Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ነገሥት 19 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ኤልያስ በሲና ተራራ

1 ኤልያስ ያደረገውን ሁሉና የበዓልንም ነቢያት በሙሉ በሞት እንዴት እንደ ቀጣ ንጉሥ አክዓብ ለሚስቱ ለኤልዛቤል ነገራት፤

2 ስለዚህ እርስዋ “በእነዚያ ነቢያት ላይ ያደረግኸውን እኔም ነገ ልክ በአሁኑ ሰዓት በአንተ ላይ ሳላደርግብህ ብቀር አማልክት በሞት ይቅሠፉኝ!” ስትል ወደ ኤልያስ የዛቻ መልእክት ላከች።

3 ኤልያስም ስለ ፈራ ሕይወቱን ለማትረፍ ከአገልጋዩ ጋር በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ቤርሳቤህ ከተማ ሄደ። አገልጋዩንም በዚያ ተወው፤

4 ኤልያስ አንድ ቀን ሙሉ በበረሓ ተጓዘ፤ ከዚህ በኋላ ጒዞውን ቆም አድርጎ፥ በአንድ የክትክታ ዛፍ ጥላ ሥር ተቀመጠ፤ ሞቱንም በመመኘት “እግዚአብሔር ሆይ! አሁንስ ይብቃኝ፤ ከቀድሞ አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ!” ሲል ጸለየ።

5 ከዚህ በኋላ በዛፉ ሥር ጋደም እንዳለ እንቅልፍ ወሰደው፤ በድንገትም አንድ መልአክ መጥቶ በመዳሰስ ቀሰቀሰውና “ተነሥ ብላ!” አለው፤

6 ኤልያስም ተነሥቶ ዙሪያውን በተመለከተ ጊዜ በድንጋይ ሙቀት የበሰለ የዳቦ ሙልሙልና አንድ ገንቦ ውሃ በራስጌው ተቀምጦ አየ፤ ከበላና ከጠጣም በኋላ ተመልሶ ተኛ፤

7 የእግዚአብሔርም መልአክ ተመልሶ መጥቶ “የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ስለ ሆነ፥ ተነሥተህ ብላ!” ሲል ዳግመኛ ኤልያስን ቀሰቀሰው፤

8 ኤልያስም ተነሥቶ ምግቡን በላ፥ ውሃውንም ጠጣ፤ ከዚያም ምግብ ባገኘው ኀይል እስከ ተቀደሰው የሲና ተራራ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሙሉ ተጓዘ፤

9 እዚያም እንደ ደረሰ ወደ አንድ ዋሻ ገብቶ እዚያ ዐደረ። በድንገትም እግዚአብሔር “ኤልያስ ሆይ! እዚህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው።

10 ኤልያስም “ሁሉን የምትችል አምላኬ ሆይ! እኔ ለአምላክነትህ በመቅናት ዘወትር አንተን ብቻ አገለግላለሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን ከአንተ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ መሠዊያዎችህንም ሰባብረዋል፤ ነቢያትህንም ሁሉ ገድለዋል፤ እነሆ እኔ ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ እነርሱ ግን እኔንም እንኳ ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ!” ሲል መለሰ።

11 እግዚአብሔርም ኤልያስን “ካለህበት ወጥተህ በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም” አለው፤ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በአጠገቡ አለፈ፤ ብርቱ ነፋስም በፊቱ በመላክ ኰረቶችን ሰነጣጠቀ፤ አለቶችንም ሰባበረ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም፤ ነፋሱም ከቆመ በኋላ ምድሪቱ ተናወጠች፤ እግዚአብሔር ግን በምድሪቱ ነውጥ ውስጥ አልነበረም፤

12 ከምድሪቱም ነውጥ በኋላ እሳት መጣ፤ እግዚአብሔር ግን በእሳት ውስጥ አልነበረም፤ ከእሳቱም በኋላ የሹክሹክታ ድምፅ ተሰማ።

13 ኤልያስ የሹክሹክታውን ድምፅ በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፈነ፤ ወጥቶም በዋሻው መግቢያ በር አጠገብ ቆመ፤ አንድ ድምፅም “ኤልያስ ሆይ! እዚህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው።

14 ኤልያስም “ሁሉን የምትችል አምላኬ ሆይ! እኔ ለአምላክነትህ በመቅናት ዘወትር አንተን ብቻ አገለግላለሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን ከአንተ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ መሠዊያዎችህንም ሰባብረዋል፤ ነቢያትንም ሁሉ ገድለዋል፤ እነሆ እኔ ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ እነርሱ ግን እኔን እንኳ ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ” ሲል መለሰ።

15 እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “በደማስቆ ከተማ አጠገብ ወደሚገኘው በረሓ ተመልሰህ ሂድ፤ እዚያም በደረስህ ጊዜ አዛሄልን ቀብተህ በሶርያ ላይ አንግሠው፤

16 የኒምሺን ልጅ ኢዩንም ቀብተህ በእስራኤል ላይ አንግሠው፤ የአቤል መሖላ ተወላጅ የሆነውን የዮሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕንም ቀብተህ በአንተ እግር ነቢይ እንዲሆን አድርገው።

17 ከአዛሄል እጅ ከመገደል ተርፎ የሚያመልጠውን ማንኛውንም ሰው ኢዩ ይገድለዋል፤ ከኢዩ እጅ የሚያመልጠውንም ኤልሳዕ ይገድለዋል።

18 ይሁን እንጂ ለእኔ ታማኞች የሆኑ፥ ለባዓል ያልሰገዱና ምስሉንም ያልተሳለሙ ሰባት ሺህ ሰዎችን በእስራኤል ምድር በሕይወት እንዲተርፉ አደርጋለሁ።”


የኤልሳዕ መጠራት

19 ኤልያስ ከዚያ ከሄደ በኋላ የዮሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ሁለት በሬዎች ጠምዶ ሲያርስ አገኘው፤ ከእርሱም ጋር በፊቱ በዐሥራ አንድ ጥማድ በሬዎች የሚያርሱ ደቦኞች ነበሩ፤ ኤልሳዕም በመጨረሻው ዐሥራ ሁለተኛ ጥማድ ያርስ ነበር፤ ኤልያስም መጐናጸፊያውን አውልቆ በኤልሳዕ ላይ ደረበለት።

20 በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ በሬዎቹን ትቶ ወደ ኤልያስ በመሮጥ “አባትና እናቴን ስሜ እንድሰናበት ፍቀድልኝ ከዚያም በኋላ እከተልሃለሁ” አለው። ኤልያስም “እሺ፥ ተመልሰህ ሂድ፤ እኔ አልከለክልህም!” ሲል መለሰለት።

21 ከዚህ በኋላ ኤልሳዕ ወደ ጥማድ በሬዎቹ ተመልሶ ዐረዳቸው፤ የተጠመዱበትንም ቀንበር በማንደድ ሥጋቸውን ቀቅሎ ለሰዎቹ አቀረበላቸው፤ እነርሱም በሉ፤ ከዚህ በኋላ ኤልያስን ተከትሎ በመሄድ ረዳቱ ሆነ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告