Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ነገሥት 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ቤተ መቅደስ መግባት
( 2ዜ.መ. 5፥2—6፥2 )

1 ከዚህ በኋላ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የዳዊት ከተማ ከሆነችው ከጽዮን ለማምጣትና ወደ ቤተ መቅደሱ ለማስገባት የእስራኤል የነገድ መሪዎችና የጐሣ አለቆች ሁሉ እርሱ ወደሚገኝበት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ ጠራ፤

2 የእስራኤልም ወንዶች ሁሉ የዳስ በዓል በሚከበርበት ኢታኒም ተብሎ በሚጠራው በሰባተኛው ወር ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ተሰበሰቡ።

3 መሪዎቹ ሁሉ በተሰበሰቡ ጊዜም ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት አንሥተው ተሸክሙ።

4 ወደ ቤተ መቅደስ አገቡት፤ እንዲሁም ሌዋውያንና ካህናት የእግዚአብሔር መገኛ ድንኳንና በድንኳኑም ውስጥ የነበሩትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ አምጥተው ወደ ቤተ መቅደስ አገቡ።

5 ንጉሥ ሰሎሞንና መላው የእስራኤል ሕዝብ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ተሰበሰቡ፤ ከብዛቱም የተነሣ ሊቈጠር የማይቻል ብዙ በግና የቀንድ ከብት መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ።

6 ከዚህም በኋላ ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው ወደ ቤተ መቅደስ በማግባት በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ወደ ቦታው አምጥተው በኪሩቤል ክንፍ ሥር አኖሩት።

7 የተዘረጉ የኪሩቤል ክንፎችም ታቦቱንና የታቦቱ መሸከሚያ መሎጊያዎችን ሸፍነው ነበር።

8 መሎጊያዎቹ ረጃጅሞች ስለ ሆኑ ጫፎቻቸው በቤተ መቅደሱ ውስጥ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ለሚቆም ሰው ሁሉ በግልጥ ይታዩ ነበር፤ በሌላ አቅጣጫ የሚቆም ግን አያያቸውም፤ መሎጊያዎቹም እስከ ዛሬ በዚያው ይገኛሉ፤

9 የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር እንደ ወጡ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በገባ ጊዜ ሙሴ በሲና ተራራ በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ካኖራቸው ከሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች በቀር በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ሌላ ምንም ነገር አልነበረም።

10 ካህናቱ ከቤተ መቅደሱ እንደ ወጡ ቤተ መቅደሱ ድንገት በደመና ተሞላ፤

11 በደመናውም ውስጥ የነበረው የእግዚአብሔር ክብር ቤቱን ስለ ሞላ ካህናቱ ተመልሰው ለመግባትና አገልግሎታቸውን ለማከናወን አልቻሉም።

12 በዚህ ጊዜ ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጸለየ፥ “እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! አንተ በደመናው ጨለማ ውስጥ እኖራለሁ ብለሃል፤

13 እነሆ አሁን ግርማ ሞገስ ያለው ቤተ መቅደስ ለአንተ ሠርቻለሁ፤ እርሱም አንተ ለዘለዓለም የምትኖርበት ቦታ ይሆናል።”


ሰሎሞን ለሕዝቡ የተናገረው ቃል
( 2ዜ.መ. 6፥3-11 )

14 በዚያ ቆመው ሳሉ፥ ንጉሥ ሰሎሞን ፊቱን ወደ እነርሱ መልሶ የእግዚአብሔር በረከት በእነርሱ ላይ እንዲወርድ እንዲህ ሲል ጸለየ፤

15 “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን! ለአባቴ ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን አጽንቶ ጠብቆአል፤ እርሱም እንዲህ የሚል ነው፦

16 ‘ሕዝቤን ከግብጽ ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ የሚሠራበት በመላው እስራኤል ምንም ዐይነት ከተማ አልመረጥኩም፤ አሁን ግን በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ይነግሥ ዘንድ ዳዊትን መርጬአለሁ።’ ”

17 ቀጥሎም ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ “አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስን ለመሥራት ዐቅዶ ነበር፤

18 እግዚአብሔርም አባቴን ዳዊትን ‘ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ ትሠራ ዘንድ በልብህ ማሰብህ መልካም ነው።

19 ነገር ግን እርሱን የሚሠራልኝ ልጅህ ነው እንጂ አንተ አይደለህም፤ ከአንተ የሚወለደው ልጅ ቤተ መቅደሴን ይሠራል’ አለው።

20 “እነሆ እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቆአል፤ ስለዚህም እኔ በአባቴ እግር ተተክቼ የእስራኤል ንጉሥ ሆኜአለሁ፤ ለእስራኤል አምላክ ቤተ መቅደስንም ሠርቼአለሁ፤

21 እግዚአብሔር ከግብጽ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከቀድሞ አባቶቻችን ጋር ቃል ኪዳን የገባበት የድንጋይ ጽላት ለሚገኝበትም ታቦት ማኖሪያ የሚሆን ቦታ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አዘጋጅቼአለሁ።”


ሰሎሞን ወደ እግዚአብሔር ያቀረበው ጸሎት
( 2ዜ.መ. 6፥12-42 )

22 ከዚህ በኋላ ሰሎሞን በሕዝቡ ፊት ተነሥቶ በመሠዊያው ፊት ለፊት ቆመ፤ እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘረጋ፤

23 እንዲህም አለ፦ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ለአገልጋዮቹ ቃል ኪዳኑን የሚጠብቅና ከልባቸው ታማኞች እስከ ሆኑ ድረስ ፍቅሩን የሚያጸና በላይ በሰማይ በታችም በምድር እንደ አንተ ያለ አምላክ የለም!

24 ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውንም የተስፋ ቃል አጽንተሃል፤ የተናገርከውም ቃል ሁሉ እነሆ ዛሬ ተፈጽሞአል፤

25 አሁንም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ለአባቴ ለዳዊት ‘አንተ ታደርግ በነበረው ዐይነት ልጆችህ ታዛዦች ቢሆኑና በፊቴም በቅንነት ቢመላለሱ ሁልጊዜ ከዘርህ በእስራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚነግሥ ልጅ አላሳጣህም’ ስትል የተናገርከውን የተስፋ ቃል ፈጽም!

26 አሁንም የእስራኤል አምላክ ሆይ! አገልጋይህ ለነበረው ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ሁሉ እንዲፈጸም አድርግ።

27 “በውኑ እግዚአብሔር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ ሰማያት፥ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ሊይዝህ አይችልም፤ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምንኛ ያንስ?

28 ይሁን እንጂ፥ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! ወደ አገልጋይህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፤ ዛሬም አገልጋይህ በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎትና ጥሪውን ስማ።

29 ስሜ ይጠራበታል ወዳልከው ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቀንና ሌሊት ተመልከት፤ እኔም አገልጋይህ ወደዚህ ቤተ መቅደስ የምጸልየውን ጸሎት ስማ።

30 ፊታችንን ወደዚህ ቤተ መቅደስ መልሰን በምንጸልይበት ጊዜ የእኔንና የሕዝብህን ጸሎት ስማ፤ ከመኖሪያህ ከሰማይ ሆነህ ስማን፤ ይቅርም በለን።

31 “አንድ ሰው ባልንጀራውን መበደሉን የሚገልጥ ክስ ቀርቦበት በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ ወደሚገኘው መሠዊያ አምጥተውት ከበደል ንጹሕ መሆኑን በመሐላ በሚያረጋግጥበት ጊዜ፥

32 በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ለአገልጋዮችህም ፍርድን ስጥ፤ ይኸውም በደል የሠራው ሰው በጥፋቱ መጠን እንዲቀጣ፥ ንጹሑም ነጻ እንዲወጣ አድርግ።

33 “ሕዝብህ እስራኤል በደል ሠርተው አንተን በማሳዘናቸው ምክንያት በጠላቶቻቸው ድል ሲሆኑ ተጸጽተውም ወደ አንተ በመመለስ ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢመጡና የአንተን ይቅርታ ለማግኘት ራሳቸውን ዝቅ አድርገው በትሕትና ቢለምኑህ፥

34 አንተ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ በምርኮ የሚገኙትንም ሕዝብህን ኃጢአት ይቅር በማለት ለቀድሞ አባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸው ምድር መልሰህ አግባቸው።

35 “ሕዝብህ በደል ሠርተው አንተን በማሳዘናቸው ምክንያት ዝናብ እንዳይዘንብላቸው አድርገህ በምትቀጣቸው ጊዜ፥ በፈጸሙት በደል በመጸጸት ፊታቸውን ወደዚህ ቤተ መቅደስ መልሰው በትሕትና ቢለምኑህ፥

36 አንተ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ የአገልጋዮችህን የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ቅን የሆነውንም ነገር ማድረግ ይችሉ ዘንድ አስተምራቸው፤ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሆይ፥ ለዘለዓለም ርስት አድርገህ ለሕዝብህ በሰጠሃቸው በዚህች ምድር ዝናብ እንዲዘንብ አድርግ።

37 “በምድሪቱ ላይ ረሀብ ወይም ቸነፈር በሚመጣበት ጊዜ፥ እንዲሁም በውርጭ በዋግና በአንበጣ ወይ በኩብኩባ መንጋ በሚወድምበት ጊዜ፥ ወይም ጠላቶቻቸው በሕዝብ ላይ አደጋ በሚጥሉበት ጊዜ፥ ወይም በሕዝብህ ላይ ልዩ በሽታና ደዌ በሚደርስባቸው ጊዜ፥

38 ጸሎታቸውን ስማ፤ በሕዝብህ በእስራኤል መካከል ልብን የሚያሸብር መራር ሐዘን ደርሶባቸው እጃቸውን ወደዚህ ቤተ መቅደስ በመዘርጋት በሚጸልዩበት ጊዜ፥

39 ጸሎታቸውን ስማ፤ በምትኖርበት በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን በመስማት በደላቸውን ይቅር በላቸው፤ ርዳቸውም፤ በሰው ልብና አእምሮ ያለውን ሐሳብ ሁሉ መርምረህ የምታውቅ አንተ ብቻ ነህ፤ ስለዚህ ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን የሚገባውን ዋጋ ስጠው፤

40 በዚህም ዐይነት ሕዝብህ ለቀድሞ አባቶቻችን ርስት አድርገህ በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ለአንተ ታዛዦች እንዲሆኑና እንዲያከብሩህ አድርግ።

41-42 “በሩቅ አገር የሚኖር የውጪ አገር ሰው የስምህን ገናናነትና ለሕዝብህ ያደረግኸውን ድንቅ ነገር ሁሉ ሰምቶ፥ በዚህ ቤተ መቅደስ ሊያመልክህና ሊጸልይ ቢመጣ፥

43 አንተ ጸሎቱን ስማ፤ ሕዝብህ እስራኤላውያን እንደሚያደርጉት በመላው ዓለም የሚኖሩ ሕዝቦች አንተን በማወቅ እንዲታዘዙህና እንዲያከብሩህ አድርግ፥ በምትኖርበት በሰማይ ሆነህ የዚህን ሰው ጸሎት ስማ፤ እንድታደርግለት የሚለምንህንም ሁሉ ፈጽምለት፤ ይህም በሚሆንበት ጊዜ ይህ እኔ የሠራሁት ቤተ መቅደስ የአንተ ስም የሚጠራበት መሆኑን ያውቃሉ።

44 “ጠላቶቻቸውን ለመውጋት እንዲዘምቱ ሕዝብህን በምታዝበት ጊዜ በየትኛውም ስፍራ ሆነው ወደዚህች ወደ መረጥኻት ከተማና እኔ ለአንተ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው በሚጸልዩበት ጊዜ፥

45 በሰማይም ሆነህ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በመስማት ዓላማቸውን ደግፍ።

46 “መቼም በደል የማይሠራ የለምና ሕዝብህ ኃጢአት በመሥራት አንተን ሲያሳዝኑህ፥ አንተም ተቈጥተህ ጠላቶቻቸው ድል እንዲነሡአቸውና ወደ ሌላ አገር ማርከው እንዲወስዱአቸው በምትፈቅድበት ጊዜ፥ ምንም እንኳ ያ አገር ሩቅ ቢሆን፥

47 ምርኮኞች ሆነው በሚኖሩባት በዚያች አገር ሳሉ ‘ኃጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ዐምፀናልም’ ብለው በመናዘዝ ተጸጽተው ንስሓ ቢገቡ፥

48 ማርከው በወሰዱአቸው በጠላቶቻቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸው በእውነትና በቅን መንፈስ ተጸጽተው ንስሓ በመግባት አንተ ለቀድሞ አባቶቻችን ወደ ሰጠሃቸው ወደዚህች ምድር፥ አንተም ወደ መረጥኻት ወደዚህች ከተማና እኔ ለአንተ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ቢጸልዩ፥

49 በመኖሪያህ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን በመስማት ፍረድላቸው፤

50 ኃጢአታቸውንና አንተን ያሳዘኑበትን ዐመፅ ሁሉ ይቅር በል፤ ጠላቶቻቸውም እንዲራሩላቸው አድርግ፤

51 እነርሱ እኮ እንደ እቶን እሳት ከምታቃጥል ከግብጽ ምድር ያወጣሃቸው ሕዝብህ ናቸው።

52 “በጠሩህ ጊዜ ሁሉ ትሰማቸው ዘንድ ለአገልጋይህና ለሕዝብህ ልመና ዐይኖችህ የተገለጡ ይሁኑ።

53 እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! የቀድሞ አባቶቻችንን ከግብጽ ምድር ባወጣህ ጊዜ ከዓለም ሕዝብ ሁሉ መካከል እስራኤልን የራስህ ሕዝብ እንዲሆን የመረጥከው መሆኑን በአገልጋይህ በሙሴ አማካይነት ተናግረሃል።”


የጸሎቱ መደምደሚያ

54 ሰሎሞን ጸሎቱን ከፈጸመ በኋላ እጆቹን እንደ ዘረጋ ተንበርክኮ ከነበረበት መሠዊያ ፊት ተነሥቶ ቆመ።

55 ድምፁንም ከፍ በማድረግ በዚያ ተሰብስቦ በነበረው ሕዝብ ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር በረከት እንዲወርድ እንዲህ ሲል ጸለየ፤

56 “በገባው የተስፋ ቃል መሠረት ለሕዝቡ ሰላምን የሰጠ እግዚአብሔር ይመስገን፤ በአገልጋዩ በሙሴ አማካይነት ከሰጠውም መልካም ተስፋ ምንም የቀረ የለም።

57 አምላካችን እግዚአብሔር ከቀድሞ አባቶቻችን ጋር እንደ ነበረ ሁሉ ከእኛ ጋርም ይኑር፤ ምንጊዜም፤ አይተወንም፤ አይጥለንም፤

58 ለቀድሞ አባቶቻችን የሰጠውን ትእዛዞች፥ ደንቦችና ሥርዓቶችን በመጠበቅ እንደ እርሱ ፈቃድ መኖር እንድንችል ለእርሱ ታዛዦች እንድንሆን ያድርገን።

59 የእኔ ያገልጋዩና የሕዝቡ የእስራኤል የየዕለት ፍላጎት ይሟላ ዘንድ እነዚህ ለእግዚአብሔር ያቀረብኳቸው ልመናዎች ቀንና ሌሊት ወደ እግዚአብሔር አምላክ ይቅረቡ።

60 በዚህ ዐይነት የዓለም ሕዝቦች ሁሉ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ መሆኑንና ያለ እርሱም ሌላ አምላክ አለመኖሩን ያውቃሉ፤

61 በዛሬው ቀን እንዳደረጋችሁት በድንጋጌው ትኖሩና ትእዛዞቹንም ታከብሩ ዘንድ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ታማኞች ሁኑ።”


የቤተ መቅደሱ መመረቅ
( 2ዜ.መ. 7፥4-10 )

62 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞንና ከእርሱ ጋር እስራኤላውያን ሁሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ፤

63 ሰሎሞንም ኻያ ሁለት ሺህ የቀንድ ከብቶችንና አንድ መቶ ኻያ ሺህ በጎችን የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ በዚህም ዐይነት ንጉሥ ሰሎሞንና እስራኤላውያን ሁሉ ቤተ መቅደሱ ለእግዚአብሔር የተለየ እንዲሆን አደረጉ።

64 እንዲሁም በዚያኑ ቀን ከቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ያለውን አደባባይ መካከለኛ ክፍል ለእግዚአብሔር የተለየ እንዲሆን አደረገ፤ ቀጥሎም በሙሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእህል ቊርባንና የኅብረት መሥዋዕት፥ የእንስሶች ስብ ሁሉ ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት ከነሐስ የተሠራው መሠዊያ ይህን ሁሉ መሥዋዕት መያዝ ስለማይችል ነው።

65 በዚያም በቤተ መቅደሱ ሰሎሞንና የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ሰባት ቀን ሙሉ የዳስ በዓል አክብረው ሰነበቱ፤ በስተ ሰሜን ከሐማት መተላለፊያ አንሥቶ በስተ ደቡብ እስከ ግብጽ ድንበር ድረስ ካለው ምድር ሁሉ የመጣው ሕዝብ እጅግ ብዙ ነበር፤

66 በሚቀጥለው ቀን ሰሎሞን ሕዝቡን ሁሉ አሰናበተ፤ ሁሉም ሰሎሞንን መረቁ፤ እግዚአብሔር ለአገልጋዩ ለዳዊትና ለሕዝቡ ለእስራኤል ስለ አደረገው በጎ ነገር ሁሉ ደስ ብሎአቸው ወደየቤታቸው ሄዱ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告