2 ዜና መዋዕል 10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበሰሜናዊ ግዛት የሚኖሩ የእስራኤል ነገዶች ማመፅ ( 1ነገ. 12፥1-20 ) 1 ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ፤ በዚያም እርሱን ለማንገሥ የፈለጉ በእስራኤል ሰሜናዊ ግዛት የሚኖሩ እስራኤላውያን ተሰብስበው ይጠብቁት ነበር፤ 2 ከንጉሥ ሰሎሞን በመሸሽ ወደ ግብጽ ኮብልሎ የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን ወሬ በሰማ ጊዜ ከግብጽ ተመልሶ ወደ አገሩ ወደ እስራኤል መጣ፤ 3 እርሱንም በእስራኤል ሰሜናዊ ግዛት የሚኖሩ ነገዶች መልእክት ልከው አስጠሩት፤ ከእርሱም ጋር አብረው ወደ ሮብዓም በመቅረብ፥ 4 “አባትህ ሰሎሞን በእኛ ላይ ከባድ የአገዛዝ ቀንበር ጭኖ አስጨንቆን ነበር፤ ከችግራችን ብታወጣን እንገዛልሃለን” አሉት። 5 ሮብዓምም “እኔም በጒዳዩ እንዳስብበት ጊዜ ስጡኝ፤ ከሦስት ቀን በኋላም ተመልሳችሁ ኑ” አላቸው፤ ስለዚህ እነርሱም ተመልሰው ሄዱ። 6 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሮብዓም የአባቱ የሰሎሞን አማካሪዎች የነበሩትን ሽማግሌዎች በአንድነት ሰብስቦ “እንግዲህ ለዚህ ሕዝብ መልስ መስጠት እንድችል ምን ትመክሩኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። 7 ሽማግሌዎቹም “ለእነርሱ ደግነትን ብታሳያቸው፥ ለጥያቄአቸውም ተስማሚ የሆነ መልስ በመስጠት ደስ ብታሰኛቸው፥ እነርሱ ዘወትር በታማኝነት ያገለግሉሃል” ሲሉ መለሱለት። 8 ሮብዓም ግን የሽማግሌዎቹን ምክር ቸል በማለት ቀድሞ አብሮ ዐደጎቹና አገልጋዮቹ የነበሩትን ጠርቶ፥ 9 “ላደርገው ስለሚገባኝ ነገር ምን ትመክሩኛላችሁ? የአገዛዝ ቀንበር እንዳቀልላቸው ለጠየቁኝስ ሰዎች ምን መልስ ልስጣቸው?” ሲል ጠየቃቸው። 10 እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “አባትህ ቀንበር አክዶብን ነበር፤ አንተ ግን አቅልልልን ለሚሉህ ሰዎች የምትሰጣቸው መልስ ይህ ነው፦ ‘የእኔ ታናሽ ጣት ከአባቴ ወገብ ይበልጥ ትወፍራለች፤ 11 አባቴ በእናንተ ላይ ከባድ የአገዛዝ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፤ እኔ ደግሞ ይኸው የአገዛዝ ቀንበር ይበልጥ እንዲከብድባችሁ አደርጋለሁ፤ ይኸውም አባቴ በአለንጋ ይገርፋችሁ ነበር፤ እኔ ግን እንደ ጊንጥ በሚናደፍ ጅራፍ በመግረፍ አሠቃያችኋለሁ።’ ” 12 ከሦስት ቀን በኋላ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ ሮብዓም በሰጣቸው ቀጠሮ መሠረት ተመልሰው ወደ እርሱ መጡ። 13 ንጉሥ ሮብዓምም ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ውድቅ አድርጎ ሕዝቡን በማመናጨቅ መናገር ጀመረ፤ 14 ወጣቶቹም በሰጡት ምክር መሠረት “አባቴ በእናንተ ላይ ከባድ የአገዛዝ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፤ እኔ ደግሞ ይኸው የአገዛዝ ቀንበር ይበልጥ እንዲከብድባችሁ አደርጋለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ይገርፋችሁ ነበር፤ እኔ ግን እንደ ጊንጥ በሚናደፍ ጅራፍ በመግረፍ አሠቃያችኋለሁ!” ሲል መለሰላቸው። 15 ይህም የሆነበት ምክንያት ከሴሎ በመጣው በነቢዩ አኪያ አማካይነት ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓም እግዚአብሔር የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው፤ ንጉሥ ሮብዓምም የሕዝቡን ሐሳብ ችላ በማለት ሳይቀበል የቀረበትም ምክንያት ይኸው ነው። 16 እስራኤላውያን ንጉሥ ሮብዓም ጥያቄአቸውን እንዳልተቀበላቸው በተገነዘቡ ጊዜ፥ “ከዳዊት ጋር ምን ድርሻ አለን? ከእሴይ ልጅስ ጋር ምን ግንኙነት አለን? እስራኤል ሆይ! ወደ እየቤትህ ሂድ! ዳዊት ሆይ የራስህን ቤት ጠብቅ!” ብለው መለሱለት። ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ወደ የቤቱ ሄደ። 17 ሮብዓምም በይሁዳ ግዛት በሚኖር ሕዝብ ላይ ብቻ ነገሠ። 18 ከዚህም በኋላ ንጉሥ ሮብዓም የጒልበት ሥራ የሚሠሩ ገባሮች ኀላፊ የነበረውን አዶኒራምን ወደ እስራኤላውያን እንዲሄድ ላከው፤ እነርሱ ግን በድንጋይ ወግረው ገደሉት፤ በዚህን ጊዜ ሮብዓም በፍጥነት ወደ ሠረገላው ገብቶ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ አመለጠ። 19 ከዚያን ጊዜም ጀምሮ ሰሜናዊው ክፍል እስራኤል በሚል ስም በዳዊት ሥርወ መንግሥት ላይ ዐመፀ። |