2 ዜና መዋዕል 23 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበዐታልያ ላይ የተደረገ ዐመፅ ( 2ነገ. 11፥4-16 ) 1 ካህኑ ዮዳሄ በሰባተኛው ዓመት የመቶ አለቆች ከነበሩት ከይሮሖም ልጅ ዐዛርያስ፥ ከይሆሐናን ልጅ እስማኤል፥ ከዖቤድ ልጅ ዐዛርያስ፥ ከዐዳያ ልጅ ማዕሴያና ከዚክሪ ልጅ ኤሊሻፋጥ ጋር ስምምነት ለማድረግ ብቃት ያለው መሆኑ ተሰማው፤ 2 እነርሱም ወደ መላው የይሁዳ ከተማዎች ተጒዘው ሌዋውያንና የጐሣ መሪዎችን ሁሉ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 3 ሁሉም በአንድነት በቤተ መቅደሱ ተሰብስበው ከንጉሡ ልጅ ከኢዮአስ ጋር የስምምነት ውል አደረጉ፤ ካህኑ ዮዳሄ እንዲህ አላቸው፦ “እግዚአብሔር ለዳዊት ‘ልጆችህ ለዘለቄታ ይነግሣሉ’ ሲል በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት አሁን መንገሥ ያለበት ኢዮአስ ነው፤ 4 አሁን ማድረግ ያለብንም ይኸው ነው፤ ካህናትና ሌዋውያን በሰንበት ቀን አገልግሎታቸውን ለማከናወን በሚመጡበት ጊዜ ከእነርሱ አንድ ሦስተኛው እጅ የቤተ መቅደሱን ቅጽር በሮች ይጠብቅ፤ 5 ሌላው አንድ ሦስተኛ እጅ ቤተ መንግሥቱን ይጠብቅ፤ የመጨረሻው አንድ ሦስተኛ እጅ የመሠረት ቅጽር በር ተብሎ የሚጠራውን ስፍራ ይጠብቅ፤ ሕዝቡም ሁሉ በቤተ መቅደሱ አደባባይ ውስጥ ይሰብሰቡ፤ 6 በአገልግሎት ላይ ከሚገኙት ካህናትና ሌዋውያን በቀር ማንም ሰው ወደ ቤተ መቅደሱ መግባት የለበትም፤ ካህናትና ሌዋውያን ግን ለእግዚአብሔር የተለዩ ስለ ሆኑ መግባት ይፈቀድላቸዋል፤ የቀሩት ሰዎች የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመፈጸም ከቤተ መቅደሱ ውጪ ይሁኑ። 7 ሌዋውያን ሰይፎቻቸውን በእጆቻቸው በመያዝ ዙሪያውን ሆነው ንጉሡን ይጠብቁት፤ ንጉሡ ወደሚሄድበትም ቦታ ሁሉ አብረው ይሂዱ፤ ወደ ቤተ መቅደስ ለመግባት የሚሞክር ማንኛውም ሰው ይገደል።” 8 ሌዋውያንና የይሁዳ ሕዝብ ካህኑ ዮዳሄ የሰጣቸውን መመሪያ ሁሉ ፈጸሙ፤ ዮዳሄም አገልግሎታቸውን ፈጽመው በሰንበት ቀን ከሥራ ነጻ መሆን የሚገባቸው ሌዋውያን አላሰናበታቸውም ነበር፤ ስለዚህ ለዘብ ጥበቃ የሚሰማሩትና ከዘብ ጥበቃ ነጻ የሆኑት እዚያው ስለ ነበሩ የጦር መኰንኖቹ በቂ ሰዎች ነበሩአቸው፤ 9 ዮዳሄም በቤተ መቅደስ ተጠብቀው ይኖሩ የነበሩትን የንጉሥ ዳዊትን ጦሮችና ጋሻዎች ለጦር መኰንኖች ሰጣቸው፤ 10 ሰይፋቸውን በእጃቸው ያያዙትን ጭፍሮች ሁሉ ንጉሡን ከአደጋ ለመከላከል በመሠዊያው በኩል በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ዙሪያውን ተሰልፈው እንዲቆሙ አደረጋቸው። 11 ከዚህ በኋላ ዮዳሄ ኢዮአስን አውጥቶ በራሱ ላይ ዘውድ ጫነበት፤ ለመንግሥቱ መመሪያ የሆነውንም ሕግ አንድ ቅጅ አስረከበው፤ በዚህ ዐይነት ካህኑ ዮዳሄና ልጆቹ ኢዮአስን ቀብተው አነገሡት፤ ሕዝቡም ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “ረጅም ዕድሜ ለንጉሡ!” በማለት ደስታቸውን ገለጡ። 12 ዐታልያ ሕዝቡ ለንጉሡ ያደረገውን እልልታና ሆታ ሰምታ ሕዝብ ወደ ተሰበሰበበት ወደ ቤተ መቅደስ በፍጥነት መጣች። 13 እዚያም እንደ ደረሰች አዲሱ ንጉሥ በተለመደው ባህል መሠረት ለነገሥታት በተመደበው በቤተ መቅደሱ መግቢያ በሚገኘው ዐምድ አጠገብ በጦር መኰንኖችና በእምቢልታ ነፊዎች ተከቦ ታጅቦ እንደ ቆመ አየች፤ ሕዝቡም ሁሉ በደስታ ተሞልተው እልል ይሉ ነበር፤ እምቢልታ ነፊዎችም መለከት ይነፉ ነበር፤ የቤተ መቅደስ መዘምራንም በሙዚቃ መሣሪያዎች ታጅበው የበዓሉን ሥነ ሥርዓት ይመሩ ነበር፤ ዐታልያም በድንጋጤ ልብስዋን በመቅደድ “ይህ ሤራ ነው! ይህ ሤራ ነው!” ስትል ጮኸች። 14 ዮዳሄ በበኩሉ ዐታልያ በቤተ መቅደሱ ክልል ውስጥ እንድትገደል አልፈለገም፤ ስለዚህም የጦር መኰንኖቹን ጠርቶ “ግራና ቀኝ በተሰለፉት ዘቦች መካከል አውጥታችሁ ውሰዱአት፤ እርስዋን ከሞት ለማትረፍ የሚሞክር ሰው ቢኖር ግደሉት” ሲል አዘዛቸው። 15 እነርሱም እርስዋን አፈፍ አድርገው በመያዝ ወደ ቤተ መንግሥት ወሰዱአት፤ እዚያም “የፈረስ መግቢያ ቅጽር በር” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ገደሉአት። ዮዳሄ ያደረገው መሻሻል ( 2ነገ. 11፥17-20 ) 16 ካህኑ ዮዳሄ ራሱ እንዲሁም ንጉሥ ኢዮአስና ሕዝቡ የእግዚአብሔር ሕዝብ መሆናቸውን ለማደስ ቃል ኪዳን እንዲገቡ አደረገ። 17 ከዚህም በኋላ ሁሉም በአንድነት ባዓል ተብሎ ወደሚጠራው ቤተ ጣዖት ሄደው አፈረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን ሁሉ ሰባበሩ፤ ማታን ተብሎ የሚጠራውንም የባዓል ካህን በመሠዊያዎቹ ፊት ለፊት ገደሉት። 18 ዮዳሄ ካህናቱንና ሌዋውያኑን የቤተ መቅደሱ ሥራ ኀላፊዎች እንዲሆኑ አደረገ፤ የእነርሱም ተግባር በንጉሥ ዳዊት የተመደበላቸውን ሥራ ማከናወንና በኦሪት ሕግ መሠረት ለእግዚአብሔር የሚቀርቡትን መሥዋዕት ማቃጠል ነበር፤ እንዲሁም በዳዊት መመሪያ መሠረት የዜማና የበዓል አከባበር ሥነ ሥርዓት ኀላፊነት ተሰጥቶአቸው ነበር፤ 19 ዮዳሄ ያልነጻ ማንኛውም ሰው ወደ ቤተ መቅደስ እንዳይገባ በቤተ መቅደሱ ቅጽር በሮች ሆነው የሚጠብቁ ዘበኞችን መድቦ ነበር። 20 የጦር መኰንኖቹ፥ የታወቁ የአገር ሽማግሌዎች የመንግሥት ባለሥልጣኖችና የቀሩትም ሕዝብ ሁሉ ከዮዳሄ ጋር በመሆን ከቤተ መቅደስ እስከ ቤተ መንግሥት ድረስ ንጉሡን አጅበው ሄዱ፤ በቤተ መንግሥቱም ዋና በር ገቡ፤ ንጉሡም በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ 21 ሕዝቡም ሁሉ በታላቅ ደስታ ተሞሉ፤ ዐታልያም ተገድላ ስለ ነበር ከተማይቱ ሰላም ሰፍኖባት ጸጥ ብላ ነበር። |