2 ዜና መዋዕል 31 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምንጉሥ ሕዝቅያስ ያደረገው መንፈሳዊ ተሐድሶ 1 ከበዓሉ ፍጻሜ በኋላ መላው የእስራኤል ሕዝብ ወደ ይሁዳ ከተሞች ሁሉ በመሄድ ከድንጋይ የተሠሩትን የጣዖት ዐምዶች ሰባበሩ፤ አሼራ ተብላ በምትጠራው ሴት አምላክ ስም የቆሙ ምስሎችንም ሰባብረው ጣሉ፤ መሠዊያዎችንና የአሕዛብ መስገጃ ስፍራዎችንም ደመሰሱ፤ እንዲሁም በቀሩት በይሁዳ፥ በብንያም፥ በኤፍሬምና በምናሴ ግዛቶች ውስጥ የነበሩትን የጣዖት መስገጃዎችንና መሠዊያዎችን ሁሉ አፈራረሱ፤ ከዚያም በኋላ ወደየመኖሪያ ስፍራዎቻቸው ተመለሱ። 2 ንጉሥ ሕዝቅያስ የካህናትንና የሌዋውያንን ሥርዓት እንደገና አቋቋመ፤ በዚህም ጉባኤ ውስጥ እያንዳንዱ ካህንና እያንዳንዱ ሌዋዊ የተለየ የሥራ ምድብ ነበረው፤ ይህም የሥራ ምድብ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕትን ማቅረብን፥ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሚከናወነው የአምልኮ ሥነ ሥርዓት መሳተፍን፥ በሌሎቹም በቤተ መቅደሱ ልዩ ልዩ ክፍሎች ምስጋናና ውዳሴ ማቅረብን የሚያጠቃልል ነበር፤ 3 ዘወትር ጠዋትና ማታ ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ በሰንበቶች፥ በወር መባቻዎችና በእግዚአብሔር ሕግ በተወሰነው በሌሎች በዓላት ለሚቀርብ መሥዋዕት ንጉሥ ሕዝቅያስ የራሱ ንብረት ከሆኑ በጎችና የቀንድ ከብቶች ይሰጥ ነበር። 4 በተጨማሪም ካህናቱና ሌዋውያኑ ጊዜአቸውን በሙሉ የእግዚአብሔር ሕግ ለሚጠይቀው አገልግሎት ማዋል ይችሉ ዘንድ ለእነርሱ መሰጠት የሚገባውን ሁሉ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንዲያመጡ ንጉሡ አዘዘ፤ 5 እስራኤላውያን ይህን የንጉሡን ትእዛዝ እንደ ሰሙ ከእህላቸውና ከወይን ጠጃቸው፥ ከወይራ ዘይታቸውና ከማራቸው ከሌላውም የእርሻቸው ፍሬ ሁሉ ምርጥ የሆነውን በኲራት በልግሥና አበረከቱ፤ ከነበራቸውም ሀብት ሁሉ ዐሥራት አውጥተው ሰጡ፤ 6 በይሁዳ ከተሞች ሰዎችም ሕዝብም ሁሉ ከቀንድ ከብቶቻቸውና ከበጎቻቸው ዐሥራት አውጥተው ሰጡ፤ እንዲሁም ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር የተለየ ያደረጉትን ስጦታ አምጥተው ከመሩት፤ 7 ስጦታዎቹንም ማምጣት የጀመሩት በሦስተኛው ወር ሲሆን፥ በተከታታይ ለአራት ወራት ስጦታቸውን እያመጡ መከመር ቀጠሉ፤ 8 ንጉሥ ሕዝቅያስና ባለሟሎቹ የሆኑት ባለሥልጣኖች መጥተው፥ እጅግ የበዛውን የስጦታ ክምር ባዩ ጊዜ፥ እግዚአብሔርንና የእርሱ ወገኖች የሆኑትን የእስራኤልን ሕዝብ አመሰገኑ፤ 9 ንጉሡ ከሕዝቡ ስለ ተበረከተው የስጦታ ክምር፥ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ጠየቀ፤ 10 የሳዶቅ ዘር የሆነው ሊቀ ካህናት ዐዛርያስም ንጉሡን፥ “ሕዝቡ ዐሥራቱን ወደ እግዚአብሔር ቤት ማምጣት ከጀመረ ወዲህ፥ እነሆ፥ በቂ ምግብ አለን፤ ብዙም ተርፎናል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለ ባረከ እነሆ፥ ይህን ሁሉ በብዛት አግኝተናል” አለው። 11 ንጉሥ ሕዝቅያስም በቤተ መቅደሱ አካባቢ የዕቃ ግምጃ ቤት እንዲዘጋጅ፥ አዞ በተዘጋጀ ጊዜ 12 ዐሥራቱንና በኲራቱን፥ የተቀደሱትንም ስጦታዎች ሁሉ በእምነት ወደዚያ አስገቡ፤ ኮናንያ ተብሎ የሚጠራው ሌዋዊ የዕቃ ግምጃ ቤቱ ኀላፊ ሆኖ ሲሾም፥ ወንድሙ ሺምዒ ደግሞ ረዳቱ ሆኖ ተሾመ፤ 13 ከእነርሱም ሥር ሆነው የሚሠሩ ይሒኤል፥ ዐዛዝያ፥ ናሐት፥ ዐሣሄል፥ ይሪሞት፥ ዮዛባድ፥ ኤሊኤል፥ ዩስማክያ፥ ማሐትና በናያ ተብለው የሚጠሩ ዐሥር ሌዋውያን ተመደቡ። እነዚህን ሁሉ የሾሙ፥ ንጉሥ ሕዝቅያስና ሊቀ ካህናቱ ዐዛርያስ ናቸው፤ 14 የቤተ መቅደሱ የምሥራቃዊ በር ዘብ ጠባቂዎች አለቃ ለነበረው ለሌዋዊው ዩምና ልጅ ለቆሬ ደግሞ፥ ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን የበጎ ፈቃድ ስጦታዎች ሁሉ የመቀበልና የማከፋፈል ኀላፊነት ተሰጠው። 15 ካህናት በሚኖሩባቸው በሌሎች ከተሞች ቆሬን በታማኝነት የሚረዱ ዔደን፥ ሚንያሚን፥ ኢያሱ፥ ሸማዕያ፥ አማርያና ሸካንያ ተብለው የሚጠሩ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም በሥራቸው ምድብ መሠረት ምግቡን ወገኖቻቸው ለሆኑ ሌዋውያን በትክክል ያከፋፍሉ ነበር። 16 በተጨማሪም በተለያዩ የየዕለት ተግባራቸው ወደ ቤተ መቅደስ ለሚገቡ ከሦስት ዓመት ዕድሜ በላይ ላላቸው ወንዶች እንደየ ኀላፊነታቸውና እንደየምድባቸው ድርሻ ድርሻቸውን ያከፋፍሉ ነበር፤ 17 የካህናት ሥራ ምድብ በጐሣ በጐሣ ሲሆን፥ ዕድሜአቸው ኻያ ወይም ከዚያ በላይ የሆነ ሌዋውያን፥ የሥራ ምድብ ግን በሚያከናውኑት የሥራ ዐይነት የሚወሰን ነበር፤ 18 እነዚህ ካህናትና ሌዋውያን ራሳቸውን የቀደሱ ታማኞች ስለ ነበሩ የሚመዘገቡት ከሚስቶቻቸው ከልጆቻቸውና በእነርሱ ሥር ከሚተዳደሩት ሰዎች ሁሉ ጋር በአንድነት ነበር፤ 19 ለአሮን ልጆች በተመደቡ ከተሞች ወይም የእነዚህ ከተሞች ይዞታ በሆኑት የግጦሽ ቦታዎች ከሚኖሩት ካህናት መካከል ለካህናት ቤተሰቦችና በሌዋውያን ጐሣ የስም ዝርዝር በያዘ መዝገብ ውስጥ ስማቸው ለሚገኝ ወንዶች ሁሉ ምግብን ለማከፋፈል ኀላፊዎች የሆኑ ሰዎች ነበሩ። 20 ንጉሥ ሕዝቅያስ በመላው የይሁዳ ግዛት መልካም የሆነውንና ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኘውን ነገር ሁሉ አደረገ፤ 21 ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት ወይም ሕጉንና ትእዛዞቹን ለመጠበቅ ያከናወነው ሥራ ሁሉ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር በፍጹም ታማኝነትና በመንፈሳዊ ቅናት ስለ ነበር ሁሉም ነገር ተሳካለት። |