2 ዜና መዋዕል 36 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየይሁዳ ንጉሥ ኢዮአሐዝ ( 2ነገ. 23፥30-35 ) 1 የይሁዳ ሕዝብ የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአካዝን መርጠው በአባቱ እግር ተተክቶ በኢየሩሳሌም እንዲነግሥ አደረጉት፤ 2 ኢዮአሐዝ በይሁዳ ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ኻያ ሦስት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሦስት ወር ገዛ። 3 የግብጽ ንጉሥ ኒካዑ ኢዮአሐዝን እስረኛ አድርጎ ወሰደው፤ የይሁዳንም ሕዝብ ሦስት ሺህ አራት መቶ ኪሎ የሚመዝን ብርና ሠላሳ አራት ኪሎ የሚመዝን ወርቅ እንዲገብርለት አደረገ። 4 ኒካዑ የኢዮአሐዝን ወንድም ኤልያቄምን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠው፤ ስሙንም በመለወጥ ኢዮአቄም ብሎ ጠራው፤ ኢዮአሐዝን ግን እስረኛ አድርጎ ወደ ግብጽ ወሰደው። የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም ( 2ነገ. 23፥36—24፥7 ) 5 ኢዮአቄም በይሁዳ ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ኻያ አምስት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ፤ እርሱም ኃጢአት በመሥራቱ አምላኩን እግዚአብሔርን አሳዘነ። 6 የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር ይሁዳን ወረረ፤ ኢዮአቄምንም ማርኮ ከነሐስ በተሠራ ሰንሰለት በማሰር፥ ወደ ባቢሎን ወሰደው። 7 ናቡከደነፆር የቤተ መቅደሱን ሀብት ዘርፎ በመውሰድ፥ በባቢሎን በሚገኘው ቤተ መንግሥቱ ውስጥ አኖረው። 8 ንጉሥ ኢዮአቄም ያደረገው ሁሉ፥ አጸያፊ የሆነው ልማዱና የፈጸመው ክፉ ነገር ጭምር፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጻሕፍት ተመዝግቦ ይገኛል፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢኮንያን ነገሠ። የይሁዳ ንጉሥ ኢኮንያን ( 2ነገ. 24፥8-17 ) 9 ኢኮንያን በይሁዳ ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሦስት ወር ከዐሥር ቀን ገዛ፤ እርሱም ኃጢአት በመሥራቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ። 10 የጸደይ ወራት በደረሰ ጊዜ ንጉሥ ናቡከደነፆር ኢኮንያንን እስረኛ አድርጎ ወደ ባቢሎን ወሰደው፤ የቤተ መቅደሱንም ሀብት ዘርፎ ወሰደ፤ ከዚህ በኋላ የኢኮንያን አጎት የሆነውን ሴዴቅያስን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠ። የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ( 2ነገ. 24፥18-20 ፤ ኤር. 52፥1-3 ) 11 ሴዴቅያስ በይሁዳ ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ኻያ አንድ ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ፤ 12 እርሱም ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ የእግዚአብሔርን ቃል የተናገረውን ነቢዩን ኤርምያስን በትሕትና አላዳመጠውም። የኢየሩሳሌም መውደቅ ( 2ነገ. 25፥1-21 ፤ ኤር. 52፥3-11 ) 13 ሴዴቅያስ፥ ታማኝ እንዲሆንለት በእግዚአብሔር ስም ባስማለው በንጉሥ ናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ፤ ተጸጽቶ ንስሓ በመግባት ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ በእልኸኛነት እምቢ አለ። 14 በተጨማሪም የካህናት መሪዎችና ሕዝቡ ጣዖቶችን በማምለክ በዙሪያቸው የሚገኙትን ሕዝቦች መጥፎ ምሳሌነት ተከተሉ፤ እግዚአብሔር ራሱ የቀደሰውን ቤተ መቅደስም አረከሱ፤ 15 የቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለቤተ መቅደሱ ስላዘነ ያስጠነቅቁአቸው ዘንድ ነቢያትን መላልሶ መላክን ቀጠለ። 16 እስራኤላውያን ግን በእግዚአብሔር መልእክተኞች ላይ ተሳለቁ፤ በነቢያቱም በማፌዝ፥ የእግዚአብሔርን ቃል አቃለሉ፤ ከዚህም የተነሣ፥ የእግዚአብሔር ቊጣ በሕዝቡ ላይ ወረደ፤ ከታላቅ ቊጣውም ለማምለጥ አልቻሉም። 17 ስለዚህ የባቢሎን ንጉሥ በእነርሱ ላይ አደጋ እንዲጥል እግዚአብሔር ፈቀደ፤ ንጉሡም በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበሩትን እንኳ ሳይቀር፥ በይሁዳ የሚገኙትን ወጣቶች ወንዶችን ሁሉ በሰይፍ ፈጀ፤ እግዚአብሔር ለናቡከደነፆር አሳልፎ ስለ ሰጣቸውም ወጣት ወይም ሽማግሌ፥ ወንድ ወይም ሴት ማንንም ሳይለይ፥ ሁሉንም ያለ ምሕረት አጠፋቸው። 18 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የቤተ መቅደሱን፥ የንጉሡንና የእርሱ ባለሟሎች የሆኑትን ባለሥልጣኖች ግምጃ ቤት በሙሉ ዘርፎ ወደ ባቢሎን ወሰደ፤ 19 ቤተ መቅደሱንና የኢየሩሳሌምን ከተማ ከነቤተ መንግሥት ሕንጻዎችና ከነሀብትዋ አቃጠለ፤ የከተማይቱንም የቅጽር ግንብ አፈራረሰ፤ 20 በሰይፍ ከመገደል የተረፉትንም ሁሉ ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፤ እነርሱም የፋርስ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት እስከ ተነሣበት ጊዜ ድረስ፥ በዚያው በባቢሎን ባሪያዎች ሆነው፥ ንጉሥ ናቡከደነፆርንና የእርሱን ዘሮች ያገለግሉ ነበር። 21 በዚህ ዐይነት አስቀድሞ እግዚአብሔር በነቢዩ ኤርምያስ አማካይነት፥ “ሕዝቡ ሰንበቶችን ባላከበሩበት ልክ ምድሪቱ ለሰባ ዓመት ባድማ ሆና ስለምትቀር፥ የሰንበት ዕረፍት ታገኛለች” ሲል የተናገረው የትንቢት ቃል ተፈጸመ። የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ቂሮስ አይሁድን ከግዞት እንዲመለሱ ማዘዙ ( ዕዝ. 1፥1-4 ) 22 እግዚአብሔር በነቢዩ ኤርምያስ አማካይነት አስቀድሞ የተናገረው የትንቢት ቃል፥ ቂሮስ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት በሆነ በመጀመሪያው ዓመት ተፈጸመ፤ ከዚህ የሚከተለውን ዐዋጅ እንዲያወጣና በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ሁሉ በጽሑፍ በማስተላለፍ ከፍ ባለ ድምፅ ለሕዝቡ በንባብ እንዲገለጥ ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር ቂሮስን አነሣሣው። 23 የዐዋጁም ቃል እንዲህ የሚል ነው፤ “ይህ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት የቂሮስ ትእዛዝ ነው፤ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ ላይ ገዢ አድርጎኛል፤ በይሁዳ ውስጥ በምትገኘው በኢየሩሳሌም ከተማ ለእርሱ ክብር ቤተ መቅደስን እሠራ ዘንድ ኀላፊነት ሰጥቶኛል፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ሰዎች የሆናችሁ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሂዱ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሁን።” |