Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ሰሎሞን ለሕዝቡ የተናገረው ቃል
( 1ነገ. 8፥12-21 )

1 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፥ ‘በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እኖራለሁ’ ብለሃል፤

2 እነሆ እኔ ግርማ ያለው ውብ ቤተ መቅደስ ለአንተ ሠርቼአለሁ፤ ይህም ቤተ መቅደስ አንተ ለዘለዓለም የምትኖርበት ስፍራ ይሆናል።”

3 በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን በዚያ ቆመው ነበር፤ ንጉሥ ሰሎሞንም ወደ እነርሱ ፊቱን መልሶ፥ የእግዚአብሔር በረከት በእነርሱ ላይ እንዲወርድ እንዲህ ሲል ጸለየ፤

4 “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን! እርሱ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠውን የተስፋ ቃል ፈጽሞአል፤ የሰጠውም የተስፋ ቃል እንዲህ የሚል ነው፦

5 ‘ሕዝቤን ከግብጽ ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በስሜ ቤተ መቅደስ የሚሠራበት ስፍራ ከመላው የእስራኤል ምድር አንድም ከተማ፥ እንዲሁም ሕዝቤን እስራኤልን የሚመራ ማንንም ሰው አልመረጥኩም ነበር፤

6 አሁን ግን ስሜ እንዲጠራበት ኢየሩሳሌምን፥ ሕዝቤን እንድትመራም አንተን ዳዊትን መርጬአለሁ።’ ”

7 ቀጥሎም ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ “አባቴ ዳዊት በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ለመሥራት አስቦ ነበር፤

8 እግዚአብሔር ግን ‘ለእኔ ቤተ መቅደስን ለመሥራት በመፈለግህ መልካም አድርገሃል፤

9 ሆኖም ለስሜ መጠሪያ እንዲሆን ቤተ መቅደስን የሚሠራልኝ ከአብራክህ የተገኘ የአንተው የራስህ ልጅ እንጂ አንተ አይደለህም’ አለው።”

10 “እነሆ እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል ፈጽሞአል፤ ስለዚህም እኔ በአባቴ እግር ተተክቼ የእስራኤል ንጉሥ ሆኜአለሁ፤ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ሠርቼአለሁ፤

11 እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የገባው ቃል ኪዳን ያለበትን ታቦትም በቤተ መቅደሱ ውስጥ አኑሬአለሁ።”


ሰሎሞን ወደ እግዚአብሔር ያቀረበው ጸሎት
( 1ነገ. 8፥22-53 )

12-13 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን ሕዝቡ ባለበት በመሠዊያው ፊት ለፊት፥ በአደባባዩ መካከል በሚገኘው መድረክ ላይ ወጥቶ ቆመ። ስፋቱና ርዝመቱ ሁለት ሜትር ከኻያ ሴንቲ ሜትር፥ ቁመቱ አንድ ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር የሆነ መድረክ ከነሐስ አሠርቶ በአደባባዩ መካከል ተክሎት ነበር፤ እርሱም ሕዝቡ ሁሉ ሊያዩት በሚችሉበት በዚህ መድረክ ላይ በመንበርከክ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘርግቶ እንዲህ ሲል ጸለየ።

14 “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! በሰማይም ሆነ በምድር ሁሉ እንደ አንተ ያለ አምላክ ከቶ የለም፤ አንተ ከሕዝብህ ጋር የገባኸውን ቃል ኪዳን ትጠብቃለህ፤ በፍጹም ልባቸው በመንገድህ ለሚሄዱ ዘለዓለማዊ ፍቅርህን ትገልጥላቸዋለህ።

15 ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን የተስፋ ቃል አጽንተሃል፤ የተናገርከው እያንዳንዱ የተስፋ ቃልም እነሆ ዛሬ ተፈጽሞአል፤

16 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ለአባቴ ለዳዊት ‘አንተ ሕጌን በጥንቃቄ እንደ ጠበቅህ ልጆችህም ቢጠብቁ፥ ከዘርህ መካከል በእስራኤል ላይ በፊቴ የሚነግሥ ዘወትር ይኖራል’ በማለት የገባህለትን ቃል ኪዳን አሁን እንድታጸናልኝ እለምንሃለሁ፤

17 እንግዲህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ለአገልጋይህ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ሁሉ እንዲፈጸም አድርግልኝ።

18 “ነገር ግን በእውነት እግዚአብሔር በምድር ላይ ከሰዎች ጋር ይኖራልን? እነሆ፥ ሰማይ፥ ከሰማያትም በላይ ያለ ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤትማ ምንኛ ያንስ?

19 ይሁን እንጂ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፥ ወደ እኔ ወደ አገልጋይህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፤ በፊትህም የምጸልየውን ጸሎትና ጥሪ አዳምጥ።

20 ‘ስሜ ይጠራበታል’ ወዳልከው ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቀንና ሌሊት ተመልከት፤ እኔም አገልጋይህ ወደዚህ ቤተ መቅደስ የምጸልየውን ጸሎት ስማ፤

21 እኔም አገልጋይህ ሆንኩ ሕዝብህ እስራኤል ፊታችንን ወደዚህ ስፍራ መልሰን ስንጸልይ ጸሎታችንን ስማ፤ መኖሪያህ በሆነው በሰማይ ስማን፤ ይቅር በለንም።

22 “አንድ ሰው ባልንጀራውን መበደሉን የሚገልጥ ክስ ቀርቦበት በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ ወደሚገኘው መሠዊያ አምጥተውት ከበደል ንጹሕ መሆኑን በመሐላ በሚያረጋግጥበት ጊዜ፥

23 እግዚአብሔር ሆይ፥ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ለአገልጋዮችህም ፍርድን ስጥ፤ ይኸውም በደል የሠራውን ሰው በጥፋቱ መጠን እንዲቀጣ፥ ንጹሑም ነጻ እንዲወጣ አድርግ።

24 “ሕዝብህ እስራኤል ኃጢአት ሠርተው አንተን በማሳዘናቸው ምክንያት ድል ሲሆኑ ተጸጽተው ወደ አንተ በመመለስ ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢመጡና የአንተን ይቅርታ ለማግኘት ራሳቸውን ዝቅ አድርገው በትሕትና ቢለምኑህ፥

25 አንተ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ የሕዝብህንም ኃጢአት ይቅር በማለት ለቀድሞ አባቶቻቸውና ለእነርሱ ወደ ሰጠሃቸው ምድር መልሰህ አግባቸው።

26 “ሕዝብህ በደል ሠርተው አንተን በማሳዘናቸው ምክንያት ዝናብ እንዳይዘንብላቸው በምታደርግበት ጊዜ በፈጸሙት በደል በመጸጸት ፊታቸውን ወደዚህ ቤተ መቅደስ መልሰው በትሕትና ቢለምኑህ፥

27 እግዚአብሔር ሆይ፥ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ አገልጋዮችህ የሆኑትን የእስራኤል ሕዝብ ኃጢአት ይቅር በል፤ ቅን የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ አስተምራቸው፤ እግዚአብሔር ሆይ ለዘለቄታው ርስታቸው ይሆን ዘንድ ለሕዝብህ በሰጠሃቸው በዚህች ምድር ላይ ዝናብ እንዲዘንብ አድርግ።

28 “በምድሪቱ ላይ ራብ ወይም ቸነፈር በሚመጣበት ጊዜ፥ እንዲሁም የእህል ሰብል በሚያቃጥል ነፋስና በአንበጣ መንጋ በሚወድምበት ጊዜ፥ ወይም ጠላቶቻቸው በሕዝብህ ላይ ከበባ በሚያደርጉበት ጊዜ፥ ወይም በሕዝብህ ላይ ልዩ ልዩ በሽታና ደዌ በሚደርስባቸው ጊዜ፥

29 በሕዝብህ በእስራኤል መካከል ልብን የሚሰብር መሪር ሐዘን ደርሶባቸው እጃቸውን ወደዚህ ቤተ መቅደስ በመዘርጋት በሚጸልዩበት ጊዜ፥

30 ጸሎታቸውን ስማ፤ በምትኖርበት በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን በመስማት በደላቸውን ይቅር በላቸው፤ በሰው ልብና አእምሮ ያለውን ሐሳብ ሁሉ መርምረህ የምታውቅ አንተ ብቻ ነህ፤ ስለዚህ ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን የሚገባውን ዋጋ ስጠው።

31 በዚህም ዐይነት ሕዝብህ ለቀድሞ አባቶቻችን ርስት አድርገህ በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ለአንተ ታዛዦች ሆነው እንዲያከብሩህ አድርግ።

32 “በሩቅ አገር የሚኖር የውጪ አገር ሰው የስምህን ገናናነትና ለሕዝብህ ያደረግኸውን ድንቅ ነገር ሁሉ ሰምቶ፥ በዚህ ቤተ መቅደስ ሊያመልክህና ሊጸልይ ቢመጣ፥

33 አንተ ጸሎቱን ስማ፤ ሕዝብህ እስራኤል እንደሚያደርገው በመላው ዓለም የሚኖሩ ሕዝቦች አንተን በማወቅ ታዛዦች እንዲሆኑልህ፥ በምትኖርበት በሰማይ ሆነህ የዚህን ሰው ጸሎት ስማ፤ እንድታደርግለት የሚለምንህን ሁሉ ፈጽምለት፤ ይህም በሚሆንበት ጊዜ ይህ እኔ የሠራሁት ቤተ መቅደስ የአንተ ስም የሚጠራበት ስፍራ መሆኑን ያውቃሉ።

34 “ጠላቶቻቸውን ለመውጋት እንዲዘምቱ ሕዝብህን በምታዝበት ጊዜ በየትኛውም ስፍራ ሆነው ወደዚህች ወደ መረጥኻት ከተማና እኔ ለአንተ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው በሚጸልዩበት ጊዜ፥

35 ጸሎታቸውን ስማ፤ በሰማይ ሆነህ ልመናቸውን በመስማት ዓላማቸውን ደግፍ።

36 “መቼም በደል የማይሠራ ሰው የለምና ሕዝብህ እስራኤላውያን ኃጢአት በመሥራት አንተን ቢያሳዝኑህ፥ አንተም ተቈጥተህ ጠላቶቻቸው ድል እንዲነሡአቸውና ወደ ሌላ አገር ማርከው እንዲወስዱአቸው በምትፈቅድበት ጊዜ፥ ያ አገር ሩቅ ቢሆንም እንኳ፥

37 ምርኮኞች ሆነው በሚኖሩበት በዚያች አገር ሳሉ ‘ኃጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ዐምፀናልም’ ብለው በመናዘዝ ተጸጽተው ንስሓ ቢገቡ እግዚአብሔር ሆይ፥ ጸሎታቸውን ስማ፤

38 ማርከው በወሰዱአቸው በጠላቶቻቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸው በእውነትና በቅን መንፈስ ተጸጽተው ንስሓ በመግባት አንተ ለቀድሞ አባቶቻችን ወደ ሰጠሃቸው ወደዚህች ምድር፥ አንተም ወደ መረጥኻት ወደዚህች ከተማና እኔ ለስምህ ወደሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ቢጸልዩ፥

39 ጸሎታቸውን ስማ፤ በመኖሪያህ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን በመስማትም ምሕረት አድርግላቸው፤ የሕዝብህን ኃጢአት ሁሉ ይቅር በል።

40 “አምላኬ ሆይ፥ በዚህ ስፍራ ወደሚቀርበው ጸሎት ዐይኖችህ የተገለጡ ጆሮዎችህም አጣርተው የሚያደምጡ እንዲሆኑ እለምንሃለሁ።

41 እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ አሁን ተነሥተህ ከኀያሉ ታቦትህ ጋር ወደ ማረፊያ ቦታህ ና፤ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ ካህናትህ ደኅንነትን ይልበሱ፤ ታማኞችህም በበረከትህ ይደሰቱ፤

42 እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ የቀባኸውን ንጉሥ አትተወው፤ ለአገልጋይህ ለዳዊት ያደረግህለትን ፍቅር አስታውስ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告