Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 18 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ነቢዩ ሚክያስ ንጉሥ አክዓብን ማስጠንቀቁ
( 1ነገ. 22፥1-28 )

1 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በሀብት በበለጸገና ዝነኛ በሆነ ጊዜ የእርሱና የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ቤተሰብ በጋብቻ እንዲተሳሰሩ አደረገ፤

2 ከጥቂት ዓመቶች በኋላም ኢዮሣፍጥ አክዓብን ለመጐብኘት ወደ ሰማርያ ከተማ ሄደ፤ አክዓብም ለኢዮሣፍጥና ለአጃቢዎቹ ክብር ብዙ በጎችንና የቀንድ ከብቶችን ዐርዶ ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ አክዓብ በገለዓድ በሚገኘው በራሞት ከተማ ላይ አደጋ ለመጣል ይተባበረው ዘንድ ኢዮሣፍጥን አግባባው፤

3 “በራሞት ላይ አደጋ ለመጣል ከእኔ ጋር ትዘምታለህን?” ሲል ጠየቀው። ኢዮሣፍጥም “እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ነው፤ በጦርነቱም እንተባበርሃለን አለው።

4 ነገር ግን አስቀድመን የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንጠይቅ” አለው።

5 ስለዚህ አክዓብ ቊጥራቸው አራት መቶ የሆነውን ነቢያት ጠርቶ “ወደ ራሞት ሄጄ ጦርነት ልክፈትን? ወይስ ልተው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ሄደህ አደጋ ጣልባት፤ እግዚአብሔርም ድልን ያቀዳጅሃል” ሲሉ መለሱለት።

6 ኢዮሣፍጥ ግን “በእርሱ አማካይነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቅበት ሌላ ነቢይ በዚህ የለምን?” ሲል ጠየቀ።

7 አክዓብም “የይምላ ልጅ የሆነ ሚክያስ ተብሎ የሚጠራ ሌላም ነቢይ አለ፤ ነገር ግን እርሱ ምንጊዜም ቢሆን ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም የትንቢት ቃል ስለማይናገር እርሱን አልወደውም” ሲል መለሰለት። ኢዮሣፍጥም “አንተ ይህን ማለት አይገባህም!” አለው።

8 ከዚህ በኋላ ንጉሥ አክዓብ ባለሟሎቹ ከሆኑት ባለሥልጣኖች አንዱን ጠርቶ “ሚክያስን ፈልገህ በማግኘት በፍጥነት እንዲመጣ አድርግ” ሲል አዘዘው።

9 በዚህ ጊዜ ሁለቱ ነገሥታት ልብሰ መንግሥታቸውን ለብሰው በሰማርያ ቅጽር በር አጠገብ በውጪ በኩል በሚገኘው አውድማ በየዙፋናቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያቱም ሁሉ በነገሥታቱ ፊት ሆነው የትንቢት ቃል ይናገሩ ነበር፤

10 ከእነርሱም አንዱ የከናዕና ልጅ ሴዴቅያስ ከብረት ቀንዶችን ሠርቶ አክዓብን “እግዚአብሔር ‘በእነዚህ ቀንዶች ሶርያውያንን ወግተህ ፍጹም የሆነ ድልን ትቀዳጃለህ’ ይልሃል” አለው።

11 ሌሎቹም ነቢያት ይህንኑ ቃል በመደገፍ “በራሞት ላይ ዝመት፤ ታሸንፋለህ፤ እግዚአብሔር ድልን ይሰጥሃል” አሉት።

12 ሚክያስን ለመጥራት ሄዶ የነበረው መልእክተኛ በዚሁ ጊዜ ሚክያስ “ሌሎች ነቢያት በሙሉ ንጉሥ አክዓብ ድል የሚያደርግ መሆኑን የሚያረጋግጥ የትንቢት ቃል ተናግረዋል፤ ስለዚህ አንተም እንደ እነርሱ ብታደርግ ይሻልሃል” አለው።

13 ሚክያስ ግን “እግዚአብሔር የሚገልጥልኝን ቃል ብቻ የምናገር መሆኔን በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ!” ሲል መለሰለት።

14 ሚክያስም ወደ ንጉሥ አክዓብ ፊት በቀረበ ጊዜ ንጉሡ “ሚክያስ ሆይ፥ ንጉሥ ኢዮሣፍጥና እኔ ወደ ራሞት ሄደን ጦርነት እንክፈት? ወይስ እንተው?” ሲል ጠየቀው። ሚክያስም “ዝመትባት! በእርግጥም ታሸንፋለህ፤ እግዚአብሔርም ድልን ያቀዳጅሃል” ሲል መለሰለት።

15 አክዓብም “በእግዚአብሔር ስም ከእውነት በቀር እንዳትነግረኝ ብዬ የማስምልህ ስንት ጊዜ ነው?” አለው።

16 ሚክያስም “መላው የእስራኤል ሠራዊት ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በኰረብቶች ላይ ተበታትነው አያለሁ፤ እግዚአብሔርም ‘እነዚህ ሰዎች መሪ የላቸውም፤ ስለዚህ ወደየቤታቸው በሰላም ይመለሱ’ ብሎአል” ሲል መለሰለት።

17 አክዓብም ኢዮሣፍጥን “እርሱ ዘወትር ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም የትንቢት ቃል አይናገርም ብዬህ አልነበረምን?” አለው።

18 ሚክያስም የሚናገረውን የትንቢት ቃል በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ እግዚአብሔር የሚለውን ስማ! እግዚአብሔር በሰማይ ባለው ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ መላእክቱም ሁሉ በቀኝና በግራው ቆመው አየሁ፤

19 እግዚአብሔርም ‘አክዓብ ወደ ራሞት ሄዶ በዚያ እንዲገደል ሊያሳስተው የሚችል ማን ነው?’ ሲል ጠየቀ፤ ከመላእክቱም መካከል አንዱ አንድ ነገር፥ ሌላው ሌላ ነገር በመግለጥ የተለያየ ሐሳብ አቀረቡ፤

20 በመጨረሻ ግን አንድ መንፈስ ወደ እግዚአብሔር ፊት ቀርቦ ‘እኔ ላሳስተው እችላለሁ’ አለ፤ እግዚአብሔርም ‘እንዴት አድርገህ ልታሳስተው ትችላለህ?’ አለው፤

21 መልአኩም ‘ሄጄ የአክዓብ ነቢያት ሁሉ ሐሰት እንዲናገሩ አደርጋለሁ’ ሲል መለሰ፤ እግዚአብሔርም ‘እንግዲያውስ ሄደህ አሳስተው፤ ይከናወንልሃል’ አለው።”

22 ሚክያስም “እግዚአብሔር እንዴት አድርጎ በእነዚህ በነቢያትህ አንደበት የሐሰት መንፈስ እንዳስቀመጠ ታያለህን? ይህንንም ያደረገው በአንተ ላይ ጥፋትን ስለ ወሰነብህ ነው!” አለው።

23 የከናዕና ልጅ ሴዴቅያስ ወደ ሚክያስ ቀረብ ብሎ በጥፊ መታውና “ኧረ ከመቼ ወዲህ ነው የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኔ አልፎ አንተን ያነጋገረህ?” አለው።

24 ሚክያስም “ወደ ጓዳ ሄደህ በምትሸሸግበት ጊዜ ታገኘዋለህ” ሲል መለሰለት።

25 በዚህን ጊዜ ንጉሥ አክዓብ ከጦር መኰንኖቹ አንዱን “ሚክያስን ያዘው፤ ወደ ከተማይቱ ገዢ ወደ አሞንና ወደ ልዑል ዮአሽ ውሰደው፤

26 እኔም ከዘመቻ በደኅና እስክመለስ ድረስ በእስር ቤት አስገብተው ደረቅ እንጀራና ውሃ ብቻ እየሰጡት እንዲቈይ ያደርጉ ዘንድ በእኔ ስም ንገራቸው” ሲል አዘዘው።

27 ሚክያስም “አንተ ከዘመቻ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አማካይነት አልተናገረም ማለት ነው!” አለው። ቀጥሎም ድምፁን ከፍ በማድረግ “በዚህ የምትገኙ ሁሉ እኔ የተናገርኩትን ሁሉ ልብ ብላችሁ አድምጡ!” አለ።


የአክዓብ መሞት
( 1ነገ. 22፥29-35 )

28 ከዚህ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በገለዓድ ምድር ወደምትገኘው ወደ ራሞት ገለዓድ ወጡ፤

29 አክዓብም ኢዮሣፍጥን “ወደ ጦርነት ለመሄድ ስንነሣ እኔ ሌላ ሰው መስዬ ለመታየት ሌላ ልብስ እለብሳለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ሌላ ልብስ ለብሶ ማንነቱን በመሰወር ዘመተ።

30 የሶርያ ንጉሥም “የእስራኤል ንጉሥ አክዓብን ነጥላችሁ ግደሉ እንጂ በሌላ በማንም ላይ አደጋ አትጣሉ” ሲል ለሠረገላ ጦር አዛዦች ትእዛዝ አስተላለፈ።

31 ስለዚህ ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ስለ መሰላቸው በእርሱ ላይ አደጋ ለመጣል ከበቡት፤ ነገር ግን ኢዮሣፍጥ ጮኸ፤ እግዚአብሔር አምላክም ከእነርሱ እጅ በመታደግ አዳነው፤ እነርሱም በእርሱ ላይ አደጋ ከመጣል ተገቱ።

32 የሠረገላዎቹ አዛዦች ኢዮሣፍጥ የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን በተገነዘቡ ጊዜ እርሱን ማሳደድ ተዉ፤

33 ይሁን እንጂ አንድ የሶርያ ወታደር በአጋጣሚ ያስፈነጠረው ፍላጻ በጥሩሩ መጋጠሚያ በኩል አልፎ አክዓብን መታው፤ ንጉሥ አክዓብም የሠረገላ ነጂውን “እኔ ቈስያለሁ! ስለዚህ ሠረገላውን መልሰህ ከጦር ሜዳው ውጣ!” ሲል አዘዘው።

34 ጦርነቱም በተፋፋመ ጊዜ ንጉሥ አክዓብ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ ተደግፎ ይታይ ነበር፤ ፀሐይ ስትጠልቅም ሞተ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告