1 ተሰሎንቄ 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየጳውሎስ ሐዋርያዊ ሥራ በተሰሎንቄ 1 ወንድሞች ሆይ! የእኛ ወደ እናንተ መምጣት ፍሬቢስ እንዳልሆነ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። 2 እናንተ እንደምታውቁት ከዚህ ቀደም በፊልጵስዩስ በነበርንበት ጊዜ መከራና ስድብ ደርሶብናል፤ ነገር ግን ታላቅ ተቃውሞ ቢደርስብንም እንኳ ወንጌሉን ለእናንተ እንድናስተምር አምላካችን ድፍረትን ሰጥቶናል። 3 እኛ የመከርናችሁ በስሕተት ወይም በርኩስ ዓላማ ተመርተን አይደለም፤ እናንተን ለማታለል ያደረግነው ምንም ነገር የለም። 4 ይልቅስ እግዚአብሔር ወንጌሉን ለእኛ በዐደራ የሰጠን በእኛ ተማምኖ ስለ ሆነ እንናገራለን፤ ይህንንም የምናደርገው ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ብለን ነው እንጂ ሰውን ለማስደሰት ብለን አይደለም። 5 አንድም ጊዜ በቃላት በማቈላመጥ ወይም የገንዘብ ፍላጎት ኖሮን ከቶ እንዳልተናገርን እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ እግዚአብሔርም ምስክራችን ነው። 6 ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ከማንም ሰው ክብርን አልፈለግንም። 7 የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን አስፈላጊውን ከእናንተ ለመጠየቅ እንችል ነበር፤ ነገር ግን ለልጆችዋ እንደምትጠነቀቅ እናት በገርነት በመካከላችሁ ተመላለስን። 8 እንዲሁም በጣም ስለምንወዳችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ ማብሠር ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንንም እንኳ ልንሰጣችሁ ዝግጁዎች ነበርን። 9 ወንድሞች ሆይ! እንዴት እንደ ሠራንና እንደ ደከምን ታውቃላችሁ፤ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ በምናበሥርበት ጊዜ በአንዳችሁም ላይ ሸክም እንዳንሆን ሌሊትና ቀን በመሥራት እንደክም ነበር። 10 በእናንተ በአማኞች መካከል በነበርንበት ጊዜ እንዴት ባለ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም በሌለበት ሕይወት እንደ ኖርን እናንተ ምስክሮች ናችሁ፤ እግዚአብሔርም ምስክር ነው፤ 11 አባት ለልጆቹ እንደሚያደርገው ዐይነት እኛም ለእናንተ ለእያንዳንዳችሁ እንዳደረግንላችሁ ታውቃላችሁ፤ 12 ዘወትር እየመከርናችሁና እያበረታታናችሁ መንግሥቱንና ክብሩን እንድትካፈሉ የጠራችሁ አምላክ ደስ በሚሰኝበት ሁኔታ እንድትኖሩ ዐደራ እንዳልናችሁ ታውቃላችሁ። 13 ደግሞም ስለ እናንተ ሳናቋርጥ እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት ምክንያት አለን፤ ይኸውም ከእኛ የሰማችሁትን የእግዚአብሔርን ቃል በተቀበላችሁ ጊዜ በእናንተ በአማኞች የሚሠራውን ይህንን ቃል የተቀበላችሁት እንደ ሰው ቃል ሳይሆን ልክ እንደ እግዚአብሔር ቃል አድርጋችሁ ነው፤ በእርግጥም የእግዚአብሔር ቃል ነው። 14 ወንድሞች ሆይ፥ እናንተም በይሁዳ ምድር የሚገኙትን በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያን የሆኑትን አርአያ ተከትላችኋል፤ እነርሱ በአይሁድ መከራ እንደ ደረሰባቸው ሁሉ እናንተም ከገዛ ወገኖቻችሁ መከራ ደርሶባችኋል። 15 አይሁድ ጌታ ኢየሱስንና ነቢያትን የገደሉ እኛንም አሳደው ከአገር ያስወጡ ናቸው፤ እነርሱ እግዚአብሔርን የሚያሳዝኑና ሰዎችን ሁሉ የሚጠሉ ናቸው፤ 16 አሕዛብ የሚድኑበትን ቃል እንዳንናገር እንኳ ይከለክሉናል፤ በዚህ ዐይነት ኃጢአትን በኃጢአት ላይ እየጨመሩ ይሄዳሉ፤ ስለዚህ በመጨረሻ የእግዚአብሔር ቊጣ መጥቶባቸዋል። ጳውሎስ የተሰሎንቄን ሰዎች እንደገና ለመጐብኘት የነበረው ምኞት 17 ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! በመንፈስ ሳይሆን በሥጋ ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ በመለየታችን ስለ እናንተ ያለን ናፍቆት ብዙ ስለ ሆነ በዐይነ ሥጋ ልናያችሁ ብዙ ጥረት አደረግን። 18 ወደ እናንተ መምጣት ፈልገን ነበር፤ በተለይም እኔ ጳውሎስ ወደ እናንተ ለመምጣት ደጋግሜ ሞክሬ ነበር፤ ነገር ግን ሰይጣን ከለከለን። 19 ታዲያ፥ ተስፋችን ወይም ደስታችን ወይም ጌታችን ኢየሱስ በሚመጣበት ጊዜ በፊቱ የምንመካበት የድል አክሊላችን እናንተ አይደላችሁምን? 20 በእርግጥ ክብራችንና ደስታችን እናንተ ናችሁ። |