Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ነገሥት 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የናቡቴ የወይን ተክል ቦታ

1 ናቡቴ ተብሎ የሚጠራ አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም በኢይዝራኤል በሚገኘው በንጉሥ አክዓብ ቤተ መንግሥት አጠገብ የራሱ ርስት የሆነ አንድ የወይን ተክል ቦታ ነበረው።

2 አንድ ቀን አክዓብ ናቡቴን “የወይን ተክል ቦታህን ስጠኝ፤ በቤተ መንግሥቴ አጠገብ ስለ ሆነ የአትክልት ቦታ ላደርገው እፈልጋለሁ፤ በምትኩ ከእርሱ የተሻለ የወይን ተክል ቦታ እሰጥሃለሁ፤ ልትሸጠው ብትፈልግም የተሻለ ጥሩ ዋጋ እከፍልሃለሁ” አለው።

3 ናቡቴም “ይህን የወይን ተክል ቦታ የወረስኩት ከቀድሞ አያቶቼ ነው፤ ለአንተ ከመስጠትስ እግዚአብሔር ይጠብቀኝ!” ሲል መለሰለት።

4 አክዓብ፥ የእዝራኤላዊው ናቡቴ “ከአባቶቼ የወረስኩትን ለአንተ አልሰጥህም!” ስላለው በንዴት እየተበሳጨ ወደ ቤቱ ገባ፤ ፊቱንም ወደ ግድግዳ አዙሮ በአልጋው ላይ ተጋደመ፤ ምግብ መብላትም አልፈቀደም።

5 ሚስቱም ኤልዛቤል ወደ እርሱ ቀርባ “እንደዚህ ያበሳጨህ ነገር ምንድን ነው? ስለምንስ ምግብ አትበላም?” ስትል ጠየቀችው።

6 እርሱም “እኔን ያበሳጨኝ ከናቡቴ ያገኘሁት መልስ ነው፤ ይኸውም የእርሱን የወይን ተክል ቦታ እንድገዛ ወይም ከፈለገ ልዋጩን እንድሰጠው ብጠይቀው የወይን ተክል ቦታውን ‘በምንም ዐይነት አልሰጥህም’ ብሎ አናደደኝ” ሲል መለሰላት።

7 ኤልዛቤልም “እንግዲህ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ሆነህ ሳለህ እንደዚህ መሆን ይገባሃልን? ይልቅስ ተነሥ፤ በመደሰትም እህል ውሃ ቅመስ፤ እኔ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ እንድታገኝ አደርጋለሁ!” አለችው።

8 ከዚህም በኋላ እርስዋ ደብዳቤ ጽፋ በአክዓብ ስም ፈርማ የእርሱኑ ማኅተም አተመችበት፤ ደብዳቤውንም ናቡቴ ወደሚኖርባት ወደ ኢይዝራኤል ባለሥልጣኖችና ሽማግሌዎች ላከች።

9 ደብዳቤውም እንዲህ የሚል ነበር፦ “የአንድ ቀን ጾም ዐውጁ፤ ሕዝቡንም በአንድነት ሰብስቡ፤ ለናቡቴም የክብር ቦታ ስጡት፤

10 ‘እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል’ ብለው የሚናገሩ ሁለት የሐሰት ምስክሮችንም አቅርቡ፤ ከዚያም በኋላ ናቡቴን ከከተማው ውጪ አውጥታችሁ በድንጋይ በመውገር ግደሉት።”

11 የኢይዝራኤል ባለሥልጣኖችና ሽማግሌዎችም ኤልዛቤል ያዘዘቻቸውን አደረጉ፤

12 የአንድ ቀን ጾም ዐወጁ፤ ሕዝቡንም በአንድነት ሰበሰቡ፤ ለናቡቴም የክብር ቦታ ሰጡት፤

13 ሁለቱም የሐሰት ምስክሮች ተነሥተው “ናቡቴ እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል” ብለው በሕዝቡ ፊት በሐሰት መሰከሩበት፤ ስለዚህም ከከተማይቱ ውጪ በመውሰድ በድንጋይ ወግረው ገደሉት።

14 “ናቡቴ ተወግሮ ተገድሎአል” የሚል መልእክትም ወደ ኤልዛቤል ላኩ።

15 ኤልዛቤልም መልእክቱን እንደ ተቀበለች ወዲያውኑ አክዓብን “ናቡቴ ሞቶአል፤ በል አሁን ተነሥተህ ሂድና ለአንተ ለመሸጥ እምቢ ያለውን የወይን ተክል ቦታ ርስት አድርገህ ውሰድ” አለችው።

16 አክዓብም የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ ለመውረስ ወዲያውኑ ተነሥቶ ሄደ።

17 ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቲስቢያዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፦

18 “ወደ ሰማርያው ንጉሥ ወደ አክዓብ ሂድ፤ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ በመውረስ ላይ እንዳለ በዚያው ታገኘዋለህ፤

19 እኔ እግዚአብሔር ስለ እርሱ የምለው ይህ ነው ‘ናቡቴን መግደልህ አንሶህ ሀብቱንም ልትወርስበት ነውን?’ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ስፍራ እንዲሁም የአንተን ደም ይልሱታል!’ ”

20 አክዓብ ኤልያስን ባየው ጊዜ “ጠላቴ ሆይ! አገኘኸኝን?” አለው። ኤልያስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አዎ! አግኝቼሃለሁ፤ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ራስህን ለኃጢአት ሸጠሃል፤

21 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይልሃል፦ ‘እነሆ በአንተ ላይ መቅሠፍትን አመጣብሃለሁ፤ አንተን ከፊቴ አስወግዳለሁ፤ ከቤተሰብህም ውስጥ ወንድ የሆነውን ሁሉ ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው አጠፋለሁ።

22 እስራኤልን ወደ ኃጢአት በመምራታችሁ ቊጣዬን ስለ አነሣሣህ ቤተሰብህን እንደ ናባጥ እንደ ንጉሥ ኢዮርብዓም ቤተሰብና እንደ አኪያ ልጅ እንደ ንጉሥ ባዕሻ ቤተሰብ ለማጥፋት የተጋለጠ ይሆናል።

23 ስለ ኤልዛቤልም እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ ሬሳዋን በኢይዝራኤል ከተማ ውስጥ ውሾች ይበሉታል፤

24 ከዘመዶችህ መካከል በከተማው ውስጥ የሚሞተውን ማንኛውንም ሰው ውሾች ይበሉታል፤ በገጠርም በየሜዳው የሚሞተውን ሁሉ አሞራዎች ይበሉታል።’ ”

25 በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር በማድረግ ሁለንተናውን ለኃጢአት አሳልፎ የሸጠ አክዓብን የሚምስል ማንም አልነበረም፤ ይህን ሁሉ ለማድረግ የተገደደው ሚስቱ ኤልዛቤል ወደ ክፋት ስለ መራችው ነው፤

26 አክዓብ ከፈጸመው አሳፋሪ በደል ሁሉ ዋናው ክፍል እስራኤላውያን ወደ ምድረ ርስት በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ከፊታቸው ነቃቅሎ ያባረራቸው አሞራውያን ያደርጉት በነበረው ዐይነት ጣዖት ማምለኩ ነው።

27 ኤልያስ ንግግሩን ከፈጸመ በኋላ አክዓብ ልብሱን በመቅደድና አውልቆ በመጣል ማቅ ለበሰ፤ እህል መቅመስንም እምቢ አለ፤ ማቁንም እንደ ለበሰ ይተኛ ነበር፤ ሲሄድም ከጭንቀቱ ብዛት የተነሣ ፊቱ ጠቊሮ ይታይ ነበር።

28 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ቴስቢያዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

29 “አክዓብ በእኔ ፊት ራሱን እንዴት እንዳዋረደ ተመልክተሃልን? ይህን ስላደረገ በሕይወቱ ሳለ መቅሠፍትን አላመጣበትም፤ የተባለውን መቅሠፍት በአክዓብ ቤተሰብ ላይ የማመጣው በልጁ የሕይወት ዘመን ይሆናል።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告