2 ዜና መዋዕል 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ንጉሥ ሰሎሞን የቤተ መቅደሱን ሥራ ሁሉ ከፈጸመ በኋላ አባቱ ዳዊት ለእግዚአብሔር የተለዩ ያደረጋቸውን ብርና ወርቅ እንዲሁም ሌሎችን ዕቃዎች ሁሉ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሚገኘው የዕቃ ግምጃ ቤት አኖራቸው። የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ቤተ መቅደስ መግባቱ ( 1ነገ. 8፥1-9 ) 2 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት የዳዊት ከተማ ከሆነችው ከጽዮን ወደ ቤተ መቅደሱ ያመጡ ዘንድ የእስራኤል ሽማግሌዎች፥ የነገድና የቤተሰብ አለቆች ሁሉ በኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ ትእዛዝ ሰጠ። 3 በሰባተኛው ወር በሚከበረው በዳስ በዓል ጊዜ ሁሉም መጥተው በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤ 4-5 መሪዎቹ ሁሉ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ ሌዋውያን የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው፥ ወደ ቤተ መቅደሱ አመጡት፤ እንዲሁም ካህናቱና ሌዋውያኑ እግዚአብሔር የሚመለክበትን ድንኳንና በውስጡ የነበሩትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ ወደ ቤተ መቅደሱ አመጡ። 6 ንጉሥ ሰሎሞንና ሕዝቡ ሁሉ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት ተሰበሰቡ፤ ከዚህም በኋላ ከብዛታቸው የተነሣ ሊቈጠሩ የማይችሉ እጅግ ብዙ በጎችንና የቀንድ ከብቶችን መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። 7 ካህናቱም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ቤተ መቅደሱ አግብተው በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ከኪሩቤል ክንፎች በታች በሚገኘው ስፍራ አኖሩት። 8 የተዘረጉት የኪሩቤል ክንፎች የቃል ኪዳኑን ታቦትና የታቦቱን መሎጊያዎች ሸፍነዋቸው ነበር። 9 መሎጊያዎቹ እጅግ ረጃጅሞች ስለ ነበሩ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት የቆመ ማንኛውም ሰው ሊያያቸው ይችላል፤ በሌላ አቅጣጫ የቆመ ግን ፈጽሞ ሊያያቸው አይችልም ነበር፤ እነዚህ መሎጊያዎች እስከ ዛሬ ድረስ በዚያው ይገኛሉ፤ 10 እስራኤላውያን ከግብጽ እንደ ወጡ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በገባ ጊዜ ሙሴ በሲና ተራራ በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ ጽላቶች በቀር በታቦቱ ውስጥ ሌላ ነገር አልነበረም። የእግዚአብሔር ክብር መገለጥ 11 እዚያ የነበሩት ካህናት ሁሉ የአገልግሎት ምድባቸውን ሳይመለከቱ በአንድነት ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ሰጥተው ነበር፤ 12 መዘምራን የሆኑ ሌዋውያን ሁሉ፥ አሳፍ፥ ሄማንና ይዱታን እንዲሁም ወንዶች ልጆቻቸውና ዘመዶቻቸው ሁሉ ጥሩ የበፍታ ልብስ ለብሰው ነበር፤ ሌዋውያኑ ጸናጽልና መሰንቆ በመያዝ በስተ ምሥራቅ በኩል ከመሠዊያው አጠገብ ቆመው ነበር፤ 13-14 ከእነርሱም ጋር እምቢልታ የሚነፉ አንድ መቶ ኻያ ካህናት ነበሩ፤ እነዚህ መዘምራን ሁሉ በመለከት፥ በጸናጽል፥ በበገናና በሌሎችም የሙዚቃ መሣሪያዎች እየታጀቡ፦ “ቸር ስለ ሆነ፥ ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ እግዚአብሔርን አመስግኑ” በማለት በአንድ ድምፅ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር። በዚህ ጊዜ በድንገት የእግዚአብሔርን ክብር የሚገልጥ አንጸባራቂ ብርሃን የሞላበት ደመና የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ስለ ሞላው ካህናቱ የአምልኮ አገልግሎታቸውን ሊያከናውኑ አልቻሉም። |