2 ዜና መዋዕል 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሸማዕያ የተናገረው የትንቢት ቃል ( 1ነገ. 12፥21-24 ) 1 ንጉሥ ሮብዓም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከይሁዳና ከብንያም ነገዶች የተውጣጡ አንድ መቶ ሰማኒያ ሺህ ምርጥ ወታደሮችን ጠርቶ በአንድነት ሰበሰበ፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት የእስራኤልን ነገዶች ወግቶ ግዛቱን እንደገና በቊጥጥሩ ሥር ለማድረግ ዐቅዶ ስለ ነበር ነው። 2 ነገር ግን እግዚአብሔር ነቢዩ ሸማዕያን፥ 3 ለሮብዓም፥ እንዲሁም ለመላው የይሁዳና የብንያም ነገዶች 4 “ወንድሞቻችሁ በሆኑት በእስራኤላውያን ሕዝብ ላይ አደጋ አትጣሉ፤ ሁላችሁም ወደየቤታችሁ ሂዱ፤ ይህ የሆነው በእኔ ፈቃድ ነው” ብሎ እንዲነግር አዘዘው፤ እነርሱም ሁሉ ለእግዚአብሔር ቃል ታዛዦች በመሆን፥ በኢዮርብዓም ላይ ሳይዘምቱ ወደየቤታቸው ተመልሰው ሄዱ። ሮብዓም ከተማዎችን መመሸጉ 5 ሮብዓም መኖሪያውን በኢየሩሳሌም አድርጎ ስማቸው ከዚህ በታች ለተመለከተው ለይሁዳና ለብንያም ከተሞች ምሽጎችን ሠራ፤ 6 ከተሞቹም ቤተልሔም፥ ዔጣም፥ ተቆዓ፥ 7 ቤትጹር፥ ሶኮ፥ ዐዱላም፥ 8 ጋት፥ ማሬሻ፥ ዚፍ፥ 9 አዶራይም፥ ላኪሽ፥ ዐዜቃ፥ 10 ጾርዓ፥ አያሎንና ኬብሮን ተብለው የሚጠሩት ናቸው። 11 ሮብዓም እነዚህን ከተሞች አጠንክሮ መሸገ፤ ለእያንዳንዳቸውም አንዳንድ የከተማ ኀላፊ ሾመ፤ በእያንዳንዳቸውም ውስጥ እህል፥ የወይራ ዘይትና የወይን ጠጅ፥ 12 እንዲሁም ጋሻና ጦር አከማቸ፤ በዚህም ዐይነት የይሁዳንና የብንያምን ግዛት በቊጥጥሩ ሥር አደረገ። ካህናትና ሌዋውያን ከእስራኤል ወደ ይሁዳ መምጣታቸው 13 ካህናትና ሌዋውያን ከመላው የእስራኤል ግዛት በደቡብ በኩል ወደሚገኘው ወደ ይሁዳ ግዛት መጡ፤ 14 የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓምና በእርሱ እግር የተተኩት ዘሮቹ ሌዋውያንን የእግዚአብሔር ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ ስላልፈቀዱላቸው ሌዋውያን ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም የመጡት የግጦሽ ቦታዎቻቸውንና የቀረውንም ንብረታቸውን ሁሉ ትተው ነው። 15 ኢዮርብዓም በኰረብቶች ላይ በሚገኙ የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎች የሚያገለግሉ፥ ለአጋንንትና እርሱ ራሱ በጥጆች አምሳል ለሠራቸው ጣዖቶች የሚሰግዱ የራሱን ካህናት ሾሞ ነበር፤ 16 ከዚህም የተነሣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔርን በቅን መንፈስ ለማምለክ የፈለጉ ከመላው የእስራኤል ነገዶች የተውጣጡ ብዙ ሰዎች ለቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ለማቅረብ ሌዋውያኑን ተከትለው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 17 ይህም ሁኔታ የይሁዳን መንግሥት አጠናከረ፤ ሦስት ዓመት ሙሉም የሰሎሞንን ልጅ ሮብዓምን ረዱ፤ የንጉሥ ዳዊትንና የንጉሥ ሰሎሞንን መንገድ ተከትለው በሰላም ኖሩ። የሮብዓም ቤተሰብ 18 ሮብዓም ማሐላት ተብላ የምትጠራ ሴት አገባ፤ የእርስዋ አባት ያሪሞት የተባለው የዳዊት ልጅ ሲሆን፥ እናትዋ አቢሃይል ተብላ የምትጠራ የእሴይ የልጅ ልጅ የኤሊአብ ልጅ ናት፤ 19 ማሐላትም ይዑሽ፥ ሸማርያና ዛሃም ተብለው የሚጠሩትን ሦስት ወንዶች ልጆች ለሮብዓም ወለደችለት፤ 20 ቈየት ብሎም ሮብዓም፥ ማዕካ ተብላ የምትጠራውን የአቤሴሎምን ልጅ አግብቶ አቢያ፥ ዓታይ፥ ዚዛና ሼሎሚት ተብለው የሚጠሩ አራት ወንዶች ልጆችን ወለደ። 21 ሮብዓም በጠቅላላ ዐሥራ ስምንት ሚስቶችና ሥልሳ ቊባቶች ነበሩት፤ ከእነርሱም ኻያ ስምንት ወንዶችና ሥልሳ ሴቶች ልጆችን ወለደ፤ ከሚስቶቹና ከቊባቶቹ ሁሉ የአቤሴሎምን ልጅ ማዕካን አብልጦ ይወድ ነበር፤ 22 ከማዕካ የተወለደውን አቢያን አልጋ ወራሽ ሊያደርገው በማቀድ የልዑላን አለቃ አድርጎ ሾመው። 23 ሮብዓም ጥበብ በተሞላበት ሁናቴ ለወንዶች ልጆቹ ኀላፊነትን በመስጠት፥ በተመሸጉት የይሁዳና የብንያም ከተሞች ሁሉ ላይ ሾማቸው፤ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በለጋሥነት አደራጀላቸው፤ ከብዙ ሚስቶችም ጋር አጋባቸው። |