለማትን በሚፈነጥቅ የዕብነ በረድ ወለል ላይ ተደርድረው ነበረ።

7 አንዱ ከሌላው በማይመሳሰል በልዩ ልዩ የወርቅ ዋንጫ መጠጥ ይታደል ነበር፤ የንጉሡ የወይን ጠጅ ብዛት ስለ ነበረው የወይን ጠጁ በገፍ እንዲሰጥ አደረገ፤

8 ንጉሡም ማንኛውም ሰው እንደየባህሉ የሚፈልገውን ያኽል መጠጣት ይችል ዘንድ ለቤተ መንግሥቱ አገልጋዮች ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር።

9 ይህ በዚህ እንዳለ ንግሥት አስጢን ደግሞ በበኲልዋ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ለሴት ወይዛዝርት ግብዣ አድርጋ ነበር።

10 ግብዣው በተጀመረ በሰባተኛው ቀን ንጉሥ አርጤክስስ በወይን ጠጅ ረክቶ ደስ ባለው ጊዜ መሁማን፥ ቢዝታ፥ ሐርቦና፥ ቢግታ፥ አባግታ፥ ዜታርና ካርካስ ተብለው የሚጠሩትን ጃንደረቦች የሆኑትን ሰባቱን የእልፍኝ አገልጋዮቹን ወደ እርሱ ጠርቶ፥

11 “ንግሥት አስጢን ልብሰ መንግሥትዋን ለብሳና ዘውድ ጭና ወደዚህ እንድትመጣ አድርጉ” አላቸው፤ ንጉሡ ይህንን ያደረገበት ምክንያት ንግሥት አስጢን እጅግ የተዋበች ስለ ነበረች ባለሟሎቹ ለሆኑት ባለሥልጣኖችና ለእንግዶቹ ሁሉ እንድትታይ ፈልጎ ነበር።

12 ነገር ግን ይህን የንጉሡን ትእዛዝ ለንግሥት አስጢን በነገሩአት ጊዜ ወደ ንጉሡ ፊት ለመቅረብ እምቢ አለች፤ ይህም ሁኔታ ንጉሡን እጅግ አስቈጣው።

13 ሕግና ባህልን በሚመለከት ጉዳይ፥ ብልኅ አማካሪዎችን መጠየቅ በንጉሡ ዘንድ የተለመደ ነገር ስለ ነበር፥ በዚህም ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚገባው ይመክሩት ዘንድ አማካሪዎቹን አስጠራ።

14 ዘወትር የሚያማክሩትም ካርሸና፥ ሼታር፥ አድማታ፥ ታርሺሽ፥ ሜሬስ፥ ማርሰናና መሙካን ተብለው የሚጠሩ በመንግሥቱ አመራር ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ሰባቱ የፋርስና የሜዶን ሹማምንት ነበሩ።

15 ንጉሡም እነዚህን አማካሪዎች “እኔ ንጉሥ አርጤክስስ ንግሥት አስጢንን ያመጡ ዘንድ በማዘዝ አገልጋዮቼን ብልክባት እርስዋ እምቢ ብላ ቀርታለች! ታዲያ፥ በእርስዋ ላይ መወሰድ ስለሚገባው እርምጃ ሕጉ ምን ይላል?” ሲል ጠየቃቸው።

16 ከዚህ በኋላ ከአማካሪዎቹ አንዱ የሆነው መሙካን እንዲህ ሲል የውሳኔ ሐሳብ አቀረበ፤ “በመሠረቱ ንግሥት አስጢን ያዋረደችው ንጉሡን ብቻ ሳይሆን ባለሟሎቹ የሆኑትን ባለሥልጣኖችና እንዲያውም በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ግዛት ውስጥ ያሉትን ወንዶች ሁሉ ጭምር ነው።

17 ከእንግዲህ ወዲህ በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ውስጥ የምትኖር ማንኛዋም ሴት፥ ንግሥት አስጢን ያደረገችውን ሁሉ ስትሰማ ባልዋን በንቀት ዐይን መመልከት ትጀምራለች፤ እነርሱም በበኩላቸው ‘ንጉሥ አርጤክስስ ንግሥት አስጢንን ወደ እርሱ እንድትመጣ ቢያስጠራት እምቢ ብላው ቀርታ የለምን?’ ይላሉ።

18 የፋርስና የሜዶን መንግሥት ባለሥልጣኖች ሚስቶች ይህን ንግሥቲቱ የፈጸመችውን አሳፋሪ ድርጊት በሚሰሙበት ጊዜ ዛሬውኑ ፀሐይ ሳትጠልቅ በባሎቻቸው ላይ መዘባነን ይጀምራሉ፤ በየሀገሩ የሚገኙ ሚስቶችም ባሎቻቸውን ማክበርን ይተዋሉ፤ ባሎችም ከሚስቶቻቸው ጋር መጣላት ሊኖርባቸው ነው።

19 ንጉሥ ሆይ! እንግዲህ መልካም ፈቃድህ ቢሆን፥ ንግሥት አስጢን ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አንተ ፊት መቅረብ ከቶ እንዳይፈቀድላት የሚገልጥ ውሳኔህን በዐዋጅ አስተላልፍ፤ ይህም ውሳኔ ከቶ የማይለወጥ ሆኖ ለዘለዓለም ይጸና ዘንድ በፋርስና በሜዶን ሕግ ውስጥ እንዲመዘገብ ትእዛዝ አስተላልፍ፤ የአስጢንንም የንግሥትነት ማዕርግ ከእርስዋ ለተሻለች ለሌላ ሴት ስጥ።

20 አንተ የምታስተላልፈውም ዐዋጅ እጅግ ታላቅ በሆነው በዚህ በንጉሠ ነገሥት መንግሥትህ ግዛት ሁሉ በይፋ በሚነገርበት ጊዜ እያንዳንድዋ ሴት ባለጸጋም ይሁን ወይም ድኻ ባልዋን በአክብሮት ትመለከታለች።”

21 ንጉሡና ባለሟሎቹ የሆኑ ባለሥልጣኖች ሁሉ ይህን ሐሳብ በደስታ ተቀበሉት፤ ንጉሡም መሙካን ያቀረበውን ምክር በሥራ ላይ አዋለ።

22 ስለዚህም ንጉሡ “እያንዳንዱ ባል የቤቱ አባወራ ሆኖ በአዛዥነት የመናገር መብቱ የተጠበቀ ይሁን!” የሚል ትእዛዝ በየቋንቋውና በየአጻጻፍ ሥርዓቱ ተዘጋጅቶ ወደያንዳንዱ አገር እንዲተላለፍ አደረገ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告