2 ዜና መዋዕል 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ኢዮሣፍጥ ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘውም በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮራም ነገሠ። የይሁዳ ንጉሥ ኢዮራም ( 2ነገ. 8፥17-24 ) 2 የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጅ የሆነው ኢዮራም ስድስት ወንድሞች ነበሩት፤ እነርሱም ዐዛርያስ፥ ይሒኤል፥ ዘካርያስ፥ ዐዛርያ፥ ሚካኤልና ሸፋጥያ ተብለው የሚጠሩ ናቸው። 3 አባታቸው ብዙ ወርቅና ብር እንዲሁም ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ሌላም ልዩ ልዩ ንብረት ሰጣቸው፤ በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች እያንዳንዱን በአንዳንድ ከተማ ላይ ሾመ፤ ኢዮራም የበኲር ልጁ ስለ ሆነ አባቱ ኢዮሣፍጥ በእርሱ እግር ተተክቶ እንዲነግሥ አደረገ፤ 4 ኢዮራም መንግሥቱን ካጠናከረ በኋላ ወንድሞቹን በሙሉ እንዲሁም አንዳንድ የእስራኤል ባለሥልጣኖችን ገደለ። 5 ኢዮራም በሠላሳ ሁለት ዓመቱ ነገሠ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ስምንት ዓመት ገዛ፤ 6 ከአክዓብ ሴቶች ልጆች አንዲቱን በማግባቱ፥ የንጉሥ አክዓብንና የሌሎቹን የእስራኤል ነገሥታት መጥፎ ምሳሌነት ተከትሎ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን ሠራ፤ 7 ይሁን እንጂ እግዚአብሔር የዳዊትን ሥርወ መንግሥት ሊያጠፋ አልፈለገም፤ ይህም የሆነው እግዚአብሔር ቀደም ብሎ ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን ገብቶ ስለ ነበርና የዳዊት ዘሮችም ዘወትር ሳያቋርጡ የሚነግሡ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የተስፋ ቃል ሰጥቶት ስለ ነበር ነው። 8 በኢዮራም ዘመነ መንግሥት ኤዶም በይሁዳ ላይ ዐምፆ የራሱን ነጻ መንግሥት አቋቋመ፤ 9 ስለዚህ ኢዮራም የጦር መኰንኖቹንና ሠረገሎቹን ይዞ በመዝመት ኤዶምን ወረረ፤ በዚያም የኤዶም ሠራዊት እነርሱን ከበባቸው፤ ነገር ግን ኢዮራምና ሠራዊቱ በሌሊት ከበባውን ጥሰው ለማምለጥ ቻሉ፤ 10 ንጉሥ ኢዮራም የቀድሞ አባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ስለ ተወ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኤዶም ከይሁዳ በመገንጠል ነጻ መንግሥት ሆነች፤ በዚሁ ወቅት የሊብና ከተማም በይሁዳ ላይ ዐመፀች፤ 11 እርሱ በይሁዳ ኰረብቶች ላይ ሳይቀር እንኳ የአሕዛብ የማምለኪያ ስፍራዎችን ሠራ፤ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ወደ ኃጢአት በመምራት እግዚአብሔርን እንዲያሳዝኑ አደረገ። 12 ከዚህ በኋላ ነቢዩ ኤልያስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ለኢዮራም ላከ፦ “የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአባትህን የንጉሥ ኢዮሣፍጥን ወይም የአያትህን የንጉሥ አሳን መልካም ምሳሌነት አልተከተልክም፤ 13 ነገር ግን የእስራኤልን ነገሥታት መጥፎ ምሳሌነት ተከተልክ፤ ልክ አክዓብና በእርሱ እግር የተተኩት ነገሥታት የእስራኤልን ሕዝብ በእግዚአብሔር እንዳይታመኑ እንዳደረጉት ሁሉ አንተም የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ለእግዚአብሔር ታማኞች እንዳይሆኑ አደረግህ፤ ከአንተ የተሻሉትን የአባትህን ቤት ወንድሞችህን እንኳ ሳይቀር ገደልካቸው፤ 14 ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሕዝብህን፥ ልጆችህንና ሚስቶችህን በብርቱ ይቀጣል፤ ንብረትህንም ሁሉ ያጠፋል፤ 15 አንተም ከደዌው ጽናት የተነሣ አንጀትህ እስኪወጣ ድረስ በማይድን ክፉ የአንጀት በሽታ ትሠቃያለህ።” 16 በባሕር ዳርቻ ሰፍረው በነበሩት ኢትዮጵያውያን አጠገብ ፍልስጥኤማውያንና ዐረቦች ይኖሩ ነበር፤ እግዚአብሔርም እነርሱን በኢዮራም ላይ ጦርነት እንዲያደርጉ አነሣሣቸው፤ 17 ስለዚህም ይሁዳን በመውረር ቤተ መንግሥቱን ዘረፉ፤ ከኢዮራም መጨረሻ ልጅ ከአካዝያስ በቀር የንጉሡን ሚስቶችና ወንዶች ልጆች ሁሉ እስረኞች አድርገው ወሰዱአቸው። 18 ከዚህም ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር ሊድን የማይችል ከባድ የአንጀት ሕመም በንጉሡ ላይ አመጣበት፤ 19 ሕመሙም ለሁለት ዓመት ያኽል እየጸናበት ስለ ሄደ አንጀቱ ወጥቶ በብርቱ ሥቃይ ሞተ፤ በቀብሩ ሥነ ሥርዓት ሕዝቡ ለቀድሞ አባቶቹ ይደረግ በነበረው ወግ ዐይነት ስለ ክብሩ እንጨት ከምረው እሳት አላነደዱለትም። 20 ኢዮራም በሠላሳ ሁለት ዓመቱ ነገሠ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ስምንት ዓመት ገዛ፤ እርሱ በሞተ ጊዜ ማንም አላዘነለትም፤ በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ ይሁን እንጂ በነገሥታት መካነ መቃብር አልተቀበረም። |