2 ዜና መዋዕል 27 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየይሁዳ ንጉሥ ኢዮአታም ( 2ነገ. 15፥32-38 ) 1 ኢዮአታም ዕድሜው ኻያ አምስት ዓመት ሲሆነው ነገሠ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ይሩሻ ተብላ የምትጠራ የሳዶቅ ልጅ ነበረች። 2 ኢዮአታም አባቱ እንዳደረገው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር ሠራ፤ አባቱ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ዕጣን በማጠን ያደረገውን ኃጢአትም አልሠራም፤ ሕዝቡ ግን ኃጢአት መሥራቱን ቀጥሎ ነበር። 3 ኢዮአታም የቤተ መቅደሱን ሰሜናዊ በር እንደገና ሠራ፤ በተጨማሪም በኢየሩሳሌም በሚገኘው ዖፌል ተብሎ በሚጠራው ኰረብታማ ቦታ የከተማ ቅጽሮችን በመሥራት ብዙ ሥራ አከናውኖአል፤ 4 እንዲሁም በይሁዳ ተራራማ ስፍራዎች ላይ ከተሞችን፥ ደን በበዛባቸው ስፍራዎችም ላይ ምሽጎችንና ቅጽሮችን ሠርቶ ነበር። 5 በዐሞን ንጉሥና በሠራዊቱ ላይ ጦርነት ከፍቶ ድል አድርጎአቸው ነበር፤ ዐሞናውያንንም በየዓመቱ ለሦስት ዓመት በተከታታይ ሦስት ሺህ አራት መቶ ኪሎ የሚመዝን ብር፥ አንድ ሚሊዮን ኪሎ የሚመዝን ስንዴና እንዲሁም አንድ ሚሊዮን ኪሎ የሚመዝን ገብስ እንዲገብሩለት አስገደዳቸው። 6 ኢዮአታም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት መንገዱን ስለ አቀና ገናና እየሆነ ሄደ። 7 በኢዮአታም ዘመነ መንግሥት የተፈጸመው ሌላው ድርጊት ሁሉ፥ ያካሄደው ጦርነትና የመንግሥቱ አመራር ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጻሕፍት ተመዝግበው ይገኛሉ፤ 8 ኢዮአታም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ኻያ አምስት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፤ 9 ከዚያም በኋላ ሞተ፤ በዳዊት ከተማም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አካዝ ነገሠ። |