Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 15 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ንጉሥ አሳ ያደረገው መሻሻል

1 የእግዚአብሔር መንፈስ በዖዴድ ልጅ በዐዛርያስ ላይ ወረደ፤

2 ዐዛርያስም ከንጉሥ አሳ ጋር ለመገናኘት ሄዶ እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ አሳ ሆይ! አድምጠኝ! እናንተም የይሁዳና የብንያም ሰዎች ሁሉ ስሙኝ! እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር እስከ ሆናችሁ ድረስ እርሱም ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ከፈለጋችሁትም ታገኙታላችሁ፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል፤

3 የእስራኤል ሕዝብ ለብዙ ዘመን ያለ እውነተኛ አምላክ፥ ያለ ሕግና ያለ አስተማሪ ካህን ይኖር ነበር፤

4 መከራ በደረሰባቸው ጊዜ ግን ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ፊታቸውን መልሰው ፈለጉት፤ አገኙትም፤

5 በዚያን ጊዜ በየስፍራው ሁሉ ሁከትና ሽብር ስለ ነበር፥ በሰላም ወጥቶ የሚገባ ማንም አልነበረም፤

6 እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ችግርን ሁሉ ያመጣባቸው ስለ ነበር አንዱ ሕዝብ ሌላውን ሕዝብ አንዲቱ ከተማ ሌላይቱን ከተማ ያጠፉ ነበር።

7 እናንተ ግን በርቱ፤ አትታክቱ፤ ለምትሠሩት መልካም ሥራም ዋጋ ታገኛላችሁ።”

8 አሳ የዖዴድ ልጅ ዐዛርያስ የተናገረውን የትንቢት ቃል በሰማ ጊዜ ተበረታታ፤ በይሁዳና በብንያም ምድር እንዲሁም እርሱ ማርኮ በያዛቸው ኰረብታማ በሆነው በኤፍሬም ግዛት በሚገኙት ከተሞች ያሉትን አጸያፊ ጣዖቶች ሁሉ አስወገደ፤ በቤተ መቅደሱ ቅጽር ግቢ ውስጥ ቆሞ የነበረውን የእግዚአብሔርን መሠዊያ አደሰ።

9 አምላኩ እግዚአብሔር ከንጉሥ አሳ ጋር መሆኑን ስላዩ፥ ከኤፍሬም፥ ከምናሴና ከስምዖን ነገዶች የሆኑ ብዙ ሰዎች ወደ አሳ መጥተው በግዛቱ ውስጥ ይኖሩ ነበር፤ አሳም እነዚህን ሰዎች ሁሉ፥ እንዲሁም መላው የይሁዳና የብንያም ሕዝብ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጡ ትእዛዝ አስተላለፈ፤

10 እነርሱም አሳ በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት፥ በሦስተኛው ወር በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤

11 እነርሱ ይዘው ካመጡት ምርኮም በዚያን ቀን ሰባት መቶ በሬዎችና ሰባት ሺህ በጎች ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ፤

12 የቀድሞ አባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ያመልኩትም ዘንድ በመስማማት ቃል ኪዳን ገቡ፤

13 የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የማያመልክ ማንም ወጣት ወይም ሽማግሌ፥ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን በሞት የሚቀጣ መሆኑን በመሐላ ቃል አረጋገጡ፤

14 የገቡትን ቃል ኪዳን የሚጠብቁ መሆናቸውንም በማረጋገጥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በእግዚአብሔር ስም ማሉ፤ ከዚህም በኋላ በጥሩምባና በእምቢልታ ድምፅ ታጅበው በሆታና በእልልታ ደስታቸውን ገለጡ።

15 የይሁዳ ሰዎች ሁሉ በፍጹም ልባቸው ይህን ቃል ኪዳን ስለ ገቡ ደስ ተሰኝተው ነበር፤ እግዚአብሔርንም አጥብቀው ፈለጉት፤ እርሱም ተገኘላቸው፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር በመሆን በዙሪያቸው ሁሉ ሰላም እንዲኖር አደረገላቸው።

16 አያቱ ማዕካ አሼራ ተብላ የምትጠራ የሴት አምላክ አጸያፊ ምስል ስላቆመች፥ ንጉሥ አሳ ከእተጌነትዋ ሻራት፤ ምስሉንም ሰባብሮ አደቀቀው፤ ስብርባሪውንም በቄድሮን ሸለቆ አቃጠለው፤

17 ምንም እንኳ አሳ በኰረብቶቹ ላይ የነበሩትን የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎች ሙሉ በሙሉ ባይደመስሳቸው፥ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆነ፤

18 አባቱ አቢያ ለእግዚአብሔር የተለዩ ያደረጋቸውን ዕቃዎች ሁሉ፥ እንዲሁም አሳ ራሱ ለእግዚአብሔር የተለዩ ያደረጋቸውን ከወርቅና ከብር የተሠሩትን ዕቃዎች በሙሉ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አኖራቸው፤

19 አሳ እስከ ነገሠበት እስከ ሠላሳ አምስተኛው ዓመት ድረስ በአገሪቱ ላይ ጦርነት አልነበረም።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告