ሐዋርያት ሥራ 23 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ጳውሎስም ሸንጎውን ትኲር ብሎ ተመለከተና “ወንድሞቼ ሆይ! እስከ ዛሬ ድረስ ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ፊት የኖርኩት በመልካም ኅሊና ነው” አለ። 2 የካህናት አለቃው ሐናንያ ግን ጳውሎስን አፉን እንዲመቱት በጳውሎስ አጠገብ የቆሙትን ሰዎች አዘዘ። 3 በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ሐናንያን፥ “አንተ በኖራ የተለሰነ ግድግዳን የምትመስል! አንተንም እግዚአብሔር ይመታሃል! በሕግ መሠረት የእኔን ጉዳይ ልትፈርድ ተቀምጠህ ሳለ ያለ ሕግ እንዲመቱኝ ታዛለህን?” 4 እዚያ የነበሩ ሰዎች ጳውሎስን “የእግዚአብሔርን የካህናት አለቃ ትሳደባለህን?” አሉት። 5 ጳውሎስም “ወንድሞቼ ሆይ! የካህናት አለቃ መሆኑን አላወቅሁም ነበር፤ ምክንያቱም ‘በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ ቃል አትናገር’ የሚል ተጽፎአል” አለ። 6 ጳውሎስ እዚያ ከነበሩት ሰዎች እኩሌቶቹ ሰዱቃውያን እኩሌቶቹ ደግሞ ፈሪሳውያን መሆናቸውን ዐውቆ “ወንድሞቼ ሆይ! እኔ ከፈሪሳዊ የተወለድኩ ፈሪሳዊ ነኝ፤ እነሆ! አሁን በፍርድ ፊት የቀረብኩት በተሰጠው ተስፋና በሙታን ትንሣኤ ምክንያት ነው” ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ በሸንጎው መካከል ተናገረ። 7 ጳውሎስ ይህን በተናገረ ጊዜ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጠብ ተነሥቶ ሸንጎው ለሁለት ተከፈለ። 8 ሰዱቃውያን “ትንሣኤ የለም፤ መላእክትም የሉም፤ መንፈስም የለም” ሲሉ ፈሪሳውያን ግን “እነዚህ ሁሉ አሉ” ብለው ያምናሉ። 9 በዚህ ጊዜ ታላቅ ሁካታ ሆነ፤ ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንድ የሕግ መምህራንም ተነሡና “እኛ በዚህ ሰው ላይ ምንም ክፉ ነገር አላገኘንበትም፤ መንፈስ ወይም መልአክ ተናግሮት ይሆናል፤ እኛ ምን እናውቃለን?” በማለት ተከራከሩ። 10 ጠቡ እየከረረ ስለ ሄደ ሰዎቹ ጳውሎስን እንዳይቦጫጭቁት ፈርቶ አዛዡ “ውረዱና ጳውሎስን ከሰዎቹ መካከል ነጥቃችሁ አምጡ! ወደ ጦሩ ሰፈርም ውሰዱት!” በማለት ወታደሮቹን አዘዘ። 11 በማግስቱ ሌሊት ጌታ በጳውሎስ አጠገብ ቆሞ “አይዞህ በኢየሩሳሌም እንደ መሰከርክልኝ፥ እንዲሁም በሮም ልትመሰክርልኝ ይገባሃል” አለው። ጳውሎስን ለመግደል የተደረገ ሤራ 12 በነጋ ጊዜ አይሁድ ተሰበሰቡና “ጳውሎስን ሳንገድል እህል አንበላም፤ ውሃም አንጠጣም” ብለው ተማማሉ። 13 በዚህ ሤራ የተስማሙ ሰዎች ቊጥራቸው ከአርባ በላይ ነበር። 14 እነርሱ ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎች ሄደው እንዲህ ሲሉ ነገሩአቸው፤ “ጳውሎስን ሳንገድል እህል እንዳንቀምስ በጥብቅ ተማምለናል፤ 15 ስለዚህ እናንተ ከሸንጎው ጋር ተስማምታችሁ በጥብቅ የምትመረምሩት ነገር እንዳለ በማስመሰል ጳውሎስን እንዲያመጡላችሁ አዛዡን ጠይቁት፤ እኛም እዚህ ከመድረሱ በፊት ልንገድለው ተዘጋጅተናል።” 16 ነገር ግን የጳውሎስ የእኅት ልጅ ይህን ሤራ ስለ ሰማ ወደ ወታደሮች ሰፈር ሄዶ ገባና ለጳውሎስ ነገረው። 17 ጳውሎስም ከመቶ አለቆች አንዱን ጠርቶ “ይህ ልጅ ለጦር አዛዡ የሚናገረው ነገር ስላለው ወደ እርሱ አቅርበው” አለው። 18 የመቶ አለቃውም ልጁን ወደ አዛዡ ይዞ ገባና “እስረኛው ጳውሎስ ጠርቶኝ ይህ ልጅ ለአንተ የሚነግርህ ነገር ስላለው ወደ አንተ እንዳቀርበው ለመነኝ” አለ። 19 አዛዡም የልጁን እጅ ይዞ ገለል አደረገውና “የምትነግረኝ ነገር ምንድን ነው?” ሲል ለብቻው ጠየቀው። 20 ልጁም እንዲህ አለ፤ “አይሁድ የጳውሎስን ነገር በጥብቅ የሚመረምሩ መስለው ነገ ወደ ሸንጎው እንድታቀርብላቸው ሊጠይቁህ ተስማምተዋል። 21 ነገር ግን እሺ አትበላቸው፤ እርሱን ሳንገድል እህል አንበላም፤ ውሃም አንጠጣም በማለት የተማማሉ ከአርባ የሚበልጡ ሰዎች እርሱን ለመግደል አድፍጠዋል፤ አሁን እነርሱ የሚጠብቁት የአንተን መልስ ብቻ ነው።” 22 አዛዡም “ይህን ነገር ለእኔ መንገርህን ለማንም አትግለጥ” ብሎ ልጁን አሰናበተው። ጳውሎስ በአገረ ገዥው በፊልክስ ፊት መቅረቡ 23 ከዚህ በኋላ የጦር አዛዡ ከመቶ አለቆቹ ሁለቱን ጠርቶ “ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ሲሆን ወደ ቂሳርያ የሚሄዱ ሁለት መቶ ወታደሮችና ሰባ ፈረሰኞች፤ ሁለት መቶ ጦር ወርዋሪዎችም አዘጋጁ፤ 24 ለጳውሎስም ፈረስ አዘጋጁለትና ወደ አገረ ገዥው ወደ ፊልክስ በደኅና እንዲደርስ አድርጉት” አላቸው። 25 እንዲህ የሚል ደብዳቤም ጻፈ፤ 26 “ከቀላውዴዎስ ሉስዮስ፤ ለክቡር አገረ ገዢ ፊልክስ! ሰላም ለአንተ ይሁን! 27 ይህን ሰው አይሁድ ይዘው ሊገድሉት ነበር፤ እኔ ግን የሮም ዜጋ መሆኑን ስላወቅሁ ከወታደሮች ጋር ደርሼ አዳንኩት። 28 በምን ምክንያት እንደ ከሰሱት ለማወቅ ፈልጌም ወደ ሸንጎአቸው አቅርቤው ነበር። 29 የከሰሱትም ሕጋቸውን በሚመለከት ነገር መሆኑን ተረዳሁ፤ ነገር ግን ለሞት ወይም ለእስራት የሚያደርሰው ነገር የለም። 30 ይህን ሰው ለመግደል ሤራ እንደ ተደረገ በሰማሁ ጊዜ ወዲያውኑ ወደ አንተ ላክሁት፤ ከሳሾቹም በእርሱ ላይ ያላቸውን ክስ በአንተ ፊት እንዲያቀርቡ ነግሬአቸዋለሁ።” 31 ስለዚህ ወታደሮቹ በታዘዙት መሠረት ጳውሎስን በሌሊት ወስደው ወደ አንቲጳጥሪስ አደረሱት። 32 በማግስቱ ፈረሰኞቹ ከጳውሎስ ጋር ጒዞአቸውን እንዲቀጥሉ አድርገው እነርሱ ወደ ጦር ሰፈሩ ተመለሱ። 33 ፈረሰኞቹ ወደ ቂሳርያ በደረሱ ጊዜ ደብዳቤውን ለአገረ ገዥው ሰጡና ጳውሎስን በፊቱ አቀረቡት። 34 አገረ ገዥው ደብዳቤውን ካነበበ በኋላ ጳውሎስን “ከየትኛው ክፍለ ሀገር ነህ?” ሲል ጠየቀው፤ የኪልቅያ ሰው መሆኑን ባወቀ ጊዜ 35 “ከሳሾችህ ሲመጡ ጉዳይህን እሰማለሁ” አለው። በሄሮድስ ቤተ መንግሥት ውስጥ እንዲጠበቅም አዘዘ። |