Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


አቢያ በኢዮርብዓም ላይ ያደረገው ጦርነት
( 1ነገ. 15፥1-8 )

1 ኢዮርብዓም በእስራኤል ላይ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፥ አቢያ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤

2 መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሦስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱ ሚካያ ተብላ የምትጠራ የጊብዓ ከተማ ተወላጅ የሆነ የኡሪኤል ልጅ ነበረች። በአቢያና በኢዮርብዓም መካከል ጦርነት ተነሥቶ ነበር፤

3 በዚህ ጊዜ አቢያ አራት መቶ ሺህ ሠራዊት ይዞ ሲዘምት፥ ኢዮርብዓም ደግሞ ስምንት መቶ ሺህ ወታደሮችን አሰለፈ።

4 ከዚህ በኋላ አቢያ ኰረብታማ በሆነ በኤፍሬም አገር ወደሚገኘው ወደ ጸማራይም ተራራ ወጥቶ ቆመ፤ ድምፁን ከፍ በማድረግም ለኢዮርብዓምና ለእስራኤላውያን በሙሉ እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ አድምጡኝ!

5 ዳዊትና ልጆቹ በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም እንደሚነግሡ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር የማይሻር ቃል ኪዳን መግባቱን አታውቁምን?

6 ይህ ሆኖ ሳለ፥ የሰሎሞን አሽከር የሆነው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በጌታው በሰሎሞን ላይ ዐመፀ፤

7 ዘግየት ብሎም ኢዮርብዓም የማይረቡ ወሮበሎችን ሰበሰበ፤ እነርሱም በዕድሜው ማነስና በዕውቀት ያልበሰለ በመሆኑ ሊቋቋማቸው የማይችለውን የሰሎሞንን ልጅ ሮብዓምን በረቱበት።

8 አሁንም እናንተ እግዚአብሔር ለዳዊት ዘሮች የሰጠውን የመንግሥት ሥልጣን በመድፈር ለመቃወም ዐቅዳችኋል፤ ይህ ዕቅዳችሁ ግቡን እንዲመታ ለማድረግም እጅግ ብዙ የሆነ የጦር ሠራዊት አሰልፋችኋል፤ ለእናንተ አማልክት እንዲሆኑ ኢዮርብዓም ከወርቅ ያሠራቸውን የጥጃ ምስሎች ይዛችሁ መጥታችኋል።

9 የእግዚአብሔር ካህናት የሆኑትን የአሮንን ልጆች ሌዋውያንን አባረራችሁ፤ በእነርሱም ምትክ ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት ሁሉ ለራሳችሁ ካህናትን ሾማችኋል፤ አንድ ወይፈንና ሰባት በጎች ይዞ ራሱን ለመለየት ወደ እናንተ የሚመጣውን ማንኛውንም ሰው ሐሰተኞች ለሆኑት አማልክታችሁ ካህን አድርጋችሁ ትሾማላችሁ።

10 “እኛ ግን አሁንም እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ ከእርሱም ፈቀቅ አላልንም፤ የአሮን ልጆች የሆኑ ካህናትም እግዚአብሔርን ማገልገላቸውን አላቋረጡም፤ ሌዋውያንም እንደ ወትሮው ሁሉ ካህናትን ይረዳሉ፤

11 በየቀኑ ጧትና ማታ መዓዛው ጣፋጭ የሆነውን ዕጣንና የሚቃጠለውን የእንስሳት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያሳርጋሉ፤ በነጻው ገበታም ላይ የመባ ኅብስት ያቀርባሉ፤ ዘወትር ማታ ማታም ከወርቅ በተሠራው መቅረዝ ላይ ያሉትን ቀንዲሎች ያበራሉ፤ እኛ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንፈጽማለን፤ እናንተ ግን እግዚአብሔርን ትታችኋል።

12 የእኛ መሪ ራሱ እግዚአብሔር ነው፤ የእግዚአብሔር ካህናትም መለከት ለመንፋት ተዘጋጅተው እዚህ ከእኛ ጋር ይገኛሉ፤ እነርሱ እምቢልታ መንፋት እንደ ጀመሩም እኛ በእናንተ ላይ ጦርነት እንከፍታለን፤ ስለዚህ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ከቶ ድል ማድረግ ስለማትችሉ፥ ከቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ጦርነት አትግጠሙ!”

13 በዚህ ጊዜ ኢዮርብዓም ከሠራዊቱ ከፊሉን ከይሁዳ ሠራዊት በስተጀርባ በማድፈጥ፥ አደጋ እንዲጥሉ ሲልክ፥ የቀሩትን ደግሞ የይሁዳን ሠራዊት ፊት ለፊት እንዲገጥሙአቸው አደረገ።

14 የይሁዳ ሕዝብም ዙሪያውን ተመልክቶ መከበቡን ባየ ጊዜ እንዲረዳው ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ ካህናቱም እምቢልታ ነፉ፤

15 የይሁዳም ሰዎች ከፍ ባለ ድምፅ እየጮኹ፥ በንጉሥ አቢያ መሪነት አደጋ ጣሉ፤ እግዚአብሔርም ኢዮርብዓምንና የእስራኤልን ሠራዊት ድል አደረገ፤

16 እስራኤላውያንም ከይሁዳ ሰዎች ፊት ሸሹ፤ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ለይሁዳ ሕዝብ አሳልፎ ሰጣቸው፤

17 አቢያና ሠራዊቱ እስራኤላውያንን ድል አድርገው ከፍ ያለ ጒዳት አደረሱባቸው፤ በዚህ ጦርነት ከእስራኤል አምስት መቶ ሺህ ምርጥ ወታደሮች ተገደሉ።

18 የይሁዳም ሰዎች በቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ በእግዚአብሔር ስለ ታመኑ፥ በእስራኤል ላይ ድልን ተቀዳጁ፤ የእስራኤል ልጆች ግን ተዋረዱ።

19 አቢያ የኢዮርብዓምን ሠራዊት አሳደደ፤ ከኢዮርብዓም ከተማዎች መካከልም ቤትኤልን፥ ይሻናንና ዔፍሮንን በአካባቢያቸው የሚገኙትን መንደሮች ጭምር በድል አድራጊነት ያዘ፤

20 ከዚያም በኋላ ኢዮርብዓም በአቢያ ዘመነ መንግሥት ኀይሉን ሊያንሠራራ አልቻለም፤ በመጨረሻም እግዚአብሔር በሞት ቀሠፈው።

21 አቢያ ግን ይበልጥ እየበረታ ሄደ፤ ዐሥራ አራት ሚስቶችን አግብቶ ኻያ ሁለት ወንዶች ልጆችንና ዐሥራ ስድስት ሴቶች ልጆችን ወለደ፤

22 የቀረው የንጉሥ አቢያ ታሪክ፥ እርሱ የተናገራቸው ቃላትና ያከናወነው ሥራ ሁሉ፥ በነቢዩ ዒዶ የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告