2 ዜና መዋዕል 32 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምአሦራውያን በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል መዛታቸው ( 2ነገ. 18፥13-37 ፤ 19፥14-19 ፤ 35-37 ፤ ኢሳ. 36፥1-22 ፤ 37፥8-38 ) 1 ንጉሥ ሕዝቅያስ እግዚአብሔርን በታማኝነት በማገልገል ብዙ ነገሮችን ካከናወነ በኋላ፥ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ሰናክሬም ይሁዳን ወረረ፤ እንደሚያሸንፍ ተማምኖ የተመሸጉትን ከተሞች ከበበ 2 ሰናክሬም በኢየሩሳሌምም ላይ አደጋ ለመጣል ያቀደ መሆኑን ንጉሥ ሕዝቅያስ በተገነዘበ ጊዜ፥ 3-4 እርሱ ከባለሟሎቹ ባለሥልጣኖች ጋር ከከተማይቱ ውጪ ያሉትን ምንጮችና የውሃ መተላለፊያ ቦይ ለመድፈን ተማከረ፤ እነርሱም ረዱት፤ ይህንንም ያደረጉት አሦራውያን ወደ ኢየሩሳሌም ሲቃረቡ ምንም ውሃ እንዳያገኙ ለማድረግ ነው፤ ስለዚህ ባለሥልጣኖቹ ብዙ ሰዎችን ወደዚያ በመውሰድ ከምንጮቹ ውሃ እንዳይፈስስ ለማድረግ፥ እነዚያን ምንጮች ሁሉ ደፈኑአቸው። 5 ንጉሥ ሕዝቅያስም ቅጽሮችን ጠግኖ በላያቸው ላይ የመቈጣጣሪያ ግንቦችን በመሥራትና ከውጪም በኩል ቅጽሮችን በመገንባት የከተማይቱን መከላከያዎች አጠናከረ፤ በተጨማሪም ከጥንታዊት ኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ በኩል በሚገኘው በተደለደለው ቦታ ላይ የተሠሩትን መከላከያዎች አደሰ፤ ብዙ ጦርና ጋሻም ሠራ። 6 የከተማይቱ ነዋሪዎች የሆኑ ወንዶች ሁሉ፥ በጦር መኰንኖች ሥልጣን ሥር እንዲሆኑ አድርጎ፥ በከተማይቱ ቅጽር በር አጠገብ በሚገኘው ገላጣ አደባባይ ላይ ሰበሰባቸው፤ እንዲህም በማለት አበረታታቸው፤ 7 “ብርቱዎች ልበ ሙሉዎች ሁኑ፤ የአሦርን ንጉሠ ነገሥትንም ሆነ በእርሱ የሚመራውን ሠራዊት አትፍሩ፤ ከእርሱ ጋር ካለው ኀይል ይልቅ ከእኛ ጋር ያለው ኀይል ይበልጣል፤ 8 ከእርሱ ጋር ያለው ኀይል ሰብአዊ ኀይል ነው፤ ከእኛ ጋር ሆኖ የሚረዳንና የሚዋጋልን ግን አምላካችን እግዚአብሔር ነው፤” ሕዝቡም ንጉሡ በተናገረው በዚህ ቃል ተበረታታ። 9 ከዚህ በኋላ ትንሽ ቈይቶ፥ ንጉሥ ሰናክሬምና ሠራዊቱ ገና በላኪሽ ሳሉ ለሕዝቅያስና ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም ለነበሩት ለይሁዳ ሕዝብ እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፤ 10 “እኔ የአሦር ንጉሠ ነገሥት የሆንኩ ሰናክሬም፥ በእኔ ሠራዊት በተከበበችው በኢየሩሳሌም ለመቈየት ያሰባችሁት በማን ተማምናችሁ እንደ ሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ፤ 11 ሕዝቅያስ ‘አምላካችን እግዚአብሔር ከአሦራውያን እጅ ያድነናል’ ይላችኋል፤ ነገር ግን እርሱ እንደዚህ ባለ አነጋገር እያታለለ፥ በራብና በውሃ ጥም እንድታልቁ ሊያደርጋችሁ ነው፤ 12 ከዚህ ቀደም የተቀደሱትን የእግዚአብሔርን ማምለኪያ ስፍራዎችና መሠዊያዎችን ያፈራረሰ፥ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብም በአንድ መሠዊያ ላይ ብቻ ዕጣን እያጠነ እንዲሰግድ ያደረገ ሕዝቅያስ ነው፤ 13 የቀድሞ አባቶቼና እኔ በሌሎች ሕዝቦች ላይ ምን እንዳደረግን አታውቁምን? ከሌሎች ሕዝቦች አማልእክት መካከል ሕዝቡን ከአሦር ንጉሠ ነገሥት ያዳነ አምላክ አንድ እንኳ ይገኛልን? 14 አባቶቼ ካወደሙአቸው ከእነዚህ አገሮች አማልክት መካከል አንዱ እንኳ አገሩን ያዳነበት ጊዜ አለን? ታዲያ፥ የእናንተ አምላክ ከእጄ እንዴት ሊያድናችሁ ይችላል? 15 ስለዚህ ሕዝቅያስ በዚህ መንገድ አያታላችሁ! ወደ ስሕተትም አይምራችሁ! ከቶ እርሱን አትመኑ! የማንም ሕዝብ አምላክ የራሱን ሕዝብ ከማንኛውም የአሦር ንጉሠ ነገሥት እጅ ሊያድን የቻለበት ጊዜ የለም፤ ይህም የእናንተ አምላክ እናንተን ሊያድን እንደማይችል የተረጋገጠ ነው።” 16 የአሦር ባለሥልጣኖችም በእግዚአብሔርና በአገልጋዩ በሕዝቅያስ ላይ ከዚህ የከፋ ነገር ተናገሩ፤ 17 የአሦር ንጉሠ ነገሥት የጻፈው ደብዳቤ “የሌሎች ሕዝቦች አማልክት ሕዝቦቻቸውን ከእኔ እጅ አላዳኑም፤ የሕዝቅያስም አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ሊያድናቸው ከቶ አይችልም” በማለት የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚዘልፍ ነበር፤ 18 የአሦር ባለሥልጣኖች ይህን የዛቻ ቃል በዕብራይስጥ ቋንቋ በቅጽሮቹ ላይ ለነበሩት ለኢየሩሳሌም ሰዎች ከፍ ባለ ድምፅ ያሰሙ ነበር፤ ይህንንም ያደረጉበት ምክንያት ሕዝቡን አስፈራርተው ተስፋ በማስቈረጥ ከተማይቱን በቀላል ለመያዝ ዐቅደው ነው። 19 በሰው እጅ በተሠሩ በሌሎች ሕዝቦች የጣዖት አማልክት ላይ በድፍረት በተናገሩት ዐይነት በኢየሩሳሌም አምላክ ላይም ይናገሩ ነበር። 20 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ፤ እንዲረዳቸውም ወደ እርሱ አጥብቀው ጮኹ፤ 21 እግዚአብሔርም መልአክን ልኮ የአሦርን ወታደሮችና የጦር መኰንኖች እንዲገደሉ አደረገ፤ ስለዚህም የአሦር ንጉሠ ነገሥት ተዋርዶ ወደ አገሩ ተመለሰ፤ አንድ ቀን በአምላኩ መስገጃ ስፍራ በነበረበት ወቅት የገዛ ልጆቹ በሰይፍ ገደሉት። 22 በዚህ ሁኔታ እግዚአብሔር ንጉሥ ሕዝቅያስንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ከአሦር ንጉሠ ነገሥት ከሰናክሬብና ከሌሎቹም ጠላቶቻቸው እጅ በመታደግ አዳናቸው፤ ጐረቤቶቻቸው ከሆኑትም ሕዝቦች ሁሉ ጋር በሰላም እንዲኖሩ ፈቀደ። 23 ብዙ ሰዎች ለእግዚአብሔር መባን፥ ለንጉሥ ሕዝቅያስ ደግሞ ገጸ በረከትን ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ሕዝቦች ሁሉ ሕዝቅያስን ከፍ ባለ አክብሮት ተመለከቱት። ሕዝቅያስ እግዚአብሔርን ባለማመስገኑ መወቀሱ ( 2ነገ. 20፥1-3 ፤ 12-19 ፤ ኢሳ. 38፥1-3 ፤ 39፥1-8 ) 24 በዚያኑ ጊዜ ንጉሥ ሕዝቅያስ ታሞ ሊሞት ተቃርቦ ነበር፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ እግዚአብሔርም እንደሚያድነው የሚያረጋግጥ ምልክት አሳየው። 25 ሕዝቅያስ ግን ልቡ በትዕቢት ተሞልቶ ስለ ነበር፥ እግዚአብሔር ስላደረገለት ቸርነት ሁሉ ተገቢ ምስጋና አላቀረበም፤ ከዚህም የተነሣ በእርሱ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ሕዝብ ብርቱ ሥቃይ ደረሰባቸው። 26 ይሁን እንጂ በመጨረሻ ሕዝቅያስና የኢየሩሳሌም ሕዝብ በትሕትና ራሳቸውን ስላዋረዱ ሕዝቅያስ ከዚህ ዓለም በሞት እስከ ተለየበት ጊዜ ድረስ እግዚአብሔር ሕዝቡን አልቀጣም። የሕዝቅያስ ብልጽግናና ገናናነት 27 ንጉሥ ሕዝቅያስ እጅግ በለጸገ፤ ሕዝቡም ሁሉ አከበሩት፤ ወርቁን፥ ብሩን፥ የከበረ ዕንቊውን፥ ቅመማ ቅመሙን፥ ጋሻዎቹንና ሌሎቹንም ውድ የሆኑ ዕቃዎቹን የሚያኖርባቸው ዕቃ ግምጃ ቤቶችን ሠራ፤ 28 በተጨማሪም ለእህሉ፥ ለወይን ጠጁና ለወይራ ዘይቱ ማኖሪያ የሚሆኑ የዕቃ ግምጃ ቤቶችን፥ ለቀንድ ከብቶቹ በረት፥ ለበጎቹም ጒረኖ ሠርቶ ነበር፤ 29 ከዚህም ሁሉ ሌላ እግዚአብሔር ብዙ የቀንድ ከብትና የበግ መንጋ እንዲሁም ሌላ እጅግ የበዛ ሀብት ስለ ሰጠው፥ ብዙ ከተሞችን ሠራ፤ 30 በላይ በኩል ያለውን የግዮንን ምንጭ መውጫ ገድቦ ውሃውን ወደ ምዕራብ፥ ወደ ዳዊት ከተማ፥ በቦይ እንዲወርድ ያደረገ ራሱ ሕዝቅያስ ነው፤ ይህ ሕዝቅያስ ሊሠራ ባቀደው ነገር ሁሉ የተሳካለት ሰው ነበር፤ 31 ነገር ግን የባቢሎን መልእክተኞች በአገሪቱ ስለ ተደረገው አስደናቂ ነገር ሊጠይቁት ወደ እርሱ መጥተው በነበረ ጊዜ እግዚአብሔር በሕዝቅያስ ልብ ውስጥ ያለውን ሐሳብ ለማወቅ ይፈትነው ዘንድ ተወው። የሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ ( 2ነገ. 20፥20-21 ) 32 ንጉሥ ሕዝቅያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ፥ ለእግዚአብሔርም የነበረው መንፈሳዊ ቅናት በአሞጽ ልጅ በነቢዩ ኢሳይያስ ራእይ እንዲሁም በይሁዳና በእስራኤል የታሪክ መጻሕፍት ተመዝግበው ይገኛሉ። 33 ሕዝቅያስ ሞተ፤ በላይኛው ክፍል በሚገኘውም በዳዊት ልጆች መካነ መቃብር ተቀበረ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብም ሁሉ ታላቅ የቀብር ሥነ ሥርዓት አደረጉለት፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ምናሴ ነገሠ። |