Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ተሰሎንቄ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕይወት

1 በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ! እግዚአብሔርን ለማስደሰት እንዴት መኖር እንደሚገባችሁ ከእኛ ተምራችኋል፤ አሁንም የምትኖሩት እንዲሁ ነው፤ በጌታ በኢየሱስ ስም የምንለምናችሁና የምንመክራችሁም ከዚህ በፊት ካደረጋችሁት ይበልጥ እንድታደርጉ ነው።

2 በጌታ ኢየሱስ ስም ምን ዐይነት መመሪያ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁ።

3 የእግዚአብሔር ፈቃድ እናንተ እንድትቀደሱና ከዝሙት እንድትርቁ ነው።

4 ከእናንተ እያንዳንዱ ሚስቱን በቅድስናና በክብር ጠብቆ መያዝን ይወቅ።

5 እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ የፍትወት ምኞት አይኑረው።

6 በዚህ ነገር ማንም ሰው አይተላለፍ፤ ሌላ አማኝን አይበድል፤ ከዚህ በፊት እንደ ነገርናችሁና እንዳስጠነቀቅናችሁ እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉትን ጌታ ይቀጣቸዋል።

7 እግዚአብሔር የጠራን በቅድስና እንድንኖር ነው እንጂ በርኲሰት እንድንኖር አይደለም።

8 ስለዚህ ይህን ምክር የሚቃወም፥ የሚቃወመው ቅዱስ መንፈሱን የሚሰጣችሁን እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አይደለም።

9 እርስ በርስ ስለ መዋደድ እናንተ ራሳችሁ ከእግዚአብሔር ስለ ተማራችሁ ስለዚህ ጉዳይ ማንም ሊጽፍላችሁ አያስፈልግም።

10 በመላ መቄዶንያ ያሉትንም ወንድሞች ሁሉ ትወዳላችሁ፤ ሆኖም ወንድሞች ሆይ፥ አሁን የምንመክራችሁ ይበልጥ እንድትወዱ ነው፤

11 በጸጥታም ለመኖር እንድትጣጣሩ እና የራሳችሁን ጉዳይ እንድታስቡ ከዚህ በፊት እንዳዘዝናችሁም በገዛ እጃችሁ እንድትሠሩ ነው።

12 በዚህ ዐይነት በማያምኑት ሰዎች ዘንድ የተከበራችሁ ትሆናላችሁ፤ የማንም ጥገኛ አትሆኑም።


ጌታ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ የሕያዋንና የሙታን ሁኔታ

13 ወንድሞች ሆይ! ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች እንዳታዝኑ ስለ ሞቱት ሰዎች እውነቱን እንድታውቁ እንወዳለን።

14 ኢየሱስ እንደ ሞተና ከሞትም እንደ ተነሣ እናምናለን፤ ስለዚህ በኢየሱስ አምነው የሞቱትን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋል።

15 ከጌታ በተቀበልነው ቃል መሠረት የምንነግራችሁ ይህ ነው፤ ጌታ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ሕያዋን ሆነን የምንቈይ የሞቱትን አንቀድምም።

16 የትእዛዝ ድምፅ፥ የመላእክት አለቃ ድምፅ፥ የእግዚአብሔር እምቢልታም ይሰማል፤ ጌታ ራሱም በእነዚህ ታጅቦ ከሰማይ ይወርዳል፤ በክርስቶስ አምነው የሞቱትም አስቀድመው ይነሣሉ።

17 ከዚህ በኋላ እኛ በሕይወት የምንገኘው ጌታን በአየር ላይ ለመገናኘት ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ ለዘለዓለምም ከጌታ ጋር እንሆናለን።

18 ስለዚህ በዚህ ቃል እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告