Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ቆሮንቶስ 15 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የክርስቶስ ከሞት መነሣት

1 አሁን ደግሞ ወንድሞች ሆይ! ያስተማርኳችሁን የወንጌል ቃል ላስታውሳችሁ እፈልጋለሁ፤ ይህም የወንጌል ቃል እናንተ የተቀበላችሁትና ጸንታችሁ የቆማችሁበት ነው።

2 እኔ ያስተማርኳችሁን የወንጌል ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ በእርሱ ትድናላችሁ፤ አለበለዚያ ግን ያመናችሁት በከንቱ ነው።

3 እኔ የተቀበልኩትን በመጀመሪያ ደረጃ ያለውን ነገር ለእናንተ አስተላለፍኩላችሁ፤ ያስተላለፍኩላችሁም ነገር በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈው ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፤

4 ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ከሞት ተነሣ የሚል ነው።

5 እርሱ ለጴጥሮስ ታየ፤ ኋላም ለዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ታየ፤

6 ከአምስት መቶ ለሚበልጡ ተከታዮቹም በአንድ ጊዜ ታያቸው፤ ከእነርሱ አብዛኞቹ እስከ አሁን በሕይወት አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን ሞተዋል።

7 ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ታየ፤ ለሐዋርያትም ሁሉ ታያቸው።

8 በመጨረሻም እንደ ጭንጋፍ ለሆንኩት ለእኔ ደግሞ ታየኝ።

9 እኔ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያሳደድኩ ስለ ሆነ ከሐዋርያት ሁሉ ያነስኩና ሐዋርያም ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነኝ።

10 ነገር ግን እኔ አሁን የሆንኩትን ሆኜ የምገኘው በእግዚአብሔር ጸጋ ነው፤ የተሰጠኝም ጸጋ ያለ ፍሬ አልቀረም፤ እንዲያውም ከሌሎቹ ይበልጥ በሥራ ደክሜአለሁ፤ ነገር ግን ይህን ያደረገው ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም።

11 እንግዲህ እኔም ሆንኩ እነርሱ የምናስተምረው ይህንኑ ነው፤ እናንተም ያመናችሁት ይህንኑ ነው።


የሰዎች ከሞት መነሣት

12 ነገር ግን ክርስቶስ ከሞት እንደ ተነሣ የምናስተምር ከሆነ ከእናንተ አንዳንዶቹ ከሞት መነሣት የለም እንዴት ይላሉ?

13 ከሞት መነሣት ከሌለ ክርስቶስ ከሞት አልተነሣም ማለት ነው፤

14 ክርስቶስ ከሞት ካልተነሣ የእኛም ትምህርት ሆነ የእናንተም እምነት ከንቱ መሆኑ ነው፤

15 ደግሞም እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት አስነሥቶታል ብለን በማስተማራችን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነናል ማለት ነው፤ እንግዲህ የሞቱት ሰዎች ከሞት ካልተነሡ እግዚአብሔር ክርስቶስንም ከሞት አላስነሣውም ማለት ነው።

16 የሞቱት ሰዎች ከሞት ካልተነሡ ክርስቶስም ከሞት አልተነሣም ማለት ነው።

17 ክርስቶስ ከሞት ያልተነሣ ከሆነ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ ገና በኃጢአታችሁ ውስጥ ትኖራላችሁ ማለት ነው፤

18 በክርስቶስ አምነው የሞቱት ጠፍተዋል ማለት ነው፤

19 በክርስቶስ ተስፋ የምናደርገው ለዚህ ዓለም ሕይወት ብቻ ከሆነ ከሰዎች ሁሉ ይበልጥ የሚታዘንልን መሆናችን ነው፤

20 ነገር ግን ክርስቶስ ለሞቱት ከሞት የመነሣት በኲር ሆኖ በእርግጥ ከሞት ተነሥቶአል።

21 ሞት የመጣው በአንዱ ሰው በአዳም ምክንያት እንደ ሆነ ከሞት መነሣትም የሚመጣው በአንዱ ሰው በክርስቶስ ምክንያት ነው።

22 በአዳም ምክንያት ሰው ሁሉ እንደሚሞት እንዲሁም በክርስቶስ ምክንያት ሰው ሁሉ ሕይወትን ያገኛል።

23 ይህም የሚሆነው ለእያንዳንዱ በየተራው ነው፤ ክርስቶስ ከሞት የመነሣት የመጀመሪያው ምሳሌ ነው፤ በኋላም ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ የእርሱ የሆኑት ከሞት ይነሣሉ።

24 ቀጥሎም እርሱ ግዛትንና ሥልጣንን ኀይልንም ሁሉ አጥፍቶ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ በሚያስረክብበት ጊዜ የዓለም ፍጻሜ ይሆናል።

25 እግዚአብሔር ጠላቶቹን ሁሉ በሥልጣኑ ሥር እስኪያደርግለት ድረስ ክርስቶስ መንገሥ ይገባዋል።

26 ተሸንፎ በመጨረሻ የሚደመሰሰው ጠላት ሞት ነው።

27 “እግዚአብሔር ሁሉን ነገር በሥልጣኑ ሥር አድርጎለታል” የሚል ተጽፎአል፤ ነገር ግን “ሁሉ ነገር በሥልጣኑ ሥር ሆኖአል” ሲባል ሁሉን ነገር በሥልጣኑ ሥር ያደረገለትን እግዚአብሔር አብን አይጨምርም።

28 ሁሉ ነገር በክርስቶስ ሥልጣን ሥር ከሆነ በኋላ እግዚአብሔር አብ ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ ወልድ ራሱ ሁሉን ነገር በሥልጣኑ ሥር በአደረገለት በእግዚአብሔር አብ ሥልጣን ሥር ይሆናል።

29 እንግዲህ የሞቱ ሰዎች የማይነሡ ከሆነ ስለ ሞቱ ሰዎች የሚጠመቁ ሁሉ ትርፋቸው ምንድን ነው? የሞቱ ሰዎች ከቶ የማይነሡ ከሆነ ሰዎች በእነርሱ ምትክ ስለምን ይጠመቃሉ?

30 እኛስ ብንሆን በየሰዓቱ ለአደጋ እየተጋለጥን የምንኖረው ለምንድን ነው?

31 ወንድሞች ሆይ! እኔን በየቀኑ ሞት ያጋጥመኛል፤ ይህንንም የምነግራችሁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በእናንተ ላይ ያለኝ ትምክሕት እርግጠኛ ስለ ሆነ ነው።

32 እንደ ሰው አስተሳሰብ እኔ በኤፌሶን ከአራዊት ጋር መታገሌ ጥቅሜ ምንድን ነው? ሙታን ከሞት የማይነሡ ከሆነማ “ነገ ስለምንሞት ኑ እንብላ፤ እንጠጣ” እንደ ተባለው መሆኑ ነው።

33 አትታለሉ፤ “መጥፎ ጓደኛ ጥሩውን ጠባይ ያበላሻል።”

34 ወደ ልቡናችሁ ተመለሱ፤ ኃጢአትም አትሥሩ፤ በእናንተ መካከል አንዳንዶች እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉ። ይህንንም የምለው እንድታፍሩ ብዬ ነው።


ከሞት የተነሣ አካል ሁኔታ

35 አንድ ሰው “የሞቱ ሰዎች የሚነሡት እንዴት ነው? ከሞት ሲነሡ የሚኖራቸው አካልስ ምን ዐይነት ነው?” ብሎ ይጠይቅ ይሆናል፤

36 አንተ ሞኝ! የምትዘራው እህል ካልሞተ ሕይወት አይኖረውም፤

37 አንተ ስትዘራም የስንዴ ዘር ወይም ሌላ እህል ብቻ ትዘራለህ እንጂ በኋላ የሚበቅለውን ተክል አይደለም።

38 እግዚአብሔር ግን ለዘሩ እንደ ፈለገ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም ዘር ልዩ ልዩ አካል ይሰጠዋል።

39 ሥጋ ሁሉ አንድ ዐይነት አይደለም፤ የሰው ሥጋም አንድ ዐይነት ነው፤ የእንስሳ ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው፤ የወፎች ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው፤ የዓሣ ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው።

40 እንዲሁም ሰማያዊ አካል አለ፤ ምድራዊ አካልም አለ፤ ነገር ግን የሰማያዊው አካል ክብር አንድ ዐይነት ነው፤ የምድራዊውም አካል ክብር ሌላ ዐይነት ነው።

41 የፀሐይ ክብር አንድ ዐይነት ነው፤ የጨረቃ ክብር ሌላ ዐይነት ነው፤ የከዋክብትም ክብር ሌላ ዐይነት ነው፤ አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ የተለየ ክብር አለው።

42 ከሞት የሚነሡ ሰዎች ሁኔታ ይህንኑ ይመስላል፤ የሚጠፋ ሟች አካል ሆኖ የተዘራው የማይጠፋ ሕያው አካል ሆኖ ይነሣል።

43 በውርደት የተዘራው በክብር ይነሣል፤ ደካማ ሆኖ የተዘራው ኀይለኛ ሆኖ ይነሣል፤

44 ሥጋዊ አካል ሆኖ የተዘራው መንፈሳዊ አካል ሆኖ ይነሣል። ሥጋዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካልም አለ።

45 ስለዚህ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ፍጡር ሆነ” ተብሎ ተጽፎአል፤ የኋለኛው አዳም ክርስቶስ ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ።

46 ነገር ግን በመጀመሪያ የመጣው ሥጋዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው አይደለም፤ መንፈሳዊው የመጣው ከሥጋዊው በኋላ ነው።

47 የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረው ከመሬት ስለ ሆነ መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው የመጣው ከሰማይ ነው።

48 ከመሬት የሆኑት ከመሬት እንደተፈጠረው ናቸው፤ ከሰማይ የሆኑት ከሰማይ እንደመጣው ናቸው።

49 የምድራዊውን ሰው መልክ እንደምንመስል የሰማያዊውንም ሰው መልክ እንመስላለን።

50 ወንድሞች ሆይ! የምነግራችሁ ይህ ነው፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ እንዲሁም የሚጠፋው ሟች አካል የማይጠፋውን ሕያው አካል አይወርስም።

51 እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ። እኛ ሁላችንም አንሞትም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን።

52 የምንለወጠውም የመጨረሻው እምቢልታ በሚነፋበት ጊዜ እንደ ዐይን ቅጽበት በአንድ ጊዜ ነው። መለከቱ ይነፋል፤ የሞቱትም ሰዎች የማይጠፉ ሕያዋን ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን፤

53 ይህ የሚጠፋው የማይጠፋውን ይህም የሚሞተው የማይሞተውን መልበስ አለበት።

54 ይህ የሚጠፋው የማይጠፋውን ይህም የሚሞተው የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ “ሞት በድል ተዋጠ!” ተብሎ የተጻፈው ይፈጸማል።

55 እንዲሁም፥ “ሞት ሆይ! ድል መንሣትህ የት ነው? ሞት ሆይ! ሰውን የምትጐዳበት ኀይል የት ነው?” ተብሎአል።

56 የሞት መንደፊያ ኀይል ኃጢአት ነው፤ የኃጢአትም ኀይል ሕግ ነው።

57 ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን!

58 ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ፤ ለጌታ ሥራ የምትደክሙት በከንቱ አለመሆኑን ዐውቃችሁ፥ ሳታቋርጡ ዘወትር የጌታን ሥራ ለመሥራት ትጉ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告