Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 20 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


በኤዶም ላይ የተደረገ ጦርነት

1 ከዚህ በኋላ የዐሞንና የሞአብ ሠራዊት ከእነርሱም ጋር የጦር ቃል ኪዳን ጓደኞቻቸው የሆኑት መዑናውያን ኢዮሣፍጥን ለመዋጋት መጡ፤

2 ሰዎች መጥተው ለንጉሥ ኢዮሣፍጥ “በአንተ ላይ አደጋ ለመጣል እጅግ ብዙ የሆነ ሠራዊት ከሙት ባሕር ባሻገር ካለው ከኤዶም ምድር መጥቶብሃል፤ እነሆ ሐጸጾንታማርን ቀደም ሲል በድል አድራጊነት ይዘዋል” ሲሉ ነገሩት፤ (ሐጸጾንታማር የዔንገዲ ሌላ መጠሪያ ስሙ ነው፤)

3 ኢዮሣፍጥ እጅግ ስለ ፈራ ፈቃዱን እንዲገልጥለት ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ ከዚህ በኋላ በመላው አገሪቱ ሕዝቡ ሁሉ እንዲጾም ትእዛዝ አስተላለፈ፤

4 ከመላው የይሁዳ ከተሞች ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር እንዲረዳቸው ለመጸለይ ፈጥነው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።

5 ከኢየሩሳሌምም ነዋሪዎች ጋር በአንድነት ሆነው በቤተ መቅደሱ አዲስ አደባባይ ተሰበሰቡ፤ ንጉሥ ኢዮሣፍጥም መጥቶ በሕዝቡ ፊት ቆመ፤

6 ድምፁንም ከፍ በማድረግ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የቀድሞ አባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ በሰማይ ሆነህ የዓለም መንግሥታትን ሁሉ የምታስተዳድር አንተ ነህ፤ ኀይልና ሥልጣን ሁሉ በአንተ እጅ ነው፤ አንተን ሊቋቋምህ የሚችል ማንም የለም፤

7 አንተ አምላካችን ነህ፤ ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህች ምድር በገባ ጊዜ ቀደም ሲል በዚህ ይኖሩ የነበሩትን አሕዛብ አስወጥተህ ወዳጅህ ለነበረው ለአብርሃም ዘሮች ምድሪቱን የሰጠህ አንተ ነህ፤

8 ሕዝብህም በዚህች ምድር እስከ አሁን ይኖራል፤ ለአንተም ክብር ቤተ መቅደስን ሠርቶአል፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት፥

9 ‘እኛን ለመቅጣት ጦርነትን፥ ቸነፈርን ወይም ራብን የመሳሰለውን መቅሠፍት ብታደርስብን የአንተ ስም ወደሚጠራበት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት መጥተን በመቆም ከመከራችን እንድታድነን ወደ አንተ እንጸልያለን፤ አንተም ጸሎታችንን ሰምተህ በመታደግ ታድነናለህ’ ብሎ ነው።

10 “እነሆ አሁን የዐሞን፥ የሞአብና የኤዶም ሕዝቦችን ተመልከት፤ አደጋ ጥለውብናል፤ የቀድሞ አባቶቻችን ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ ወደነዚህ ሕዝቦች ግዛቶች እንዲገቡ አልፈቀድክላቸውም፤ የቀድሞ አባቶቻችን እነርሱን ዞረው አለፉ እንጂ አላጠፉአቸውም፤

11 እነርሱ የሚከፍሉን ወሮታ ግን ይህ ነው፦ አንተ ርስት አድርገህ ከሰጠኸን ምድር አባረው ሊያስወጡን መጥተዋል፤

12 አምላካችን ሆይ! በእኛ ላይ አደጋ ሊጥሉ በብዛት የመጡትን እነዚህን ሠራዊት ሁሉ መቋቋም ስለማንችል አንተ ራስህ ፍረድባቸው፤ የአንተን ርዳታ ለማግኘት ዐይናችንን ወደ አንተ ከማንሣት በቀር ሌላ ምንም ማድረግ እንደሚገባን አናውቅም።”

13 የይሁዳ ሰዎች ሁሉ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር በዚያው በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ቆመው ነበር፤

14 በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ ከሕዝቡ ጋር በነበረ በአንድ ሌዋዊ ላይ ወረደ፤ ይህም ሌዋዊ ያሐዚኤል ተብሎ የሚጠራ የዘካርያስ ልጅ ነበር፤ እርሱም በማታንያ፥ በይዒኤልና በበናያ በኩል ደግሞ የአሳፍ ወገን ነበር፤

15 ያሐዚኤልም እንዲህ አለ፦ “ንጉሥ ሆይ! እናንተም የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ በሙሉ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ተስፋ አትቊረጡ፤ ይህንንም ታላቅ ሠራዊት ለመቋቋም አትፍሩ፤ ጦርነቱ የእግዚአብሔር ነው እንጂ የእናንተ አይደለም፤

16 ስለዚህ ነገ እነርሱ በጺጽ አጠገብ ወዳለው መተላለፊያ ሲመጡ አደጋ ጣሉባቸው፤ በይሩኤል አጠገብ ወዳለው በረሓማ አገር በሚያመራው ሸለቆ መጨረሻ ጫፍ ላይ ታገኙአቸዋላችሁ።

17 በዚህ ጦርነት ላይ የምትዋጉ እናንተ አይደላችሁም፤ ስፍራ ስፍራችሁን ይዛችሁ ብቻ ጠብቁ፤ እግዚአብሔር ድልን እንደሚያጐናጽፋችሁ ታያላችሁ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሆይ! ሳታመነቱና በፍርሃት ሳትሸበሩ ነገ በቀጥታ ሄዳችሁ ተዋጉ! እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል!’ ”

18 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ኢዮሣፍጥና ከእርሱ ጋር የነበሩት የይሁዳና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ በግንባራቸው ወደ መሬት ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤

19 የቀዓትና የቆሬ ጐሣዎች አባላት የሆኑ ሌዋውያን ቆሙ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

20 ሰዎቹ በማግስቱ ጠዋት በማለዳ ተነሥተው ተቆዓ ተብሎ ከሚጠራ ስፍራ አጠገብ ወደሚገኘው በረሓማ አገር ሄዱ፤ ወደዚያ ለመሄድ ጒዞ በመጀመር ላይ ሳሉም ኢዮሣፍጥ እነርሱን “የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሆይ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ተማመኑ፤ እርሱም ብርታትን ይሰጣችኋል፤ የእግዚአብሔር ነቢያት የሚነግሩአችሁንም እመኑ፤ ይሳካላችኋልም” አላቸው።

21 ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ከሕዝቡ ጋር ከተመካከረ በኋላ መዘምራኑ በተቀደሱ በዓላት የሚለብሱአቸውን ካባዎች ለብሰው “ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ!” እያሉ በመዘመር በሠራዊቱ ፊት ለፊት እንዲያልፉ አዘዘ።

22 መዘምራኑ መዘመርና ማመስገን በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔር በወራሪዎቹ ሠራዊት ላይ ድብቅ ጦር አምጥቶባቸው፥ ግራ ተጋቡ፤

23 ስለዚህ ዐሞናውያንና ሞአባውያን በኤዶማውያን ሠራዊት ላይ አደጋ ጥለው በሙሉ ደመሰሱአቸው፤ ከዚያም በመቀጠል በጭካኔ እርስ በርሳቸው ተፋጁ፤

24 የይሁዳ ሠራዊት በረሓውን የሚያሳይ ከፍተኛ ቦታ በደረሱ ጊዜ ጠላቶቹ ወዳሉበት አቅጣጫ ሲመለከቱ ጠላቶቹ በሙሉ አልቀው ሬሳዎቻቸው በምድር ላይ ተጋድመው አዩ፤ አንድም እንኳ በሕይወት ተርፎ ያመለጠ አልነበረም።

25 ከዚህ በኋላ ኢዮሣፍጥና ወታደሮቹ ምርኮ ለመውሰድ ወደዚያ ሄዱ፤ ብዙ የቀንድ ከብት፥ ስንቅና ትጥቅ፥ ልብስና ሌላም ውድ የሆኑ ዕቃዎች አገኙ፤ ምርኮውንም ለመሰብሰብ ሦስት ቀን ፈጀባቸው፤ ነገር ግን ምርኮው እጅግ ብዙ ስለ ነበር ሁሉንም መውሰድ አልቻሉም፤

26 በአራተኛው ቀን እስከ ዛሬ ድረስ “የበረከት ሸለቆ” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ተሰበሰቡ፤ እግዚአብሔር ስላደረገላቸውም ነገር ሁሉ አመሰገኑት፤ ሸለቆው “በረከት” ተብሎ የተጠራውም ስለዚህ ነው።

27 ከዚያ በኋላ በኢዮሣፍጥ መሪነት የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ ድልን ስላጐናጸፋቸው እየተደሰቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

28 ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜም በእምቢልታ፥ በዋሽንትና በበገና ድምፅ እየታጀቡ በሰልፍ ወደ ቤተ መቅደስ ገቡ፤

29 እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንዴት እንደ ተዋጋ የሰሙ መንግሥታት ሁሉ የእግዚአብሔር ፍርሀትና ድንጋጤ ዐደረባቸው።

30 ስለዚህም ኢዮሣፍጥ አገሪቱን በሰላም አስተዳደረ፤ እግዚአብሔርም በሁሉ አቅጣጫ የሰላም ዋስትና ሰጠው።


የኢዮሣፍጥ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ
( 1ነገ. 22፥41-50 )

31 ኢዮሣፍጥ የይሁዳ ንጉሥ የሆነው በሠላሳ አምስት ዓመቱ ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኻያ አምስት ዓመት ገዛ፤ እናቱ ዐዙባ ተብላ የምትጠራ የሺልሒ ልጅ ነበረች፤

32 ኢዮሣፍጥ ከእርሱ በፊት እንደ ነበረው እንደ አባቱ እንደ አሳ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ አደረገ፤

33 ነገር ግን በከፍተኛ ቦታዎች ላይ የሚገኙትን የማምለኪያ ቦታዎች አላስወገደም፤ ሕዝቡም ወደ ቀድሞ አባቶቹ አምላክ ወደ እግዚአብሔር በሙሉ ልቡ ገና አልተመለሰም ነበር።

34 ኢዮሣፍጥ ከነገሠበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዘመነ መንግሥቱ ፍጻሜ ድረስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ ከእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ክፍል አንዱ በሆነው በሐናኒ ልጅ በኢዩ ታሪክ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል።

35 በአንድ ወቅት ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ብዙ ክፉ ነገር ከፈጸመው ከእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ ጋር የስምምነት ውል አድርጎ ነበር፤

36 ሁለቱም በመተባበር ዔጽዮንጋብር ተብሎ በሚጠራ ወደብ ላይ ውቅያኖስን አቋርጠው ሊጓዙ የሚችሉ መርከቦችን ሠርተው ነበር፤

37 ነገር ግን የማሬሻ ተወላጅ የሆነው የዶዳዋ ልጅ ኤሊዔዘር ኢዮሣፍጥን “ከአካዝያስ ጋር የስምምነት ውል ስላደረግህ እግዚአብሔር የሠራኸውን ሁሉ ያጠፋል” ሲል አስጠንቅቆት ስለ ነበር መርከቦቹ በሙሉ ተሰባበሩ፤ ከቶም በባሕር ላይ አልተጓዙም።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告