2 ዜና መዋዕል 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየቤተ መቅደሱ መመረቅ ( 1ነገ. 8፥62-66 ) 1 ንጉሥ ሰሎሞን ጸሎቱን እንደ ፈጸመ ወዲያውኑ እሳት ከሰማይ ወርዶ የሚቃጠለውንና ሌላውን መሥዋዕት በላ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ቤተ መቅደሱን ሞላው፤ 2 ቤተ መቅደሱ በእግዚአብሔር ክብር ስለ ተሞላ ካህናቱ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግባት አልቻሉም። 3 እስራኤላውያን እሳት ከሰማይ ሲወርድና የእግዚአብሔርም ክብር በቤተ መቅደስ ላይ ማረፉን ባዩ ጊዜ በግንባራቸው ወደ መሬት ተደፍተው፦ “እግዚአብሔር ቸር ነው፤ ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ነው!” እያሉ ሰገዱ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ። 4 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞንና በዚያ የነበረው ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት አቀረቡ፤ 5 ሰሎሞንም ኻያ ሁለት ሺህ የቀንድ ከብቶችና አንድ መቶ ኻያ ሺህ በጎችን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ በዚህም ዐይነት ንጉሥ ሰሎሞንና ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን ለእግዚአብሔር የተለየ እንዲሆን አደረጉ። 6 ካህናቱም በተመደበላቸው ቦታ ቆሙ፤ ከእነርሱም ፊት ለፊት ሌዋውያን ቆመው አስቀድሞ ንጉሥ ዳዊት አሠርቶ እግዚአብሔርን ለማመስገን ይጠቀምባቸው በነበሩት የዜማ መሣሪያዎች ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ እያሉ በመዘመር እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር፤ ካህናቱም መለከት ሲነፉ እስራኤላውያን ሁሉ ቆመው ነበር። 7 እንዲሁም ሰሎሞን ከቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ያለውን አደባባይ መካከለኛ ክፍል ለእግዚአብሔር የተለየ እንዲሆን አደረገ፤ ቀጥሎም በሙሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእህል መባና የኅብረት መሥዋዕት፥ የእንስሶች ስብ ሁሉ በዚያ ስፍራ ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት ከነሐስ ያሠራው መሠዊያ ይህን ሁሉ መሥዋዕት መያዝ ስለማይችል ነው። 8 በዚያም በቤተ መቅደሱ ሰሎሞንና እስራኤላውያን ሁሉ ሰባት ቀን ሙሉ የዳስ በዓል አክብረው ሰነበቱ፤ በስተ ሰሜን ከሐማት መተላለፊያ አንሥቶ በስተ ደቡብ እስከ ግብጽ ሸለቆ ድረስ ካለው ምድር ሁሉ የመጣው ሕዝብ እጅግ ብዙ ነበር። 9 መሠዊያውን ለእግዚአብሔር የተለየ በማድረግ ሥነ ሥርዓት ላይ ሰባት ቀን አሳለፉ፤ ሌላ ሰባት ቀን በዓሉን በማክበር ከሰነበቱ በኋላ በስምንተኛው ቀን የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ተደርጎ የበዓሉ ፍጻሜ ሆነ፤ 10 በማግስቱ ማለትም በሰባተኛው ወር በሃያ ሦስተኛው ቀን ሰሎሞን፥ ወደሚኖሩበት ስፍራ እንዲሄዱ ሰዎቹን አሰናበተ፤ እነርሱም እግዚአብሔር ለሕዝቡ ለእስራኤል፥ ለዳዊትና ለሰሎሞን ስለ ሰጠው በረከት ተደስተው ወደየመኖሪያ ስፍራቸው ሄዱ። እግዚአብሔር ለሰሎሞን እንደገና መገለጡ ( 1ነገ. 9፥1-9 ) 11 ንጉሥ ሰሎሞን የቤተ መቅደሱንና የቤተ መንግሥቱን ሥራ ሁሉ ባቀደው መሠረት በተሳካ ሁኔታ ከፈጸመ በኋላ፥ 12 እግዚአብሔር በሌሊት ተገልጦለት እንዲህ አለው፤ “ጸሎትህን ሰምቼአለሁ፤ ይህን ቤተ መቅደስ ለእኔ መሥዋዕት የሚቀርብበት ስፍራ ይሆን ዘንድ መርጬዋለሁ፤ 13 ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማያትን በምዘጋበት ጊዜ፥ ወይም ሰብሉን እንዲበላ አንበጣ በምልክበት ጊዜ፥ ወይም ቸነፈር በሕዝቤ ላይ በማወርድበት ጊዜ ሁሉ፥ 14 በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ እስራኤላውያን ራሳቸውን አዋርደው ከሚያደርጉት ክፉ ነገር በመራቅ ተጸጽተውና ንስሓ ገብተው ወደ እኔ ቢጸልዩ በሰማይ ሆኜ እሰማቸዋለሁ፤ ኃጢአታቸውን ይቅር እልላቸዋለሁ፤ ምድራቸውም እንደገና ፍሬያማ እንድትሆን አደርጋለሁ፤ 15 ይህን ቤተ መቅደስ እጠብቀዋለሁ፤ በዚህ ቤተ መቅደስ የሚቀርበውንም ጸሎት ሁሉ እሰማለሁ። 16 ለዘለዓለም የስሜ መጠሪያ ይሆን ዘንድ ይህን ቤተ መቅደስ መርጬዋለሁ ቀድሼዋለሁም፤ በልቤም ውስጥ አድርጌ ዘወትር እጠብቀዋለሁ። 17 አባትህ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ አንተም በታማኝነት ብታገለግለኝ፥ ሕጎቼንና ሥርዓቴን በመጠበቅ ትእዛዞቼን ሁሉ ብትፈጽም፥ 18 ለአባትህ ለዳዊት ‘ከዘርህ መካከል በእስራኤል ላይ የሚነግሥ ዘወትር ይኖራል’ ስል በሰጠሁት የተስፋ ቃል መሠረት መንግሥትህን አጸናለሁ፤ 19 ነገር ግን አንተና ሕዝብህ እኔ የሰጠኋችሁን ሕጎችና ትእዛዞች ባትጠብቁ፥ ባዕዳን አማልክትንም ብታመልኩና፥ ብትሰግዱላቸው፥ 20 እኔ ከሰጠኋችሁ ከምድሬ ተነቅላችሁ እንድትባረሩ አደርጋለሁ፤ እኔ ለስሜ የቀደስኩትን ይህን ቤተ መቅደስ እተወዋለሁ፤ በሁሉ ስፍራ የሚኖሩ ሕዝቦችም በንቀት መሳለቂያና መዘባበቻ ያደርጉታል። 21 “ይህ ቤተ መቅደስ እነሆ አሁን ከፍ ያለ ክብር አለው፤ በዚያን ጊዜ ግን በቤተ መቅደሱ አጠገብ የሚያልፍ ሰው ሁሉ በመገረም ‘እግዚአብሔር በዚህች ምድርና በዚህ ቤተ መቅደስ ላይ ስለምን እንደዚህ አደረገ?’ ብሎ ይጠይቃል፤ 22 ሰዎችም ‘እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ጥፋት በእነርሱ ላይ ያደረሰባቸው ከግብጽ ያወጣቸውን የቀድሞ አባቶቻቸውን አምላክ ትተው ሌሎችን አማልክት ስለ ተከተሉና ስለ ሰገዱላቸው ነው’ ሲሉ ይመልሱላቸዋል።” |