2 ዜና መዋዕል 30 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምለፋሲካ በዓል አከባበር የተደረገ ዝግጅት 1-3 ራሳቸውን ያነጹ በቂ ካህናት ስላልነበሩና በኢየሩሳሌም ብዙ ሕዝብ ስላልተሰበሰበ፥ ሕዝቡ የፋሲካን በዓል እንደ ተለመደው በመጀመሪያው ወር ሊያከብር አልቻለም፤ ስለዚህ ንጉሥ ሕዝቅያስ፥ ባለሟሎቹ የሆኑት ባለሥልጣኖችና የኢየሩሳሌም ሕዝብ የፋሲካ በዓል በሁለተኛው ወር እንዲከበር ተስማምተው ወሰኑ፤ በዚህ መሠረት ንጉሡ ለመላው የእስራኤልና የይሁዳ እንዲሁም የኤፍሬምና የምናሴ ሕዝብ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብር በፋሲካ በዓል ተካፋዮች ይሆኑ ዘንድ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ እንዲመጡ የጥሪ ደብዳቤ ላከላቸው፤ 4 ንጉሡና ሕዝቡም በዚሁ ዕቅዳቸው ደስ ተሰኙ። 5 በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት የእስራኤል አምላክ የእግዚአብሔር ፋሲካ ለብዙ ጊዜ ብዛት ባለው ሕዝብ ስላልተከበረ ንጉሡና ሕዝቡ በሰሜን ከሚገኘው ከዳን በደቡብ እስከሚገኘው እስከ ቤርሳቤህ ለሚገኙ እስራኤላውያን በኢየሩሳሌም ተሰብስበው እንዲያከብሩት ዐዋጅ ይታወጅ ዘንድ ወሰኑ። 6 በንጉሡ ትእዛዝ መልእክተኞቹ እንዲህ የሚለውን የንጉሡንና የሕዝቡን ደብዳቤ ይዘው ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ሄዱ። “የእስራኤል ልጆች ሆይ! ከአሦር ንጉሥ ምርኮ የተረፋችሁት ወደ እናንተ ይመለስ ዘንድ፥ ወደ አብርሃም፥ ወደ ይስሐቅና ወደ ያዕቆብ አምላክ ተመለሱ፤ 7 ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ታማኞች እንዳልሆኑት እንደ ቀድሞ አባቶቻችሁና እንደ ወገኖቻችሁ እስራኤላውያን አትሁኑ፤ እንደምታውቁት እግዚአብሔር እነርሱን ለጥፋት አሳልፎ ሰጥቶአቸዋል፤ 8 ለእግዚአብሔር ታዘዙ እንጂ እንደ እነርሱ ልበ ደንዳኖች አትሁኑ፤ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ስጡ፤ ለዘለዓለም ወደ ቀደሰው በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ ኑ፤ ከእንግዲህ ወዲህ እግዚአብሔር ቊጣውን ከእናንተ እንዲመልስ እርሱን ብቻ አምልኩ፤ 9 ወደ እግዚአብሔር ብትመለሱ፥ እነዚያ ልጆቻችሁንና ዘመዶቻችሁን ማርከው የወሰዱ ሰዎች ለእነርሱ በመራራት ወደየመኖሪያ ስፍራቸው ተመልሰው እንዲመጡ ይፈቅዱላቸዋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ስለ ሆነ እናንተ ወደ እርሱ ብትመለሱ እርሱ ፊቱን ከእናንተ አያዞርም።” 10 መልእክተኞቹ በኤፍሬምና በምናሴ ነገዶች ግዛት ወደሚገኙ ከተማዎች ሁሉ በመሄድ እስከ ዛብሎን ነገድ ሰሜናዊ ግዛት ድረስ ዘለቁ፤ እነዚያ ግን በንቀት እየሳቁ ተሳለቁባቸው፤ 11 ይሁን እንጂ ለእግዚአብሔር ትሕትናን በማሳየት ወደ ኢየሩሳሌም ፈቃደኞች ሆነው የመጡ ከአሴር፥ ከምናሴና ከዛብሎን ነገዶች አንዳንድ ሰዎች ነበሩ፤ 12 ደግሞም አንድ ልብ ይሰጣቸው ዘንድ፥ በእግዚአብሔር ቃል የሆነውን የንጉሡንና የባለሥልጣኖቹን ትእዛዝ ያደርጉ ዘንድ እግዚአብሔር የይሁዳን ሕዝብ ልብ አነሣሣ። የፋሲካ በዓል መከበር 13 በሁለተኛው ወር የቂጣን በዓል ለማክበር ብዙ ሰዎች በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። 14 በኢየሩሳሌም መሥዋዕትን ለማቅረብና ዕጣንን ለማጠን አገልግሎት ይውሉ የነበሩትን የጣዖቶች መሠዊያዎች ሁሉ አንሥተው በመውሰድ በቄድሮን ሸለቆ ጣሉአቸው፤ 15 የሁለተኛው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን የበግ ጠቦቶችን ለፋሲካ በዓል መሥዋዕት አድርገው ዐረዱ፤ በዚህ ጊዜ ራሳቸውን ያላነጹ ካህናትና ሌዋውያን በጣም አፈሩ፤ ከዚህም የተነሣ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለዩ፤ ከዚያም በኋላ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ማቅረብ ቻሉ። 16 የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ በሰጠውም ሕግ መመሪያ መሠረት በቤተ መቅደሱ ውስጥ በተመደበላቸው ቦታ ቆሙ፤ ሌዋውያኑም የመሥዋዕቱን ደም ለካህናቱ አቀረቡ፤ ካህናቱም ደሙን በመሠዊያው ላይ ረጩ፤ 17 ከሕዝቡ መካከል ብዙዎቹ ራሳቸውን ያላነጹ ስለ ነበሩ ለፋሲካ የሚሆኑትን የበግ ጠቦቶች ለማረድ አልተፈቀደላቸውም ነበር፤ ስለዚህ ሌዋውያን በእነርሱ ምትክ የበግ ጠቦቶቹን በማረድ ለእግዚአብሔር አቀረቡላቸው፤ 18 በተጨማሪም ከኤፍሬም፥ ከምናሴ ከይሳኮርና ከዛብሎን ነገዶች የመጡት ብዙ ሰዎች የነጹ ስላልነበሩ የፋሲካን በዓል በሚገባ አላከበሩም፤ ንጉሥ ሕዝቅያስም ስለ እነርሱ፥ 19 “የቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን በሥርዓት ያላነጹ ቢሆኑም እንኳ እነሆ በፍጹም ልባቸው አንተን በማምለክ ላይ ይገኛሉ፤ ስለዚህ በቸርነትህ ይቅር በላቸው!” ሲል ጸለየ፤ 20 እግዚአብሔርም የሕዝቅያስን ጸሎት ሰምቶ ይቅር አላቸው፤ አንዳች ጒዳትም አላደረሰባቸውም። 21 በኢየሩሳሌም የተሰበሰበውም ሕዝብ ሰባት ቀን ሙሉ የቂጣን በዓል በታላቅ ደስታ አከበረ፤ ሌዋውያኑና ካህናቱም በየቀኑ በዜማ መሣሪያዎቻቸው በመታጀብ እየዘመሩ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር፤ 22 ሕዝቅያስም ለእግዚአብሔር የተደረገውን የአምልኮ ሥነ ሥርዓት በመምራት ከፍ ያለ ችሎታ ስላሳዩ ሌዋውያኑን አመሰገነ። ለቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ ለእግዚአብሔር ክብር ሰባት ቀን የኅብረት መሥዋዕት አቅርበው ከበሉ በኋላ፥ 23 በተጨማሪ ለሰባት ቀን በዓል እንዲያደርጉ በአንድነት ወስነው በዓሉን በደስታ አከበሩ። 24 ንጉሥ ሕዝቅያስ አንድ ሺህ ኰርማዎችን፥ ሰባት ሺህ በጎችንና ፍየሎችን፥ ባለሟሎቹ የሆኑት ባለሥልጣኖች ደግሞ አንድ ሺህ ኰርማዎችን፥ ዐሥር ሺህ በጎችንና ፍየሎችን ዐርደው እንዲበሉ ለሕዝቡ ሰጡ፤ ቊጥራቸው እጅግ የበዛ ካህናትም ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለዩ፤ 25 ስለዚህ የይሁዳ ሕዝብ፥ ካህናቱ፥ ሌዋውያኑ፥ ከሰሜን ግዛቶች የመጡ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ምድር ለዘለቄታው የሰፈሩ መጻተኞች ሁሉ እጅግ ደስ አላቸው። 26 ከዳዊት ልጅ ከሰሎሞን ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ይህንን የመሰለ በዓል በኢየሩሳሌም ተከብሮ ስለማያውቅ የኢየሩሳሌም ከተማ ሰዎች እጅግ ተደሰቱ። 27 ካህናቱና ሌዋውያኑም ቆመው የእግዚአብሔር በረከት በሕዝቡ ላይ እንዲወርድ ጸለዩ፤ እግዚአብሔርም በተቀደሰ መኖሪያው በሰማይ ሆኖ ጸሎታቸውን ሰማ። |