Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የንግሥተ ሳባ ጒብኝት በኢየሩሳሌም
( 1ነገ. 10፥1-13 )

1 ንግሥተ ሳባ ስለ ሰሎሞን የሚነገረውን አስደናቂ ጥበብ ሁሉ ሰማች፤ ስለዚህ አስቸጋሪ በሆኑ የእንቆቅልሽ ጥያቄዎች ልትፈትነው ወደ ኢየሩሳሌም መጣች፤ ወደ ኢየሩሳሌም ስትመጣም ብዙ የክብር አጃቢዎችን አስከትላ ሽቶ፥ የከበሩ ዕንቆችና እጅግ የበዛ ወርቅ በግመሎች አስጭና ነበር፤ ከሰሎሞንም ጋር በተገናኘች ጊዜ በሐሳብዋ የነበረውን ጥያቄ ሁሉ አቀረበችለት፤

2 እርሱም ላቀረበችለት ጥያቄ ሁሉ መልስ ሰጠ፤ ሊተረጒምላት የተሳነውና ከእርሱ የተሰወረ ምንም ዐይነት እንቆቅልሽ አልነበረም።

3 ንግሥተ ሳባም ጥበብ የተሞላበትን የሰሎሞንን አነጋገር አዳመጠች፤ እርሱ ያሠራውንም ቤተ መንግሥት አየች፤

4 በሰሎሞን ገበታ ላይ የሚቀርበውን የምግብ ዐይነት፥ የመኳንንቱ አቀማመጥ፥ የቤተ መንግሥቱን ሠራተኞች የሥራ አደረጃጀት፥ የመጠጥ አሳላፊዎቹ የደንብ ልብስ ዐይነት፥ በግብዣ ጊዜ የሚያገለግሉትን አሳላፊዎችና በቤተ መቅደስም የሚያቀርባቸውን መሥዋዕቶች ሁሉ ተመለከተች፤ በዚህም ሁሉ የተሰማት አድናቆት ከጠበቀችው በላይ ነበር።

5 ንጉሥ ሰሎሞንንም እንዲህ አለችው “ስለ አንተ ሥራና ስለ ጥበብህ ታላቅነት በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ሁሉ እውነት ነው!

6 ይሁን እንጂ እዚህ መጥቼ ሁሉን ነገር በዐይኔ እስካየሁ ድረስ የተነገረኝን ሁሉ አላመንኩም ነበር፤ ታዲያ በጆሮዬ የሰማሁት በዐይኔ ያየሁትን እኩሌታ እንኳ አልሆነም፤ በእርግጥም ጥበብህ ከተነገረኝ በጣም ይበልጣል፤

7 ዘወትር በአንተ ፊት በመገኘት ጥበብ የተሞላበት ንግግርህን የሚሰሙ ባለሟሎችና አገልጋዮችህ እንዴት የታደሉ ናቸው!

8 ንጉሥ ሆነህ በእርሱ ስም ትገዛ ዘንድ አንተን መርጦ የእስራኤል ንጉሥ ለማድረግ መልካም ፈቃዱ ስለ ሆነ አምላክህ እግዚአብሔር ይመስገን! በፍቅሩም እስራኤል ለዘለዓለም ጸንቶ እንዲኖር ስለ ፈለገ ሕግና ፍትሕ ጸንቶ እንዲኖር ታደርግ ዘንድ አንተን መርጦ ንጉሥ አድርጎሃል።”

9 ንግሥተ ሳባ ያመጣችውን ከአራት ሺህ ኪሎ የሚበልጥ ወርቅ፥ እጅግ ብዙ ሽቶና ዕንቊ ገጸ በረከት አድርጋ ለሰሎሞን ሰጠችው፤ እርስዋ ለሰሎሞን የሰጠችው የሽቶ ዐይነት፥ ከዚያ በፊት ከቶ ታይቶ የማይታወቅ ነው።

10 ከኦፊር ወርቅ ያመጡ የንጉሥ ኪራምና የንጉሥ ሰሎሞን ሰዎች ከዚያው ከኦፊር የሰንደል እንጨትና ዕንቊ ለሰሎሞን አምጥተውለት ነበር፤

11 ሰሎሞንም የሰንደሉን እንጨት የቤተ መቅደሱንና የቤተ መንግሥቱን ደረጃዎች እንዲሁም የመዘምራኑን መሰንቆና በገና አሠራበት፤ እነዚህን የዜማ መሣሪያዎች የመሰለ ከዚያ በፊት በይሁዳ ምድር ከቶ አልታየም።

12 ንጉሥ ሰሎሞን እርስዋ ካመጣችው ስጦታ በላይ የሳባ ንግሥት የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣት፤ ከዚህ በኋላ ንግሥተ ሳባ ከክብር አጃቢዎችዋ ጋር ወደ አገርዋ ተመልሳ ሄደች።


የንጉሥ ሰሎሞን ሀብት ብዛት
( 1ነገ. 10፥14-25 )

13 ንጉሥ ሰሎሞን በየዓመቱ ኻያ ሦስት ሺህ ኪሎ ያኽል የሚመዝን ወርቅ ያገኝ ነበር፤

14 ይህም ነጋዴዎች ከሚከፍሉት ቀረጥ፥ እንዲሁም ከዐረብ ነገሥታትና ከእስራኤል ክፍላተ ሀገር አስተዳዳሪዎች ከሚገባለት ግብር ሌላ ተጨማሪ ነበር።

15 ንጉሥ ሰሎሞን እያንዳንዳቸው ሰባት ኪሎ በሚያኽል ንጹሕ ወርቅ የተለበጡ ሁለት መቶ ታላላቅ ጋሻዎችንና

16 እያንዳንዳቸው ሦስት ኪሎ በሚያኽል ንጹሕ ወርቅ የተለበጡ ሦስት መቶ አነስተኛ ጋሻዎችን አሠርቶ ነበር፤ እነዚህንም ሁሉ ጋሻዎች “የሊባኖስ ደን” ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ውስጥ አኖራቸው።

17 እንዲሁም ንጉሥ ሰሎሞን ከዝሆን ጥርስ አንድ ትልቅ ዙፋን አሠርቶ በንጹሕ ወርቅ አስለበጠው፤

18-19 ዙፋኑም ከታች ወደ ላይ መወጣጫ የሆኑ ስድስት ደረጃዎች ነበሩት፤ በእያንዳንዱም ደረጃ ጫፍ በግራና በቀኝ አንዳንድ የአንበሳ ምስል ሲኖር በድምሩ የተቀረጹት የአንበሳ ምስሎች ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ከዙፋኑ ጋር ተያይዞ ከወርቅ የተሠራ የእግር መረገጫም ነበረው፤ በሁለቱ የክንድ መደገፊያ ጫፎችም ላይ አንዳንድ የአንበሳ ምስል ነበር፤ በሌላ በየትኛውም አገር መንግሥት ይህን የመሰለ ዙፋን ከቶ አልነበረም።

20 ንጉሥ ሰሎሞን የሚጠጣባቸው ዋንጫዎችና “የሊባኖስ ደን” ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ውስጥ የሚገኙት ዕቃዎች ሁሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ብር ከመብዛቱ የተነሣ ዋጋ እንዳለው ሆኖ አይቈጠርም ነበር።

21 ሰሎሞንም በኪራም አገልጋዮች አማካይነት ወደ ተርሴስ የሚጓዙ መርከቦች ነበሩት፤ እነርሱም በየሦስት ዓመቱ ወርቅን፥ ብርን፥ የዝሆን ጥርስን፥ ጦጣዎችንና ዝንጀሮዎችን ያመጡለት ነበር።

22 ንጉሥ ሰሎሞን በዓለም ከሚገኝ ከማንኛውም ንጉሥ ይበልጥ ሀብታምና ጥበበኛ ነበር፤

23 በመላው ዓለም የሚገኙ ነገሥታት ሁሉ እግዚአብሔር የሰጠውን ጥበብ የሞላበትን ንግግር ይሰሙ ዘንድ ከሰሎሞን ጋር መገናኘት ይፈልጉ ነበር።

24 ወደ እርሱም የሚመጡት ሁሉ የብርና የወርቅ፥ የልብስ፥ የጦር መሣሪያዎች፥ የሽቶ፥ የፈረሶችና የበቅሎዎች ስጦታዎችን ያመጡለት ነበር፤ ይህም በየዓመቱ የሚደረግ ነበር።

25 ንጉሥ ሰሎሞን ለሠረገሎቹና ለፈረሶቹ አራት ሺህ ጋጣዎች፥ እንዲሁም ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት፤ ከእነርሱም ከፊሉን በኢየሩሳሌም፥ የቀሩትም ደግሞ በሌሎች ልዩ ልዩ ከተሞች ተመድበው እንዲኖሩ አደረገ፤

26 ሰሎሞን ከኤፍራጥስ ወንዝ አንሥቶ እስከ ፍልስጥኤም ምድርና እስከ ግብጽ ግዛት ዳርቻ ድረስ ያሉትን ነገሥታት ሁሉ ያስገብር ነበር፤

27 በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት በኢየሩሳሌም ብር እንደ ድንጋይ፥ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ብዛት በይሁዳ ኰረብቶች ግርጌ በየትኛውም ስፍራ እንደሚበቅል ሾላ ይቈጠር ነበር።

28 ሰሎሞን ከግብጽና ከሌሎች አገሮች ሁሉ ፈረሶችን ያስመጣ ነበር።


የሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ታሪክ ባጭሩ
( 1ነገ. 11፥41-43 )

29 ሌላው የሰሎሞን ታሪክ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በነቢዩ ናታን ታሪክ፥ የሴሎ ተወላጅ በሆነው በነቢዩ አኪያ ትንቢትና ስለ እስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ጭምር በሚናገረው በነቢዩ ዒዶ ራእይ ተመዝግቦ ይገኛል፤

30 ሰሎሞን መኖሪያውን በኢየሩሳሌም አድርጎ በመላው እስራኤል ላይ አርባ ዓመት ነገሠ፤

31 ከዚያም በኋላ ሞተ፤ በዳዊት ከተማም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ሮብዓም ነገሠ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告