2 ዜና መዋዕል 25 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ ( 2ነገ. 14፥2-6 ) 1 አሜስያስ ዕድሜው ኻያ አምስት ዓመት ሲሆን ነገሠ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኻያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ፤ እናቱ ይሆዓዲን ተብላ የምትጠራ የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች፤ 2 አሜስያስ አብዛኛውን ጊዜ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር ያደርግ ነበር፤ ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ የሚያደርገውን ነገር በሙሉ ልብ አያደርግም ነበር፤ 3 መንግሥቱን እንዳጠናከረ ወዲያውኑ አባቱን የገደሉትን ባለሥልጣኖች በሙሉ በሞት ቀጣ፤ 4 ይሁን እንጂ ልጆቻቸውን አልገደለም፤ ልጆቻቸውንም ያልገደለበት ምክንያት እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሰጠው ሕግ “ወላጆች ልጆቻቸው በፈጸሙት ወንጀል፥ ልጆችም ወላጆቻቸው በፈጸሙት ወንጀል በሞት አይቀጡም፤ አንድ ሰው በሞት መቀጣት ያለበት ራሱ በፈጸመው ወንጀል ብቻ ነው” ሲል የተናገረውን ቃል በማክበር ነው። በኤዶም ላይ የተደረገ ጦርነት ( 2ነገ. 14፥7 ) 5 ንጉሥ አሜስያስ የይሁዳና የብንያም ነገዶች የሆኑትን ወንዶች ሁሉ በየጐሣዎቻቸው በቡድን በቡድን በመደልደል በየቡድኑ በሺህ አለቆችና በመቶ አለቆች ሥር መደበ፤ በቡድን የተመደቡትም ሰዎች ዕድሜአቸው ኻያ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶችን ሁሉ የሚያጠቃልል ሲሆን ብዛታቸውም ሦስት መቶ ሺህ ነበር፤ እነርሱም ለጦርነት የተዘጋጁ፥ በጦርና በጋሻ አያያዝ የሠለጠኑ ምርጥ ወታደሮች ነበሩ፤ 6 አሜስያስ በተጨማሪ በሦስት ሺህ አራት መቶ ኪሎ ጥሬ ብር ከእስራኤል አንድ መቶ ሺህ ወታደሮችን ቀጠረ፤ 7 ነገር ግን አንድ ነቢይ ወደ ንጉሥ አሜስያስ መጥቶ “እግዚአብሔር ከኤፍሬምም ሆነ ከማንኛውም የእስራኤል ሕዝብ ጋር ስላልሆነ እነዚህን የእስራኤል ወታደሮች ይዘህ አትዝመት” አለው። 8 “አንተ በዚህ በምታደርገው ጦርነት የእስራኤል ወታደሮች ድጋፍ ይሆኑኛል ብለህ ታስብ ይሆናል፤ ነገር ግን አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ እንድትሆን የሚያደርግህ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ እነሆ አሁንም እርሱ በጠላቶችህ ድል እንድትሆን ያደርግሃል።” 9 አሜስያስ፥ ነቢዩን “አስቀድሜ የከፈልኩትስ ያ ሁሉ ገንዘብ እንዴት ሊሆን ነው?” ሲል ጠየቀው። ነቢዩም “እግዚአብሔር ከዚህ ገንዘብ ይበልጥ የበዛ ሊሰጥህ ይችላል!” ሲል መለሰለት። 10 ስለዚህ አሜስያስ ቅጥረኞቹን ወታደሮች ወደየመኖሪያ ስፍራቸው እንዲሄዱ አሰናበታቸው፤ እነርሱም በይሁዳ ሕዝብ ላይ እጅግ ተቈጥተው ወደ መኖሪያ ስፍራቸው ሄዱ። 11 ከዚህ በኋላ አሜስያስ በወኔ ተነሣሥቶ ወታደሮቹን በመምራት ወደ ጨው ሸለቆ ሄደ፤ በዚያም ወታደሮቹ በኤዶም ሠራዊት ላይ አደጋ ጥለው ዐሥር ሺህ ወታደሮችን ገደሉ፤ 12 ሌሎች ዐሥር ሺህ ወታደሮችንም ማረኩ፤ እስረኞቹንም ሴላዕ ተብላ በምትጠራው ከተማ አጠገብ በሚገኘው ገደል አፋፍ ላይ አውጥተው ጣሉአቸው፤ ሁሉም ከገደሉ በታች በሚገኙ አለቶች ላይ ተፈጥፍጠው ሞቱ። 13 በዚሁ ወቅት፥ አሜስያስ ከእርሱ ጋር ወደ ጦርነት እንዲሄዱ ያልፈቀደላቸው የእስራኤል ወታደሮች በሰማርያና በቤትሖሮን መካከል በሚገኙት በይሁዳ ከተማዎች ላይ አደጋ በመጣል ሦስት ሺህ ሰዎችን ገደሉ፤ እጅግ የበዛ ምርኮም ወሰዱ። 14 አሜስያስ ኤዶማውያንን ድል አድርጎ በተመለሰ ጊዜ ጣዖቶቻቸውን ይዞ መጣ፤ አማልክት አድርጎም በማቆም ሰገደላቸው፤ ዕጣንም አጠነላቸው፤ 15 ይህም ድርጊት እግዚአብሔርን አስቈጣ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ወደ አሜስያስ አንድ ነቢይ ላከ፤ ይህም ነቢይ አሜስያስን “የገዛ ሕዝባቸውን ከአንተ እጅ ለማዳን እንኳ ላልቻሉ ለባዕዳን አማልክት ስለምን ሰገድክ?” ሲል ጠየቀው። 16 ነቢዩ ገና ንግግሩን ሳይፈጽም አሜስያስ “ለመሆኑ አንተን የንጉሡ አማካሪ አድርገን የሾምንህ ከመቼ ወዲህ ነው? ይልቅስ ንግግርህን አቁም፤ አለበለዚያ እገድልሃለሁ!” አለው። ነቢዩም ለአንድ አፍታ ንግግሩን ቆም ካደረገ በኋላ “ይህን ሁሉ በማድረግህና የእኔን ምክር ለመስማት እምቢ በማለትህ እግዚአብሔር ሊያጠፋህ መወሰኑን አሁን ዐወቅሁ” አለው። በእስራኤል ላይ የተደረገ ጦርነት ( 2ነገ. 14፥8-20 ) 17 ከዚህ በኋላ ንጉሥ አሜስያስና አማካሪዎቹ በእስራኤል ላይ አሤሩ፤ አሜስያስም የኢዩ የልጅ ልጅ የኢዮአካዝ ልጅ ወደ ሆነው ወደ እስራኤል ንጉሥ ዮአስ መልእክተኞች በመላክ “እንግዲህ፥ ና ይዋጣልን?” ሲል ለጦርነት አነሣሣው፤ 18 ንጉሥ ዮአስ ግን እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንድ ጊዜ በሊባኖስ ተራራ ላይ የምትገኝ ኲርንችት ወደ ሊባኖስ ዛፍ መልእክት ልካ ‘ለወንድ ልጄ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሴት ልጅህን ስጠኝ’ ስትል ጠየቀችው፤ ነገር ግን አንድ አውሬ በዚያ በኩል ሲያልፍ ስለ ረገጣት ያቺ ኲርንችት ሞተች፤ 19 አሜስያስ ሆይ፥ እነሆ አንተም ኤዶማውያንን ድል ስላደረግህ ልብህ በትዕቢት ተሞልቶአል፤ ይልቅስ በቤትህ ዐርፈህ ብትቀመጥ የሚሻልህ መሆኑን እመክርሃለሁ፤ በአንተና በሕዝብህ ላይ መቅሠፍትን የሚያስከትል ነገር ለመቈስቈስ ስለምን ትፈልጋለህ?” 20 አሜስያስ ግን የዮአስን ምክር ከምንም አልቈጠረውም፥ ይህም የሆነበት ምክንያት አሜስያስ የኤዶማውያንን ጣዖቶች ስላመለከ ድል እንዲሆን እግዚአብሔር ስለ ፈቀደ ነው፤ 21 ስለዚህም የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ የይሁዳን ንጉሥ አሜስያስን ለመውጋት ዘመተ፤ በይሁዳ በሚገኘው ቤትሼሜሽ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ጦርነት ገጠሙ፤ 22 የይሁዳ ሠራዊትም ድል ሆነ፤ ወታደሮቹም ሸሽተው ወደ መኖሪያ ስፍራቸው ሄዱ፤ 23 ንጉሥ ዮአስም አሜስያስን ማርኮ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደው፤ ከኤፍሬም ቅጽር በር አንሥቶ እስከ ማእዘን ቅጽር በር ድረስ ያለውን ርዝመቱ ሁለት መቶ ሜትር ያኽል የሆነውን የኢየሩሳሌምን ቅጽር አፈረሰ። 24 በቤተ መቅደስ የነበረውን ወርቅና ብር ሁሉ፥ በዖቤድኤዶም ዘሮች ይጠበቁ የነበሩትን የቤተ መቅደሱን ዕቃዎችና የቤተ መንግሥቱን ሀብት በሙሉ ምርኮ አድርጎ በመያዣም ስም የወሰዳቸውን ሰዎች በመውሰድ ወደ ሰማርያ ይዞ ሄደ። የአሜስያስ መሞት 25 የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ከሞተ በኋላ የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ፤ 26 አሜስያስ በዘመነ መንግሥቱ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 27 አሜስያስ እግዚአብሔርን ከተወበት ጊዜ ጀምሮ በኢየሩሳሌም ውስጥ እርሱን ለመግደል ሤራ ተጠንስሶ ነበር፤ በመጨረሻም አሜስያስ ሸሽቶ ወደ ላኪሽ ሄደ፤ ነገር ግን ጠላቶቹ እዚያው ድረስ ልከው አስገደሉት፤ 28 ሬሳውንም በፈረስ ላይ ጭነው ወደ ኢየሩሳሌም በማምጣት በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታት መካነ መቃብር ቀበሩት። |