Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 22 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ
( 2ነገ. 8፥25-29 ፤ 9፥21-28 )

1 ዐረቦችና ተከታዮቻቸው ወረራ ባደረጉ ጊዜ በሰፈሩ ላይ አደጋ ጥለው ከሁሉ ታናሽ ከሆነው ከአካዝያስ በቀር የንጉሥ ኢዮራምን ወንዶች ልጆች በሙሉ ገደሉ፤ ስለዚህ የኢየሩሳሌም ሕዝብ አካዝያስ በአባቱ እግር ተተክቶ እንዲነግሥ አደረገ፤

2-3 አካዝያስ ዕድሜው ኻያ ሁለት ዓመት ሲሆን ነገሠ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ አንድ ዓመት ገዛ፤ የንጉሥ አክዓብ ልጅ፥ የእስራኤል ንጉሥ የዖምሪ የልጅ ልጅ የሆነች ዐታልያ ተብላ የምትጠራ እናቱ ወደ ክፋት የሚመራ ምክር ትሰጠው ስለ ነበር አካዝያስ የንጉሥ አክዓብን መጥፎ ምሳሌነት ተከተለ፤

4 ከአባቱ ሞት በኋላ፥ የአክዓብ ቤተሰብ አባላት ለጥፋቱ አማካሪዎቹ ስለ ነበሩ እንደ እነርሱ ክፉ አደረገ፤

5 የእነርሱንም ምክር ተከትሎ በሶርያ ንጉሥ አዛሄል ላይ በተደረገው ጦርነት ከእስራኤል ንጉሥ ኢዮራም ጋር ተባበረ፤ ጦርነቱም በገለዓድ በምትገኘው በራሞት አጠገብ ተደርጎ በዚያ ውጊያ ላይ ኢዮራም ቈሰለ፤

6 ስለዚህ ከቊስሉ ለመፈወስ ተመልሶ ወደ ኢይዝራኤል ከተማ ሄደ፤ አካዝያስም ኢዮራምን ለመጠየቅ ወደዚያ ሄደ።

7 አካዝያስ ኢዮራምን ሊጠይቅ የሄደው እግዚአብሔር ይህ ጒብኝት የአካዝያስ መጥፊያ እንዲሆን ስለ ፈቀደ ነው፤ አካዝያስ በዚያ በነበረበት ጊዜ እርሱና ኢዮራም የአክዓብን ሥርወ መንግሥት ለማጥፋት እግዚአብሔር የመረጠውን የኒምሺ ልጅ ኢዩን ለመቀበል ወጡ፤

8 ኢዩ በአክዓብ ሥርወ መንግሥት ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ በመፈጸም ላይ በነበረበት ጊዜ አካዝያስን አጅበው ከእርሱ ጋር መጥተው የነበሩትን የይሁዳ መሪዎችና የአካዝያስን ዘመዶች በዚያ አግኝቶ ሁሉንም ገደላቸው።

9 አካዝያስንም ፈልገው በሰማርያ ተሸሽጎ አገኙት፤ ወደ ኢዩም አምጥተው ገደሉት፤ ነገር ግን የተቻለውን ያኽል እግዚአብሔርን ያገለግል ስለ ነበረው ስለ አያቱ ስለ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ክብር ሲሉ ሬሳውን ቀበሩት። ከአካዝያስ ቤተሰብ አባላት መካከል መንግሥቱን ሊመራ የሚችል አንድም ሰው አልተረፈም።


የይሁዳ ንግሥት ዐታልያ
( 2ነገ. 11፥1-3 )

10 የንጉሥ አካዝያስ እናት ዐታልያ የልጅዋን መገደል እንደሰማች ወዲያውኑ የይሁዳ ንጉሣውያን ቤተሰብ አባሎች በሙሉ እንዲገደሉ ትእዛዝ አስተላለፈች።

11 አካዝያስ፥ ይሆያዳዕ ተብሎ የሚጠራውን ካህን ያገባች ይሆሼባዕ ተብላ የምትጠራ እኅት ነበረችው፤ እርስዋም ከአካዝያስ ወንዶች ልጆች አንዱ የሆነውን ኢዮአስን ሊገድሉ ጥቂት ቀርቶአቸው ከነበሩት መሳፍንት መካከል በስውር ወስዳ እርሱንና ሞግዚቱን በቤተ መቅደስ አጠገብ በሚገኝ መኝታ ቤት ውስጥ ደበቀቻቸው፤ በዚህም ዐይነት በመደበቅ ኢዮአስን በዐታልያ እጅ ከመገደል አዳነችው፤

12 በዐታልያ ዘመነ መንግሥት ኢዮአስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ስድስት ዓመት ሙሉ ተደብቆ ኖረ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告