Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 28 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የይሁዳ ንጉሥ አካዝ
( 2ነገ. 16፥1-4 )

1 አካዝ ዕድሜው ኻያ ዓመት ሲሆን ነገሠ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፤ የቀድሞ አባቱን የንጉሥ ዳዊትን መልካም ምሳሌነትን ባለመከተሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገርን አላደረገም፤

2 የእስራኤልን ነገሥታት መጥፎ አርአያነት ተከተለ፤ ባዓል ተብሎ የሚጠራ የጣዖት ምስሎችን አቅልጦ ሠራ፤

3 በሂኖም ሸለቆም ዕጣን አጠነ፤ እስራኤላውያን ወደ ምድሪቱ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ከዚያ ያባረራቸውን ሕዝቦች አጸያፊ ልማድ በመከተል፥ የራሱን ወንዶች ልጆች እንኳ ሳይቀር የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ለጣዖቶች አቀረበ።

4 በኰረብቶች ላይ በሚገኙ በአሕዛብ የማምለኪያ ስፍራዎችና በየዛፉ ጥላ ሥር መሥዋዕትን አቀረበ፤ ዕጣንንም አጠነ።


በሶርያና በእስራኤል ላይ የተደረገ ጦርነት
( 2ነገ. 16፥5 )

5-6 ንጉሥ አካዝ ኃጢአት ስለ ሠራ የሶርያ ንጉሥ ድል እንዲያደርገውና ብዙ ወገኖቹን እስረኞች አድርጎ ወደ ደማስቆ እንዲወስድ እግዚአብሔር ፈቀደ፤ እንዲሁም የረማልያ ልጅ የሆነው የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔ አካዝን ድል እንዲያደርግና እጅግ በጣም ጀግኖች ከሆኑ ከይሁዳ ወታደሮች መካከል በአንድ ቀን መቶ ኻያ ሺህ እንዲገድል እግዚአብሔር ፈቀደ፤ የቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ይህን የፈቀደበት ምክንያት የይሁዳ ሰዎች እርሱን ስለ ተዉ ነው።

7 ዚክሪ ተብሎ የሚጠራ አንድ እስራኤላዊ ወታደር የንጉሥ አካዝን ልጅ ማዕሤያን፥ የቤተ መንግሥቱን አስተዳዳሪ ዓዝሪቃምንና በሥልጣን ከንጉሡ ሁለተኛ የሆነውን ሕልቃናን ገደለ፤

8 አይሁድ ወገኖቻቸው ቢሆኑም እንኳ የእስራኤል ወታደሮች ሁለት መቶ ሺህ ሴቶችንና ሕፃናትን እስረኞች አድርገው ከብዙ ምርኮ ጋር ወደ ሰማርያ ወሰዱአቸው።


ነቢዩ ዖዴድ

9 የእግዚአብሔር ነቢይ የሆነ፥ ዖዴድ ተብሎ የሚጠራ አንድ ሰው በሰማርያ ከተማ ይኖር ነበር፤ የእስራኤል ሠራዊት አይሁድን እስረኞች አድርገው በመውሰድ ወደ ሰማርያ ከተማ በመግባት ላይ ሳሉ ወደ እነርሱ መጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “የቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር በይሁዳ ሕዝብ ላይ ስለ ተቈጣ እነርሱን ድል እንድታደርጉአቸው አደረገ፤ እናንተ ግን ወደ ሰማይ በደረሰ ቊጣ ፈጃችኋቸው፤

10 ይህም አልበቃ ብሎአችሁ የኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ወንዶችና ሴቶች በሙሉ የእናንተ ባሪያዎች ልታደርጉአቸው ታስባላችሁ፤ እናንተስ ይህን ስታደርጉ ኃጢአት በመሥራት አምላካችሁን እግዚአብሔርን ማሳዘናችሁ አይደለምን?

11 አሁንም እነሆ አድምጡኝ! የእግዚአብሔር ቊጣ በእናንተ ላይ ስለ ነደደ እነዚህ እስረኞች ወንድሞቻችሁንና እኅቶቻችሁን ወደየመኖሪያ ስፍራቸው ተመልሰው ይሄዱ ዘንድ ልቀቁአቸው።”

12 እንዲሁም የይሆሐናን ልጅ ዐዛርያስ፥ የመሺሌሞት ልጅ ቤሬክያ፥ የሻሉም ልጅ የይሒዝቂያና የሐድላይ ልጅ ዐማሣ የተባሉት አራት የታወቁ የኤፍሬም ግዛት መሪዎች የሠራዊቱን ድርጊት ተቃወሙ፤

13 እንዲህም አሉአቸው፦ “እነዚህን እስረኞች ወደዚህ አታምጡብን! ከዚህ ቀደም ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን ስላሳዘንን ቊጣው በእኛ ላይ ወርዶአል፤ አሁንም በበደል ላይ በደል እንድንፈጽም ትፈልጋላችሁን?”

14 ስለዚህ ሠራዊቱ እስረኞቹንና ምርኮውን ለሕዝቡና ለመሪዎቻቸው አስረከቡ።

15 ከዚያም በኋላ እነዚያ አራት ሰዎች ለእስረኞቹ ከምርኮው አስፈላጊውን ነገር ሁሉ እንዲሰጡ ተመደቡ፤ እነርሱም ራቊታቸውን ለቀሩት እስረኞች ልብስና ጫማ፥ እንዲሁም በቂ ምግብና ውሃ ሰጡአቸው፤ በቊስላቸውም ላይ የወይራ ዘይት በማፍሰስ ርዳታ አደረጉላቸው፤ በእግር ለመሄድ የማይችሉትን ደካሞችንም በአህያ ላይ አስቀመጡአቸው፤ እስረኞቹም ሁሉ በይሁዳ ግዛት ወደምትገኘው፥ የዘንባባ ዛፍ በብዛት ወደሚገኝባት ወደ ኢያሪኮ ከተማ መልሰው ወሰዱአቸው፤ ከዚህም በኋላ እስራኤላውያን ወደ መኖሪያ ከተማቸው ወደ ሰማርያ ተመለሱ።


አካዝ የአሦርን ርዳታ መለመኑ
( 2ነገ. 16፥7-9 )

16-17 ኤዶማውያን የይሁዳን ግዛት እንደገና በመውረር ብዙ ሰዎችን ማርከው ወሰዱ፤ ስለዚህ ንጉሥ አካዝ ርዳታ እንዲልክለት የአሦርን ንጉሠ ነገሥት ለመነ።

18 በዚሁ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን በምዕራባዊ ኰረብቶች ግርጌና በደቡባዊ ይሁዳ የሚገኙትን ታናናሽ ከተሞች ወረሩ፤ ቤትሼሜሽ፥ አያሎን፥ ገዴሮት፥ ሶኮ፥ ቲምናና ጊምዞ ተብለው የሚጠሩትን ከተሞችና በዙሪያቸው የሚገኙትን መንደሮች በድል አድራጊነት ያዙ፤ በዚያም ኖሩ።

19 የይሁዳ ንጉሥ አካዝ በሀገሩ ላይ ክፉ ነገርን ስላስፋፋና ለእግዚአብሔር የነበረውን ታማኝነት ስላጐደለ፥ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ችግርና መከራ እንዲወርድ ፈቀደ።

20 የአሦር ንጉሠ ነገሥት ቲግላት ፐሌሴርም አካዝን በመርዳት ፈንታ ተቃወመው፤ ችግርም አመጣበት፤

21 ስለዚህ አካዝ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፥ ከቤተ መንግሥቱና ከሕዝቡ መሪዎች ዘንድ ብዙ ወርቅ ወስዶ ለንጉሠ ነገሥቱ መማለጃ አድርጎ ሰጠ፤ ይሁን እንጂ ይህን ማድረጉም አልጠቀመውም።


አካዝ የሠራው ኃጢአት

22 አካዝ፥ ችግሩ እየባሰበት በሄደ ጊዜ ከምንጊዜውም ይበልጥ ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ።

23 አካዝ ድልን ላጐናጸፉአቸው ለሶርያውያን አማልክት መሥዋዕት አቀረበ፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት “የሶርያ አማልክት የሶርያን ነገሥታት ረድተዋል፤ መሥዋዕት ባቀርብላቸው እኔንም ይረዱኛል” ብሎ በማሰብ ነው፤ ይህም ድርጊት በራሱና በሀገሩ ላይ ጥፋትን አመጣ፤

24 በተጨማሪም አካዝ የቤተ መቅደሱን ዕቃ ሁሉ አውጥቶ ሰባበረው፤ ቤተ መቅደሱንም ዘጋ፤ በኢየሩሳሌምም በየስፍራው የጣዖት መሠዊያዎችን አቆመ፤

25 በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ለባዕዳን አማልክት ዕጣን የሚታጠንባቸውን የኰረብታ የማምለኪያ ስፍራዎችን ሠራ፤ በዚህም ሁኔታ አካዝ የቀድሞ አባቶቹን አምላክ የእግዚአብሔርን ቊጣ በራሱ ላይ አመጣ።

26 በአካዝ ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የተፈጸመው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጻሕፍት ተመዝግቦ ይገኛል።

27 ንጉሥ አካዝ ሞተ፤ በኢየሩሳሌምም ተቀበረ፤ ይሁን እንጂ በነገሥታት መካነ መቃብር አልተቀበረም፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ሕዝቅያስ ነገሠ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告