Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 34 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የይሁዳ ንጉሥ ኢዮስያስ
( 2ነገ. 22፥1-2 )

1 ኢዮስያስ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ስምንት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ።

2 ኢዮስያስ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ፤ የቀድሞ አባቱን የንጉሥ ዳዊትን መልካም ምሳሌነት ከመከተል ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም።


ኢዮስያስ የአሕዛብ የማምለኪያ ስፍራዎችን ማስወገዱ

3 ኢዮስያስ በነገሠ በስምንተኛ ዓመቱ፥ ገና ወጣት ሳለ የቀድሞ አባቱን የንጉሥ ዳዊትን አምላክ እግዚአብሔርን ማምለክ ጀመረ፤ ከአራት ዓመት በኋላም የአሕዛብ የማምለኪያ ስፍራዎችን፥ አሼራ ተብላ የምትጠራ የሴት አምላክ ምስሎችንና ሌሎችን ጣዖቶች ሁሉ ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ማስወገድ ጀመረ፤

4 በእርሱም ትእዛዝ የእርሱ ሰዎች ባዓል ተብሎ የሚጠራው ጣዖት ይመለክባቸው የነበሩትን መሠዊያዎችንና በእነርሱም አጠገብ የነበሩትን ዕጣን የሚታጠንባቸውን መሠዊያዎች ሰባበሩ፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስሎችንና ሌሎችንም ጣዖቶች ሁሉ ትቢያ እስኪሆኑ ድረስ አደቀቁአቸው፤ ትቢያውንም ወስደው ለእነዚያ ጣዖቶች መሥዋዕት ያቀርቡ በነበሩ ሰዎች መቃብር ላይ በተኑት፤

5 ኢዮስያስ የአሕዛብን ካህናት ዐፅም ሁሉ እነርሱ ራሳቸው ይሰግዱላቸው በነበሩት መሠዊያዎች ላይ አቃጠላቸው፤ ይህን ሁሉ በማድረጉም ይሁዳና ኢየሩሳሌም በሥርዓት እንደገና እንዲነጹ አደረገ፤

6 እስከ ሰሜን ንፍታሌም ድረስ ባሉ በምናሴ፥ በኤፍሬምና በስምዖን ግዛቶች በሚገኙ ከተሞች እንዲሁም በተደመሰሱት አካባቢዎቻቸው ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸመ።

7 የሰሜን የእስራኤል ግዛት የነበሩትን የጣዖቶች መሠዊያዎችንና የአሼራ ምስሎችን ሁሉ ሰባበራቸው፤ ጣዖቶቹንም ትቢያ እስኪሆኑ አደቀቃቸው፤ ዕጣን የሚታጠንባቸውንም የጣዖት መሠዊያዎች አንከታክቶ ጣለ፤ ከዚህም በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።


የእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ መገኘት
( 2ነገ. 22፥3-20 )

8 ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የአሕዛብን አምልኮ በማጥፋት ምድሪቱንና ቤተ መቅደሱን ካነጻ በኋላ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ያድሱ ዘንድ የአጻልያን ልጅ ሳፋንን፥ የኢየሩሳሌም አስተዳዳሪ የሆነውን ማዕሤያንና የኢዮአሐዝን ልጅ ጸሐፊውን ዮአሕን ላከ፤

9 ዘብ ጠባቂዎች የሆኑ ሌዋውያን በቤተ መቅደስ ውስጥ የሰበሰቡት ገንዘብ ሁሉ፥ ለሊቀ ካህናቱ ለሒልቂያ ተሰጠ፤ ገንዘቡም የተሰበሰበው ከኤፍሬም፥ ከምናሴና ከቀረውም የእስራኤል ሕዝብ፥ እንዲሁም ከይሁዳ፥ ከብንያምና ከኢየሩሳሌም ሕዝብ ነበር፤

10 ይህም ገንዘብ ለቤተ መቅደሱ እድሳት ኀላፊዎች ለነበሩት ለነዚያ ሦስት ሰዎች ተሰጠ፤ እነርሱም በበኩላቸው ገንዘቡን ለሠራተኞችና

11 የይሁዳ ነገሥታት እንዲፈራርሱ ያደረጉአቸውን ሕንጻዎች ማሠሪያ የሚሆን ድንጋይና እንጨት ይገዙበት ዘንድ ለአናጢዎችና ለግንበኞች ሰጡ፤

12 አናጢዎቹና ግንበኞቹም ሥራውን በታማኝነት አከናወኑ፤ የእነርሱም የበላይ ተቈጣጣሪዎች ከመራሪ ጐሣ ያሐትና አብድዩ፥ ከቀዓት ጐሣ ዘካርያስና መሹላም ተብለው የሚጠሩት አራት ሌዋውያን ነበሩ፤ (ሌዋውያን ሁሉ በዜማ መሣሪያ የመዘመር ከፍ ያለ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ነበሩ፤)

13 ሌሎቹ ሌዋውያን ዕቃዎችን ለሚያጓጒዙና በልዩ ልዩ ሥራ ለተመደቡ ሠራተኞች የበላይ ኀላፊዎችና ተቈጣጣሪዎች ሲሆኑ፥ የቀሩት ሌዋውያን ደግሞ ጸሐፊዎች ወይም ዘብ ጠባቂዎች ነበሩ።

14 የቀረበውን ገንዘብ ከግምጃ ቤት ያወጡ በነበሩበት ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ሒልቂያ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ፤

15 እርሱም ጸሐፊውን ሳፋንን “የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ በዚህ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አግኝቻለሁ” በማለት መጽሐፉን ሰጠው፤

16 ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ ወስዶ ንጉሡን “እነሆ፥ አንተ ያዘዝከንን ሁሉ አድርገናል፤

17 በቤተ መቅደሱ ተቀምጦ የነበረውን ገንዘብ ወስደን ለሠራተኞችና እነርሱን ለሚቈጣጠሩ ሰዎች አስረክበናል” አለው፤

18 ንግግሩንም በመቀጠል “ሒልቂያ የሰጠኝ መጽሐፍ እነሆ፥ በእጄ ይገኛል” አለው፤ መጽሐፉንም ለንጉሡ አነበበለት።

19 ንጉሡም የሕጉ ቃላት ሲነበብለት በሰማ ጊዜ፥ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤

20 ከዚህም በኋላ ንጉሡ ለሒልቂያ፥ ለሳፋን ልጅ ለአሒቃም፥ ለሚክያስ ልጅ ለዐብዶን፥ ለቤተ መንግሥቱ ጸሐፊ ለሳፋንና የንጉሡ የቅርብ አገልጋይ ለሆነው ለዓሳያ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጠ፥

21 “ሄዳችሁ ስለ እኔና እንዲሁም በእስራኤልና በይሁዳ ስለ ቀረው ሕዝብ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ በዚህ መጽሐፍ ስላለውም ትምህርት አረጋግጡ፤ የቀድሞ አባቶቻችን ለእግዚአብሔር ቃል ባለመታዘዛቸውና ይህ መጽሐፍ አድርጉ የሚላቸውን ሁሉ ባለመፈጸማቸው፥ እግዚአብሔር ቊጣውን በእኛ ላይ አውርዶአል።”

22 ሒልቂያና የቀሩት ሰዎች ንጉሡ ባዘዛቸው መሠረት በኢየሩሳሌም ከተማ አዲሱ ክፍል ነዋሪ ወደሆነችው ሑልዳ ተብላ ወደምትጠራ ነቢይት ሄደው ስለ ተላኩበት ጉዳይ ጠየቁአት፤ የዚህች ነቢይት ባለቤት ሻሉም ተብሎ የሚጠራ የቲቅዋ ልጅ የሐርሐስ የልጅ ልጅ ሲሆን፥ እርሱም የቤተ መቅደሱ አልባሳት ኀላፊ ነበር፤ ሰዎቹም ለነቢይቱ ሁኔታውን በዝርዝር ገለጡላት፤

23 እርስዋም “ወደ እኔ ወደ ላካችሁ ሰው ተመልሳችሁ በመሄድ፥ ከዚህ የሚከተለውን የእግዚአብሔር ቃል ስጡት አለቻቸው።”

24 ቃሉም እንዲህ የሚል ነበር፦ “እኔ እግዚአብሔር ለይሁዳ ንጉሥ በተነበበለት መጽሐፍ ውስጥ በሚገኙት እርግማኖች ኢየሩሳሌምንና ሕዝብዋን ሁሉ እቀጣለሁ፤

25 እነርሱ እኔን ትተው ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት አቅርበዋል፤ ይህም ያደረጉት በደል ቊጣዬን አነሣሥቶአል፤ በኢየሩሳሌም ላይ የተነሣሣው ቊጣዬም ይፈጸማል እንጂ አይበርድም፤

26 ስለ ንጉሡ የሆነ እንደ ሆነ፥ እኔ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፤ ‘አንተ በዚያ መጽሐፍ የተነገረውን ቃል ሰምተሃል፤

27 እኔ ኢየሩሳሌምንና ሕዝብዋን እንዴት እንደምቀጣ በሰማህ ጊዜ፥ ራስህን አዋርደኽ በሐዘን ልብስህን በመቅደድና በማልቀስ ንስሓ ገብተሃል፤ ስለዚህ ጸሎትህን ሰምቼአለሁ።

28 አንተ በሕይወት እስካለህ ድረስ በኢየሩሳሌም ላይ ቅጣት አላመጣም፤ አንተ በሰላም እንድትሞት አደርጋለሁ።’ ” ሰዎቹም ይህን መልእክት ይዘው ወደ ንጉሥ ኢዮስያስ ተመለሱ።


ኢዮስያስ ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ ቃል ኪዳን መግባቱ
( 2ነገ. 23፥1-20 )

29 ንጉሥ ኢዮስያስ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን የታወቁ ሽማግሌዎች ሁሉ በማስጠራት በአንድነት እንዲሰበሰቡ አደረገ፤

30 እነርሱም ከንጉሡ ጋር ካህናትንና ሌዋውያንን፥ ሌሎችንም ሰዎች ማለትም ባለጸጎችንም ድኾችንም ሁሉ አስከትለው ወደ ቤተ መቅደስ ሄዱ፤ ንጉሡም በዚያ ጠፍቶ በነበረውና በቤተ መቅደስ በተገኘው የቃል ኪዳን መጽሐፍ የሰፈረውን ቃል በሙሉ ለሕዝቡ አነበበ፤

31 ንጉሡ በዐምዱ አጠገብ ቆሞ በሙሉ ልቡና ሐሳቡ እግዚአብሔርን ለመከተልና ትእዛዞቹን፥ ደንቦቹንና ድንጋጌዎቹን ለመጠበቅ በእርሱ ፊት ቃል ኪዳኑን አደሰ፤ ስለዚህም በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ቃል ኪዳን አረጋገጠ።

32 ከዚህ በኋላ መላው የብንያም ሕዝብና በኢየሩሳሌም የተገኙ ሌሎች ሰዎች ሁሉ ቃል ኪዳኑን ይጠብቁ ዘንድ ቃል እንዲገቡ አደረገ፤ በዚህም መሠረት የኢየሩሳሌም ሕዝብ ከቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር የገቡት ቃል ኪዳን የሚጠይቀውን ግዴታ ሁሉ ፈጸሙ፤

33 ንጉሥ ኢዮስያስ በእስራኤል ግዛት ውስጥ የነበሩትን አጸያፊ ጣዖቶች ሁሉ አስወግዶ፥ ሕዝቡ አምላኩን እግዚአብሔርን እንዲያገለግል አደረገ፤ በዘመነ መንግሥቱም ሁሉ ሕዝቡ ከቀድሞ አባቶቹ አምላክ ከእግዚአብሔር ፈቀቅ አላሉም።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告