Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሐዋርያት ሥራ 28 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ጳውሎስ በማልታ ደሴት

1 ወደ ምድር በደኅና ከደረስን በኋላ የደረስንባት ደሴት ማልታ የምትባል መሆንዋን ዐወቅን።

2 የዚያች ደሴት ነዋሪዎች የሚያስደንቅ ደግነት አደረጉልን፤ በዚያን ጊዜም ዝናብ ስለ ዘነበና ብርድ ስለ ሆነ እሳት አንድደው ተቀበሉን፤

3 ጳውሎስ ጭራሮ ሰብስቦ ወደ እሳቱ ሲጥል፥ ከሙቀቱ የተነሣ አንድ እባብ ወጣና በእጁ ላይ ተጣብቆ ተንጠለጠለ፤

4 የማልታ ሰዎች እባብ በጳውሎስ እጅ ላይ ተንጠልጥሎ ባዩ ጊዜ “ይህ ሰው በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው! ከባሕሩ ማዕበል በደኅና ቢወጣም ከአምላክ ፍርድ አምልጦ በሕይወት ለመኖር አልቻለም” ተባባሉ።

5 ጳውሎስ ግን እባቡን ወደ እሳቱ አራግፎ ጣለውና ምንም ጒዳት ሳያገኘው ቀረ።

6 ሰዎቹም “ከአሁን አሁን ሰውነቱ ያብጣል፤ ወይም በድንገት ሞቶ ይወድቃል” በማለት ይጠባበቁ ነበር። ነገር ግን ብዙ ጊዜ ተጠባብቀውት ምንም ጒዳት እንዳልደረሰበት ባዩ ጊዜ አሳባቸውን ለወጡና “ይህስ አምላክ ነው!” አሉ።

7 በዚያ በነበርንበት ስፍራ አጠገብ የደሴቲቱ ገዢ የፑፕልዮስ መሬት ነበር፤ ይህ ሰው በቤቱ ተቀብሎን ሦስት ቀን በጥሩ ሁኔታ አስተናገደን።

8 በዚያን ጊዜ የፑፕልዮስ አባት ትኩሳትና ተቅማጥ ይዞት ታሞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስ ወደ እርሱ ገብቶ ጸለየለት፤ እጁንም ጫነበትና ፈወሰው።

9 ይህ ከሆነ በኋላ በደሴቲቱ የሚኖሩት ሌሎች በሽተኞች መጡና ተፈወሱ።

10 ሰዎቹ ብዙ ስጦታ አመጡልን፤ አክብሮታቸውንም ገለጡልን፤ በመርከብ ለመሄድ በተነሣንም ጊዜ የሚያስፈልገንን ሁሉ በመርከብ ላይ ጫኑልን።


የጳውሎስ ጒዞ ከማልታ ወደ ሮም

11 ሦስት ወር በማልታ ከቈየን በኋላ ክረምቱን በደሴቲቱ ባሳለፈው በእስክንድርያው መርከብ ተሳፍረን ተነሣን፤ መርከቡ ዲዮስቆሮስ የተባሉ የመንታ አማልክት አርማ ነበረበት።

12 ወደ ስራኩስ ከተማ በደረስን ጊዜ እዚያ ሦስት ቀን ተቀመጥን።

13 ከዚያም በባሕሩ ዞረን ወደ ሬጊዩም ከተማ ደረስን፤ እዚያ አንድ ቀን ካሳለፍን በኋላ የደቡብ ነፋስ ስለ ነፈሰ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ ሄድን።

14 እዚያ ወንድሞችን አገኘንና ከእነርሱ ጋር ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ ከዚህ በኋላ ወደ ሮም ሄድን።

15 በሮም ያሉ ምእመናን ስለ እኛ በሰሙ ጊዜ እስከ አፍዮስ ገበያና “ሦስት ማደሪያዎች” እስከሚባለው ቦታ ድረስ ሊቀበሉን መጡ፤ ጳውሎስ እነርሱን ባየ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነና ተጽናና።


ጳውሎስ በሮም

16 ወደ ሮም በገባን ጊዜ ጳውሎስ አንድ የሚጠብቀው ወታደር ተሰጠውና ብቻውን እንዲኖር ተፈቀደለት።

17 ከሦስት ቀን በኋላ ጳውሎስ በሮም የሚኖሩትን የአይሁድን ታላላቅ ሰዎች አስጠራ፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “ወንድሞቼ ሆይ፥ በእስራኤል ሕዝብ ላይና በአባቶች ሥርዓት ላይ ያደረግኹት ምንም በደል የለም፤ ይሁን እንጂ በኢየሩሳሌም ታስሬ ለሮማውያን ተላልፌ ተሰጠሁ።

18 ሮማውያን ከመረመሩኝ በኋላ በሞት የሚያስቀጣ ምክንያት ስላላገኙብኝ በነጻ ሊለቁኝ አስበው ነበር።

19 አይሁድ ግን የእኔን በነጻ መለቀቅ በተቃወሙ ጊዜ ወደ ሮም ንጉሠ ነገሥት ይግባኝ ለማለት ተገደድኩ፤ ሆኖም ሕዝቤን የምከስበት ነገር አልነበረኝም።

20 አሁንም ያስጠራኋችሁ እንዳያችሁና ይህንንም እንድነግራችሁ ነው፤ እኔ በዚህ በሰንሰለት የታሰርኩት ለእስራኤል በተሰጠው ተስፋ ምክንያት ነው።”

21 እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “ከይሁዳ ምድር ስለ አንተ ጉዳይ የተጻፈ ደብዳቤ አልደረሰንም፤ ወደዚህ ከመጡ ሰዎች ማንም ስለ አንተ ክፉ ያወራ ወይም የተናገረ የለም።

22 ይህን አንተ የምትከተለውን የሃይማኖት ክፍል በየቦታው ሰዎች እንደሚቃወሙት እናውቃለን፤ ስለዚህ የአንተ አሳብ ምን እንደ ሆነ መስማት እንፈልጋለን።”

23 ቀን ከቀጠሩለትም በኋላ ብዙ ሆነው ወደ መኖሪያ ቤቱ መጡ፤ እርሱም ከጧት እስከ ማታ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት በመመስከር አሳቡን ገለጠላቸው፤ እነርሱንም ለማሳመን ከሙሴ ሕግና ከነቢያት መጻሕፍት እየጠቀሰም ስለ ኢየሱስ አስረዳቸው።

24 አንዳንዶቹ የተናገረውን ቃል አመኑ፤ ሌሎች ግን አላመኑም።

25 እነርሱም እርስ በርሳቸው ሳይስማሙ ተለያዩ። ሆኖም ከመለያየታቸው በፊት ጳውሎስ ለመጨረሻ ጊዜ ሲናገር እንዲህ አለ፦ “መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ አማካይነት ለአባቶቻችሁ የተናገረው ልክ ነበር!

26 የተናገረውም ቃል ይህ ነው፦ ‘ወደዚህ ሕዝብ ሂድና መስማትስ ትሰማላችሁ፤ ግን አታስተውሉም፤ ማየትስ ታያላችሁ፤ ግን ልብ አታደርጉም በላቸው፤

27 የእነዚህ ሰዎች ልብ ደንድኖአል፤ ጆሮአቸውም ተጨፍኖአል፤ ዐይናቸውም ተዘግቶአል፤ እንዲህስ ባይሆን ኖሮ፥ በዐይናቸው አይተው፥ በጆሮአቸው ሰምተው፥ በልባቸውም አስተውለው፥ ወደ እኔ በተመለሱና እኔም በፈወስኩአቸው ነበር።’

28 “እንግዲህ የእግዚአብሔር አዳኝነት መልእክት ለአሕዛብ እንደ ተላከ ዕወቁ፤ እነርሱም እሺ ብለው ይቀበሉታል።”

29 [“ጳውሎስ ይህን ከተናገረ በኋላ አይሁድ በብርቱ እየተከራከሩ ከዚያ ወጥተው ሄዱ።”]

30 ጳውሎስ በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፤ ወደ እርሱ የሚመጡትንም ሰዎች ሁሉ ይቀበል ነበር፤

31 የእግዚአብሔርንም መንግሥት በመስበክ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንም ሳይከለክለው በድፍረት ያስተምር ነበር።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告