2 ዜና መዋዕል 24 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስ ( 2ነገ. 12፥1-16 ) 1 ኢዮአስ በሰባት ዓመቱ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ አርባ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ጺቢያ ተብላ የምትጠራ የቤርሳቤህ ከተማ ተወላጅ ነበረች፤ 2 ካህኑ ዮዳሄ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ ኢዮአስ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያስኝ ነገር ያደርግ ነበር፤ 3 ዮዳሄ ለንጉሥ ኢዮአስ ሁለት ሚስቶችን መርጦለት ነበር፤ እነርሱም ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወልደውለታል። 4 ኢዮአስ ከነገሠ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቤተ መቅደሱን ለማደስ ወሰነ፤ 5 ስለዚህ ካህናቱንና ሌዋውያኑን በአንድነት ሰብስቦ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ሄዳችሁ ለአምላካችሁ ቤት ዓመታዊ እድሳት የሚሆን በቂ ገንዘብ ከእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በፍጥነት ሰብስቡ” ሲል አዘዛቸው፤ ሌዋውያኑ ግን ቸል በማለት ዘገዩ፤ 6 ስለዚህ ንጉሥ ኢዮአስ የሌዋውያኑን መሪ ዮዳሄን ጠርቶ፦ “የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ፥ እግዚአብሔር ለሚመለክበት ድንኳን አገልግሎት የሚሆን ግብር የእስራኤል ሕዝብ እንዲያዋጣ ያዘዘውን ሌዋውያኑ ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ሕዝብ ሰብስበው ያመጡ ዘንድ ስለምን አላተጋሃቸውም?” አለ። 7 የዚያች ዐታልያ ተብላ የምትጠራ ክፉይቱ ሴት ተከታዮች ቤተ መቅደሱን አበላሽተውት ነበር፤ ንዋያተ ቅድሳቱን እንኳ ሳይቀር ባዓል ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት በሚደረገው የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ይጠቀሙባቸው ነበር። 8 ንጉሥ ኢዮአስ “የገንዘብ መሰብሰቢያ ሣጥን ሠርታችሁ በቤተ መቅደሱ ቅጽር በር በስተውጭ በኩል አኑሩት” ሲል ሌዋውያኑን አዘዘ፤ 9 ከዚህ በኋላ ሌዋውያኑ በመላው ኢየሩሳሌምና በይሁዳ የሚገኙ ነዋሪዎች ሁሉ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ በምድረ በዳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከእስራኤል ሕዝብ እንዲሰበሰብ ያዘዘውን ግብር ለእግዚአብሔር እንዲያመጡ ትእዛዝ አስተላለፉ፤ 10 ይህም ሕዝቡንና መሪዎቹን ሁሉ ደስ ስላሰኛቸው ገንዘብ በማምጣት ሣጥኑን ሞሉት። 11 ሌዋውያኑም ሣጥኑን ወስደው ኀላፊዎች ለሆኑት ለመንግሥት ባለሥልጣኖች በየቀኑ ያስረክቡት ነበር። ሣጥኑ በገንዘብ በሞላ ቊጥር የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊና የካህናት አለቃው እንደ ራሴ ገንዘቡን ከሣጥኑ አውጥተው ከወሰዱ በኋላ፥ ሣጥኑን መልሰው በቦታው ያኖሩት ነበር፤ በዚህ ዐይነት ብዙ ገንዘብ ሰበሰቡ። 12 ንጉሡና ካህኑ ዮዳሄ ገንዘቡን የቤተ መቅደሱ እድሳት ኀላፊዎች ለሆኑት ሰዎች ይሰጡአቸው ነበር፤ እነዚህም ኀላፊዎች ገንዘቡን ቤተ መቅደሱን የሚጠግኑ ግንበኞችን፥ አናጢዎችንና ብረታ ብረት ሠራተኞችን ይቀጥሩበት ነበር፤ 13 ሠራተኞቹም በብርቱ ትጋት በመሥራት ቤተ መቅደሱን ቀድሞ በነበረው ሁኔታ በጥሩ አኳኋን አደሱት። 14 የእድሳቱ ሥራ ባለቀ ጊዜም ቀሪው ገንዘብ ለንጉሥ ኢዮአስና ለካህኑ ዮዳሄ ተሰጠ፤ እነርሱም በዚህ ወርቅ ለቤተ መቅደሱ አገልግሎትና ለመሥዋዕት የሚውሉ ሳሕኖችንና ሌሎች ልዩ ልዩ ዕቃዎችን ገዙ። ዮዳሄ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ ዘወትር በቤተ መቅደስ መሥዋዕት ይቀርብ ነበር፤ የዮዳሄ አመራር ተለወጠ 15 ዮዳሄ በዕድሜ እጅግ ከሸመገለ በኋላ በአንድ መቶ ሠላሳ ዓመቱ ሞተ፤ 16 እርሱ ለእስራኤል ሕዝብ፥ ለእግዚአብሔርና ለቤተ መቅደሱ ስለ ሰጠው አገልግሎት ውለታ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታት መካነ መቃብር ቀበሩት። 17 ዮዳሄ ከሞተ በኋላ ግን የይሁዳ መሪዎች ወደ ንጉሥ ኢዮአስ መጥተው እጅ በመንሣት ፍላጎታቸውን ገለጡለት፤ እርሱም በሐሳቡ ተስማማ፤ 18 ስለዚህ ሰዎቹም በቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ መስገድ ትተው፥ አሼራ ተብላ ለምትጠራ ሴት አምላክ ጣዖቶችና ምስሎች መስገድ ጀመሩ። ይህንንም ኃጢአት በመሥራታቸው የእግዚአብሔር ቊጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ወረደ። 19 እግዚአብሔር ወደ እርሱ እንዲመለሱ አጥብቀው ያሳስቡአቸው ዘንድ ነቢያትን ላከ፤ መሰከሩባቸውም፤ እነርሱ ግን አላዳመጡም፤ 20 ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ ልጅ በዘካርያስ ላይ ወረደ፤ እርሱም ሕዝቡ ሊያዩት በሚችሉበት ከፍ ያለ ስፍራ ላይ ቆሞ “እግዚአብሔር ‘ትእዛዞቼን ስለምን ትተላለፋላችሁ? በገዛ ራሳችሁስ ላይ ስለምን ጥፋትን ታመጣላችሁ?’ ሲል ይጠይቃችኋል፤ እንግዲህ እናንተ ስለ ተዋችሁት እርሱም ትቶአችኋል” አላቸው። 21 ንጉሥ ኢዮአስ በዘካርያስ ላይ በተደረገው ሤራ ተባባሪ ሆነ፤ ሕዝቡም በንጉሡ ትእዛዝ ዘካርያስን በቤተ መቅደሱ አደባባይ ውስጥ በድንጋይ ወግረው ገደሉት። 22 ንጉሥ ኢዮአስ የዘካርያስ አባት ዮዳሄ ያደረገለትን ቅን አገልግሎት በመዘንጋት ዘካርያስን ገደለ፤ ዘካርያስም ሊሞት ሲያጣጥር ሳለ “እግዚአብሔር ይህን ግፍ ተመልክቶ ይቅጣህ” አለ። የኢዮአስ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ 23 በዚያን ዓመት በመከር ወራት የሶርያ ወታደሮች በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ በመጣል መሪዎቹን ሁሉ ገደሉ፤ እጅግ ብዙ የሆነ ምርኮም ይዘው ወደ ደማስቆ ተመለሱ፤ 24 የሶርያ ሠራዊት ቊጥር ጥቂት ነበር፤ ነገር ግን እጅግ ብዙ የሆነውን የይሁዳን ሠራዊት ድል እንዲያደርግ እግዚአብሔር ፈቀደ፤ ይህም የሆነው እነርሱ የቀድሞ አባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ስለ ተዉ ነው፤ በዚህ ዐይነት በኢዮአስ ላይ ትክክለኛ ፍርድ ተፈጸመበት። 25 በብርቱም ቈስሎ ነበር፤ የጠላት ሠራዊት ከዚያ ተነሥቶ ከሄደ በኋላ ባለሟሎቹ ከሆኑት ባለሥልጣኖች የካህኑን የዮዳሄን ልጅ ደም ለመበቀል በንጉሡ ላይ አሢረው በአልጋው ላይ እንዳለ ገደሉት፤ ንጉሡም በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ይሁን እንጂ በነገሥታት መካነ መቃብር አልተቀበረም። 26 በንጉሡ ላይ ያሤሩትም ሺምዓት ተብላ የምትጠራ የዐሞን ተወላጅ ልጅ የሆነው ዛባድና ሺምሪት ተብላ የምትጠራ የሞአብ ተወላጅ ልጅ የሆነው ይሆዛባድ ናቸው። 27 የኢዮአስ ልጆች ታሪክ፥ በኢዮአስ ላይ ተነግረው የነበሩት የትንቢት ቃላትና ኢዮአስ ቤተ መቅደሱን እንዴት እንዳደሰ በነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ መግለጫ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አሜስያስ ነገሠ። |