2 ዜና መዋዕል 29 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ( 2ነገ. 18፥1-3 ) 1 ሕዝቅያስ ዕድሜው ኻያ አምስት ዓመት ሲሆነው ነገሠ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኻያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ፤ እናቱ አቢያ ተብላ የምትጠራ የዘካርያስ ልጅ ነበረች። 2 ሕዝቅያስ የቀድሞ አባቱን የንጉሥ ዳዊትን መልካም ምሳሌነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር አደረገ። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደገና የመንጻት ተግባር 3 ሕዝቅያስ በነገሠበት ዓመት በመጀመሪያው ወር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በር ሁሉ እንደገና ከፍቶ አደሰ፤ 4 ካህናትንና ሌዋውያንን በስተ ምሥራቅ በኩል በሚገኘው በቤተ መቅደሱ አደባባይ ሰበሰባቸው፤ 5 እንዲህም አላቸው፦ “እናንተ ሌዋውያን! ራሳችሁን መቀደስና የቀድሞ አባቶቻችሁን አምላክ የእግዚአብሔርን ቤተ መቀደስ ማንጻት አለባችሁ፤ ቤተ መቅደሱን የሚያረክስ ነገር ሁሉ ከቤተ መቅደሱ ማስወገድ ይኖርባችኋል። 6 የቀድሞ አባቶቻችን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የነበራቸውን ታማኝነት አጓድለዋል፤ እርሱንም በመተው የእርሱ መኖሪያ ከሆነው ስፍራ ፊታቸውን አዞሩ፤ 7 የቤተ መቅደሱን በር ሁሉ ዘጉ፤ መብራቶቹንም አጠፉ፤ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ዕጣንን ማጠን ወይም የሚቃጠል መሥዋዕትን ማቅረብ ተዉ፤ 8 በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቊጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ወረደ፤ እናንተም እንደምታዩት በእነርሱ ላይ ፍርሀትንና ድንጋጤን አምጥቶባቸዋል፤ መዘባበቻም አድርጎአቸዋል። 9 ስለዚህ አባቶቻችን በጦርነት ተገድለዋል፤ ሚስቶቻችንና ልጆቻችን ሁሉ እስረኞች ሆነው ተወስደዋል። 10 “ከእንግዲህ ወዲህ የእግዚአብሔር ቊጣ ከእኛ እንዲርቅ እነሆ እኔ አሁን ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ለመግባት ወስኛለሁ፤ 11 ልጆቼ ሆይ! በፊቱ ቆማችሁ እንድታገለግሉትና የእርሱ አገልጋዮች እንድትሆኑ፥ መሥዋዕትንም እንድታቀርቡ እግዚአብሔር የመረጣችሁ ስለ ሆነ እንግዲህ ቸልተኞች አትሁኑ።” 12-14 ሥራውን እንዲቀጥሉ የተደረጉት ስማቸው ከዚህ በታች የተዘረዘረው ሌዋውያን እነዚህ ነበሩ፦ ከቀዓት ጐሣ፦ የዐማሣይ ልጅ ማሐትና የዐዛርያስ ልጅ ኢዩኤል፤ ከመራሪ ጐሣ፦ የዓብዲ ልጅ ቂሽና የይሀልኤል ልጅ ዐዛርያስ፤ ከጌርሾን ጐሣ፦ የዚማ ልጅ ዮአሕና የዮአሕ ልጅ ዔዴን፤ ከኤሊጻፋን ጐሣ፦ ሺምሪና ይዒኤል፤ ከአሳፍ ጐሣ፦ ዘካርያስና ማታንያ፤ ከሄማን ጐሣ፦ ይሒኤልና ሺምዒ፤ ከይዱቱን ጐሣ፦ ሸማዕያና ዑዚኤል። 15 እነዚህም ሰዎች ሌዋውያን ወገኖቻቸውን ሰብስበው ሁሉም በእግዚአብሔር ሕግ መሠረት ራሳቸውን አነጹ፤ ከዚህም በኋላ ንጉሡ እንዳዘዛቸው ሌዋውያኑ በእግዚአብሔር ሕግ መሠረት ቤተ መቅደሱን አነጹ፤ 16 ካህናቱም ቤተ መቅደሱን ለማንጻት ወደ ውስጡ ገቡ፤ ያልነጻውንም ነገር ሁሉ ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ አወጡት፤ ሌዋውያኑም ከዚያ አንሥተው ከከተማ ውጪ በመውሰድ በቄድሮን ሸለቆ ጣሉት። 17 የማንጻቱ ሥራ በመጀመሪያው ወር መባቻ ቀን ተጀምሮ በስምንተኛው ቀን ወደ ቤተ መቅደስ የሚያስገባው ክፍል ጭምር ሙሉ በሙሉ ተፈጸመ፤ ከዚህ በኋላም ቤተ መቅደሱን ለአምልኮ ሥነ ሥርዓት ለማዘጋጀት በተከታዮቹ ስምንት ቀኖች ማለትም ወሩ በገባ እስከ ዐሥራ ስድስተኛው ቀን ድረስ ሠሩ። ቤተ መቅደሱ እንደገና ለእግዚአብሔር የተለየ መሆኑ 18 ሌዋውያኑ ስለ ተከናወነው ሥራ ለንጉሥ ሕዝቅያስ የሚከተለውን መግለጫ አቀረቡ፦ “የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ፥ የተቀደሰው ኅብስት የሚቀመጥበትን ገበታና ከእነርሱም ጋር የተያያዙትን ሌሎች ዕቃዎች ጭምር ቤተ መቅደሱን በሙሉ አንጽተናል፤ 19 እንዲሁም ንጉሥ አካዝ ለእግዚአብሔር ታማኝ ባልነበረባቸው ዓመቶች ወስዶት የነበረውን ዕቃ ሁሉ መልሰን በማምጣት ለእግዚአብሔር የተለዩ እንዲሆኑ አድርገናል፤ እነዚህም ዕቃዎች በሙሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ፊት ለፊት ባለው ስፍራ ይገኛሉ።” 20 በማግስቱ ጠዋት በማለዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ የከተማይቱን ባለሥልጣኖች ሰብስቦ እነርሱን በማስከተል ወደ ቤተ መቅደሱ ሄደ፤ 21 እነርሱም ለንጉሣዊው ቤተሰብና ለይሁዳ ሕዝብ የኃጢአት ስርየት፥ እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ መንጻት መሥዋዕት ሆነው ለእግዚአብሔር ይቀርቡ ዘንድ ሰባት ኰርማዎችን፥ ሰባት የበግ አውራዎችን፥ ሰባት የበግ ጠቦቶችንና ሰባት ፍየሎችን አመጡ፤ ንጉሡም የአሮን ዘሮች የሆኑትን ካህናት እንስሶቹን በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ መሥዋዕት አድርገው እንዲያቀርቡ አዘዛቸው፤ 22 ካህናቱም በመጀመሪያ ኰርማዎቹን፥ ቀጥሎም በጎቹን፥ በመጨረሻም የበግ ጠቦቶቹን ዐርደው የእያንዳንዱን መሥዋዕት ደም በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ 23 ከዚህ በኋላም ፍየሎቹን ወደ ንጉሡና ወደተሰበሰቡት ሰዎች አቀረቡአቸው፤ ንጉሡና ሰዎቹም እጃቸውን ጫኑባቸው። 24 ንጉሡ ስለ መላው የእስራኤል ሕዝብ የሚቃጠል መሥዋዕትና ለኃጢአት ስርየት የሚሆን መሥዋዕት እንዲቀርብ አዞ ስለ ነበር፥ ካህናቱ በትእዛዙ መሠረት ፍየሎቹን ዐርደው ደማቸውን መሥዋዕት በማድረግ በመሠዊያው ላይ አፈሰሱ። 25 ንጉሥ ሕዝቅያስ እግዚአብሔር በነቢዩ ጋድና በነቢዩ ናታን አማካይነት ለንጉሥ ዳዊት የሰጠውንና ዳዊትም ተግባራዊ ያደረገውን ትእዛዝ በመከተል በበገና፥ በጸናጽልና በመሰንቆ የሠለጠኑ ሌዋውያንን በቤተ መቅደሱ ውስጥ መደበ፤ 26 ሌዋውያን እነዚህን ዳዊት ይጠቀምባቸው የነበሩትን የዜማ መሣሪያዎች ይዘው፥ ካህናቱም እምቢልታ ይዘው በዚያው በቤተ መቅደሱ ውስጥ ቆሙ፤ 27 ንጉሥ ሕዝቅያስ የሚቃጠለውን መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ ያሳርጉ ዘንድ አዘዘ፤ መሥዋዕቱንም ማሳረግ ሲጀምሩ ሕዝቡ የምስጋና መዝሙር አቀረበ፤ መዘምራኑም እምቢልታ መንፋትና በዳዊት የዜማ መሣሪያዎች በመታጀብ ማዜም ጀመሩ፤ 28 በዚያ የነበረ ሕዝብም ሁሉ በኅብረት ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ መሥዋዕቱም ሁሉ ፈጽሞ እስከሚቃጠል ድረስ እምቢልተኞቹ እምቢልታቸውን ይነፉ ነበር። 29 መሥዋዕቱን የማቅረብ ሥራ በተፈጸመ ጊዜ ንጉሥ ሕዝቅያስና በዚያ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ተንበርክከው ለእግዚአብሔር ሰገዱ። 30 ንጉሡና የሕዝቡ መሪዎች ሁሉ በዳዊትና በነቢዩ አሳፍ የተደረሱትን የምስጋና መዝሙሮች ለእግዚአብሔር ክብር እንዲዘምሩ ሌዋውያንን አዘዙ፤ ስለዚህ ሁሉም ተንበርክከው በመስገድ ላይ ሳሉ በታላቅ ደስታ ይዘምሩ ነበር። 31 ንጉሥ ሕዝቅያስም ሕዝቡን “አሁን ራሳችሁን ለእግዚአብሔር የለያችሁ ስለ ሆነ ለእግዚአብሔር ምስጋና ለማቅረብ መሥዋዕታችሁን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አምጡ!” አላቸው፤ እነርሱም ንጉሡ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ አንዳዶቹም በገዛ ፈቃዳቸው ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶችን አመጡ፤ 32 በዚህ ዐይነት ሕዝቡ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ሆነው እንዲቀርቡ ያመጡአቸው እንስሶች ብዛት ሰባ ኰርማዎች፥ አንድ መቶ የበግ አውራዎችና ሁለት መቶ የበግ ጠቦቶች ነበሩ። 33 በተጨማሪ ለአንድነት መሥዋዕት የተለዩ እንስሶች ብዛት ስድስት መቶ በሬዎችና ሦስት ሺህ አውራ በጎች ነበሩ፤ 34 ይህን ሁሉ እንስሳ ዐርደው ቆዳውን ለመግፈፍ በቂ ካህናት ስላልነበሩ ሥራው እስኪጠናቀቅና የነጹ ካህናት እስከሚገኙ ድረስ ሌዋውያን ይረዱአቸው ነበር፤ በመንጻት ረገድ ከካህናት ይልቅ ሌዋውያን ዘወትር ዝግጁዎች ነበሩ። 35 ብዙ ከሆነው የሚቃጠል መሥዋዕት ለደኅንነት መሥዋዕት የሚቀርበው ስብ ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር የሚቀርበው የመጠጥ ቊርባን ነበር። በዚህ ሁኔታ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚደረገው የአምልኮ ሥነ ሥርዓት እንደገና ተጀመረ፤ 36 ንጉሥ ሕዝቅያስና ሕዝቡ ይህን ሁሉ በተፋጠነ አኳኋን ለማከናወን እግዚአብሔር ስለ ረዳቸው እጅግ ተደሰቱ። |