2 ዜና መዋዕል 26 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየይሁዳ ንጉሥ ዖዝያ ( 2ነገ. 14፥21-22 ፤ 15፥1-7 ) 1 መላው የይሁዳ ሕዝብ ዐሥራ ስድስት ዓመት የሆነውን የአሜስያስን ልጅ ዖዝያን በአባቱ እግር ተተክቶ እንዲነግሥ መረጡት። 2 (ዖዝያ ኤላትን መልሶ በመያዝ ከተማይቱን እንደገና የሠራው ከአባቱ ከአሜስያስ ሞት በኋላ ነው።) 3 ዖዝያ በዐሥራ ስድስት ዓመቱ ነገሠ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኀምሳ ሁለት ዓመት ገዛ፤ እናቱ ይኮልያ ተብላ የምትጠራ የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች። 4 ዖዝያ የአባቱን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር አደረገ፤ 5 መንፈሳዊ አማካሪው ዘካርያስ በሕይወት እስከ ነበረበት ዘመን ድረስ ዖዝያ እግዚአብሔርን በታማኝነት ያገለግል ነበር፤ እግዚአብሔርም ባረከው። 6 ዖዝያ በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ ጥሎ የጋትን፥ የያብኔንና የአሽዶድን ከተማዎች ቅጽሮችን አፈራረሰ፤ በአሽዶድ አጠገብና በቀሩትም የፍልስጥኤም ግዛት ውስጥ የተመሸጉ ከተሞችን ሠራ። 7 ፍልስጥኤማውያንን፥ በጒርባዓል ይኖሩ የነበሩትን ዐረቦችና መዑናውያንን ድል እንዲያደርግ እግዚአብሔር ረዳው። 8 ዐሞናውያንም ለዖዝያ ገበሩለት፤ እጅግ እየገነነ በመሄዱ ዝናው እስከ ግብጽ ድረስ ተሰማ። 9 ዖዝያ በማእዘን ቅጽር በር፥ በሸለቆ ቅጽር በርና በቅጽሩም መጠምዘዣ ላይ መቈጣጠሪያ ግንቦችን በመሥራት የኢየሩሳሌምን ምሽጎች አጠናከረ፤ 10 በምዕራባዊ ኰረብቶች ግርጌና በሜዳዎች ላይ ብዙ የቀንድ ከብቶች ስለ ነበሩትም በገጠር የተመሸጉ መጠበቂያ ግንቦችን ሠራ፤ ብዙ ጒድጓዶችንም ማሰ፤ ግብርና ይወድ ስለ ነበረ በኰረብታማ አገሮችና በለሙ ቦታ የወይን ተክል ተካዮችና ገበሬዎች ነበሩት። 11 ዖዝያ ለጦርነት ዝግጁ የሆነ እጅግ የበዛ ሠራዊት ነበረው፤ የሠራዊቱም አባላት ስም ዝርዝር የንጉሡ ጸሐፊዎች በሆኑት በይዒኤልና በማዕሤያ ይመዘገብ ነበር፤ የእነርሱም የበላይ ተቈጣጣሪ የቤተ መንግሥቱ ሠራተኞች አባል የሆነው ሐናንያ ነበር። 12 ሠራዊቱም የሚመራው በሁለት ሺህ ስድስት መቶ የጐሣ መሪዎች ነበር፤ 13 በእነርሱም ሥልጣን ሥር የንጉሡን ጠላቶች ለመመከት በቂ ችሎታ ያላቸው ሦስት መቶ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ጀግኖች ወታደሮች ነበሩ፤ 14 ዖዝያም ለመላው ሠራዊቱ ጋሻና ጦር፥ የራስ ቊርና የደረት ጥሩርን፥ ቀስትና ፍላጻን፥ ወንጭፍና የሚወነጨፉ ድንጋዮችን አዘጋጅቶለት ነበር፤ 15 ንጉሥ ዖዝያ በኢየሩሳሌም በእጅ ሥራ ጥበብ የሠለጠኑ ሰዎች ከመጠበቂያ ግንቦችና ከከተማይቱ ቅጽር ማእዘኖች ላይ ፍላጻዎችንና ታላላቅ ድንጋዮችን የሚያስፈነጥሩ መሣሪያዎችን እንዲሠሩ አደረገ፤ እግዚአብሔር ስለ ረዳውም እጅግ በረታ፤ እጅግም ገናና ሆነ፤ ዝናውም በሁሉ ስፍራ ተሰማ። ዖዝያ በዕብሪተኛነቱ ተቀጣ 16 ንጉሥ ዖዝያ መንግሥቱን ባጠናከረ ጊዜ ዕብሪተኛ ሆነ፤ ይህም ዕብሪተኛነቱ ወደ ውድቀት አደረሰው፤ በዕጣን መሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን ወደ ቤተ መቅደስ በድፍረት በመግባቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ 17 በዚህ ጊዜ ካህኑ ዐዛርያስና ከእርሱም ጋር ልበ ሙሉና ቈራጥ የሆኑ ሰማኒያ ካህናት ድርጊቱን ለመቃወም ንጉሡን ተከትለው ወደ ቤተ መቅደሱ ገቡ። 18 እንዲህም አሉት፦ “ዖዝያ ሆይ! አንተ ለእግዚአብሔር ዕጣን ታጥን ዘንድ አይገባህም፤ ይህን ለማድረግ የተመደቡት ለእግዚአብሔር የተለዩት የአሮን ልጆች የሆኑት ካህናት ብቻ ናቸው፤ ስለዚህ ከዚህ ከተቀደሰው ስፍራ ውጣ፥ እግዚአብሔር አምላክን አሳዝነሃል፤ ይህም ከእግዚአብሔር ዘንድ ክብርን የሚያስገኝልህ ድርጊት አይደለም።” 19 ዕጣን ለማጠን ዝግጁ ሆኖ ጥናውን በእጁ እንደ ያዘ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በዕጣን መሠዊያው አጠገብ ቆሞ የነበረው ዖዝያም በካህናቱ ላይ እጅግ ተቈጣ፤ ወዲያውኑ በግንባሩ ላይ የቆዳ በሽታ ታየ። 20 ዐዛርያስና ሌሎቹም ካህናት በታላቅ ድንጋጤ የንጉሡን ግንባር ትኲር ብለው ተመለከቱ፤ ከቤተ መቅደስም እንዲወጣ አስገደዱት፤ ዖዝያም እግዚአብሔር እንደ ቀጣው ዐውቆ ለመውጣት ተጣደፈ። 21 ንጉሥ ዖዝያ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የቆዳው በሽታ አለቀቀውም፤ ይህም በመሆኑ በተለየ ቤት ኖረ፤ ከእግዚአብሔርም ቤት እንዲገለል ተደረገ፤ ልጁ ኢዮአታም የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ በመሆን የአገሪቱን ሕዝብ ያስተዳድር ነበር። 22 ንጉሥ ዖዝያ በዘመነ መንግሥቱ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ መዝግቦት ይገኛል። 23 ዖዝያ ሞተ፤ በነገሥታትም መካነ መቃብር አጠገብ ባለው ስፍራ ቀበሩት፤ በነገሥታት መካነ መቃብር ያልተቀበረው የቆዳ በሽታ ስለ ነበረበት ነው፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮአታም ነገሠ። |