2 ዜና መዋዕል 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሰሎሞን ያከናወናቸው ሌሎች ሥራዎች ( 1ነገ. 9፥10-28 ) 1 ሰሎሞን ቤተ መቅደሱንና ቤተ መንግሥቱን ለመሥራት ኻያ ዓመት ፈጀበት፤ 2 እንዲሁም ንጉሥ ኪራም የሰጠውን ከተሞች እንደገና ሠርቶ እስራኤላውያን እንዲሰፍሩባቸው አደረገ፤ 3 ሰሎሞን በሐማትና በጾባ ግዛቶች ላይ ዘምቶ በቊጥጥሩ ሥር አደረጋቸው፤ 4 በበረሓ የምትገኘውን የታጽሞርን ከተማና በሐማት ያለውን የስንቅና የትጥቅ ማኖሪያ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ አጠናከረ፤ 5 እንዲሁም ሰሎሞን በላይኛውና በታችኛው ቤትሖሮን በብረት መዝጊያ ሊዘጉ የሚችሉ ቅጽር በሮች ያሉአቸው የተመሸጉ ከተሞችን እንደገና ሠራ፤ 6 የባዕላት ከተማ፥ ስንቅና ትጥቅ የሚያስቀምጥባቸው ከተሞች ሁሉ፥ ፈረሶችና ሠረገሎች የሚኖሩባቸው ከተሞች፤ በዚህም ዐይነት ሰሎሞን በኢየሩሳሌም፥ በሊባኖስና በእርሱ አስተዳደር ባለው ግዛት በሙሉ ሊሠራ ያቀዳቸውን የግንባታ ሥራዎች ሁሉ ፈጸመ። 7-8 ሰሎሞን በጒልበት ሥራ ያሰማራቸው ገባሮች፥ እስራኤላውያን ምድራቸውን ርስት አድርገው በያዙ ጊዜ ያልገደሉአቸው የከነዓን ሕዝብ ዘሮች ነበሩ፤ እነዚህም የከነዓን ዘሮች እስከ አሁን ድረስ ባሪያዎች ሆነው የሚያገለግሉ ሒታውያን፥ አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን ናቸው፤ 9 ሰሎሞን ከእስራኤላውያን ወገን ማንንም ባሪያ አድርጎ አላሠራም፤ እስራኤላውያን ወታደሮች፥ የጦር መኰንኖች፥ የጦር አዛዦች፥ ሠረገላ ለሚነዱ ሁሉ ኀላፊዎችና ፈረሰኞች ሆነው ያገለግሉ ነበር። 10 ሰሎሞን ለሚያከናውነው ልዩ ልዩ የሕንጻ ሥራ፥ የጒልበት ሥራ ይሠሩ ዘንድ ለተመደቡት ገባሮች ሁለት መቶ ኀምሳ እስራኤላውያን ኀላፊዎች ነበሩአቸው። 11 ሰሎሞን “የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ያለበት ስፍራ ሁሉ ቅዱስ ስለ ሆነ፥ ግብጻዊት ሚስቴ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት ቤተ መንግሥት ውስጥ መኖር አይገባትም” በማለት የግብጽ ንጉሥ ልጅ የሆነችውን ሚስቱን ከዳዊት ከተማ አውጥቶ እርሱ ወዳሠራላት ወደ ሌላ መኖሪያ ቤት ተዘዋውራ እንድትኖር አደረገ። 12 ሰሎሞን በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ባሠራው መሠዊያ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ 13 ሙሴ ባዘዘው መሠረትም በእያንዳንዱ የበዓል ቀን ማለትም በየሰንበቱ፥ በየወሩ መባቻ፥ በየዓመቱ በሚከበሩ ሦስት በዓላት ማለትም በቂጣ በዓል፥ በመከር በዓልና በዳስ በዓል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቀርብ ነበር። 14 አባቱ ዳዊት የደነገጋቸውን መመሪያዎች በመከተልም የካህናቱንና ካህናቱን በሥራና መዝሙር በመዘመር የሚረዱትን ሌዋውያን የየዕለቱን የሥራ መደብ አቀናበረ፤ እንዲሁም የእግዚአብሔር ሰው ዳዊት ባዘዘው መሠረት የቤተ መቅደሱ ዘበኞች በእያንዳንዱ ቅጽር በር የዕለት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ አከፋፍሎ መደበ። 15 እነርሱም ስለ ግምጃ ቤቶችና ስለ ሌሎችም ጉዳዮች ዳዊት ለካህናትና ለሌዋውያን በሰጠው መመሪያ መሠረት አንድም ሳይቀር ሁሉም በሚገባ እንዲከናወን አደረጉ። 16 በዚህም ጊዜ የሰሎሞን የሥራ ዕቅድ ሁሉ፥ ማለትም ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት መጣል ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ ሥራው ሁሉ በተሳካ ሁኔታ ተከናወነ። 17 ከዚህ በኋላ ሰሎሞን በኤዶም ምድር የባሕር ወደብ ወደሆኑት ወደ ዔጽዮንጋብርና ወደ ኤላት ሄደ፤ 18 ንጉሥ ኪራም በሠለጠኑ መርከበኞች የሚነዱና በራሱ መኰንኖች የሚመሩ መርከቦችን ለሰሎሞን ልኮለት ነበር፤ እነርሱም ከሰሎሞን መኰንኖች ጋር በመሆን ወደ ኦፊር ምድር መጡ፤ ከዚያም ከዐሥራ አምስት ሺህ ኪሎ የሚበልጥ ወርቅ ለሰሎሞን ይዘውለት መጡ። |