2 ዜና መዋዕል 19 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኢዩ ተብሎ የሚጠራ ነቢይ ኢዮሣፍጥን መገሠጹ 1 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መንግሥቱ በደኅና ተመለሰ፤ 2 የሐናኒ ልጅ የሆነው ኢዩ ተብሎ የሚጠራው ነቢይ ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ለመገናኘት መጥቶ እንዲህ ሲል ገሠጸው፤ “አንተ ክፉዎችን መርዳትና እግዚአብሔርን ከሚጠሉት ጋር መተባበር መልካም ይመስልሃልን? ይህ ያደረግኸው ክፉ ነገር የእግዚአብሔር ቊጣ በአንተ ላይ እንዲወርድ አድርጎአል፤ 3 ይህም ሁሉ ሆኖ አንዳንድ መልካም ነገር አድርገሃል፤ ይኸውም ሕዝቡ ያመልካት የነበረችውን አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስሎችን ሁሉ ከምድሪቱ አስወግደሃል፤ የእግዚአብሔርንም ፈቃድ ለይተህ ለመፈጸም ጥረት አድርገሃል።” ኢዮሣፍጥ ያደረገው ማሻሻል 4 ንጉሥ ኢዮሣፍጥ መኖሪያውን በኢየሩሳሌም ቢያደርግም እንኳ ሕዝቡ ወደ ቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ለማድረግ በደቡብ ከቤርሳቤህ ጀምሮ በሰሜን እስከ ኰረብታማው የኤፍሬም አገር ዳርቻ ድረስ እየተመላለሰ በየጊዜው በሕዝቡ መካከል ተገኝቶአል፤ 5 በተመሸጉት በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ዳኞችን ሾሞአል፤ 6 እንዲህ የሚል መመሪያም ሰጣቸው፦ “ፍርድ በምትሰጡበት ጊዜ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር መሆኑን በመገንዘብ ብርቱ ጥንቃቄ አድርጉ፤ እናንተ የምትፈርዱት ሰውን ለማስደሰት ሳይሆን ለእግዚአብሔር ነው። 7 ፍትሕ ማጓደል ወይም ማድላት ወይም ጉቦ መቀበል በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ የሌሉ ስለ ሆነ እግዚአብሔርን በመፍራት ትክክለኛ ፍርድ ስጡ።” 8 ንጉሥ ኢዮሣፍጥ የእግዚአብሔርን ሕግ በመተላለፍ ወይም በከተማይቱ ኗሪዎች መካከል የሚነሣውን ሕግ ነክ ክርክር በሚመለከት ጉዳይ ሁሉ ይዳኙ ዘንድ ሌዋውያንን፥ ካህናትንና ከታወቁ የአገር ሽማግሌዎች አንዳንዶቹን በኢየሩሳሌም ሾመ፤ እነርሱም በኢየሩሳሌም ተቀመጡ። 9 የሚከተለውንም መመሪያ ሰጣቸው፤ “እግዚአብሔርን በመፍራት በታማኝነትና በቅን ልቡና አገልግሉ፤ 10 በከተሞች ከተቀመጡት ከወገኖቻችሁ ወደ እናንተ የሚመጣ ጉዳይ፥ የግድያ፥ ወይም ሌላ የሕግ ጉዳይ፥ ሕግን፥ ትእዛዞችን ወይም ድንጋጌና ሥርዓቶችን መተላለፍ ቢሆን በእግዚአብሔር ላይ በደል እንዳይፈጽሙ፥ ቊጣም በእናንተና በወንድሞቻችሁ ላይ እንዳይመጣ አስጠንቅቁአቸው፤ እንዲህም ብታደርጉ በደለኞች አትሆኑም። 11 በመንፈሳዊ ጉዳይ ሁሉ ወሳኝ ሥልጣን የሚኖረው ሊቀ ካህናቱ አማርያ ነው፤ በሌላው ጉዳይ ሁሉ ወሳኝ ሥልጣን የሚኖረው የይሁዳ አስተዳዳሪ የሆነው የእስማኤል ልጅ ዘባድያ ነው፤ ሌዋውያን በፊታችሁ እንደ ባለሥልጣን ሆነው ያገለግላሉ፤ ያለ ፍርሀት በድፍረት ሥሩ! እግዚአብሔርም መልካም ሥራ ከሚሠሩት ጋር ይሁን!” |