1 ዜና መዋዕል 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምከምርኮ የተመለሰው የእስራኤል ሕዝብ 1 የእስራኤል ሕዝብ በየቤተሰቡ ተመዝግቦ ነበር፤ ይህም ታሪክ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ሰፍሮ ይገኛል። የይሁዳ ሕዝብ በሠራው ኃጢአት ምክንያት በመቀጣት ተማርኮ ወደ ባቢሎን ተወስዶ ነበር፤ 2 በየከተማው ወዳለው ይዞታቸው የተመለሱት የመጀመሪያዎቹ ካህናት፥ ሌዋውያን፥ የቤተ መቅደስ አገልጋዮችና ሌሎችም እስራኤላውያን ነበሩ። 3 ከይሁዳ፥ ከብንያም፥ ከኤፍሬምና ከምናሴ ነገድ የሆኑ ሰዎች በኢየሩሳሌም ለመኖር ወደዚያ ሄዱ። 4-6 ከይሁዳ ነገድ በኢየሩሳሌም ለመኖር የሄዱት ስድስት መቶ ዘጠና ቤተሰቦች ነበሩ። የይሁዳ ልጅ የፋሬስ ዘሮች የዖምሪን የልጅ ልጅ የዓሚሁድን ልጅ ዑታይን መሪ አድርገው መረጡ፤ ሌሎቹ የፋሬስ ዘሮች ኢምሪና ባኒ ናቸው። የይሁዳ ልጅ የሼላ ዘሮች በኲሩ ዐሳያን እርሱም ከልጆቹ ጋር የቤተሰቡ አለቃ ነበር። የይሁዳ ልጅ የዛራሕ ዘሮች ይዑኤልን መሪያቸው እንዲሆን አደረጉ። 7-8 ከብንያም ነገድ በኢየሩሳሌም ለመኖር የሄዱት የሚከተሉት ናቸው፦ የሃሰኑአ ልጅ ሆዳውያ፥ የሆዳውያ ልጅ መሹላም፥ የመሹላም ልጅ ሳሉ፥ የይሮሐም ልጅ ዩብነያ፥ የሚክሪ የልጅ ልጅ የዑዚ ልጅ ኤላ፥ የዩብኒያ ልጅ ረዑኤል፥ የረዑኤል ልጅ ሸፋጥያ፥ የሸፋጥያ ልጅ መሹላም። 9 ከብንያም ነገድ በኢየሩሳሌም ለመኖር የሄዱት በአጠቃላይ ዘጠኝ መቶ ኀምሳ ስድስት ቤተሰቦች ነበሩ፤ ከዚህ በላይ የተጠቀሱትም ወንዶች ሁሉ የቤተሰብ አለቆች ነበሩ። በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ካህናት 10-12 በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩት ካህናት የሚከተሉት ናቸው፦ ይዳዕያ፥ ይሆያሪብና ያኪን፤ በቤተ መቅደስ ዋና ባለሥልጣን የሆነው የሒልቂያ ልጅ ዐዛርያስ፤ የእርሱም የቀድሞ አባቶች መሹላም፥ ጻዶቅ፥ መራዮትና አሒጡብ ናቸው። የይሮሐም ልጅ ዐዳያ፤ የእርሱም የቀድሞ አባቶች ፓሽሑር ማልኪያ ናቸው። የዐዲኤል ልጅ ማዕሳይ፤ የእርሱም የቀድሞ አባቶች ያሕዜራ፥ መሹላም፥ መሺሌሚትና ኢሜር ናቸው። 13 የቤተሰብ አለቆች የነበሩት ካህናት በድምሩ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሥልሳ ነበሩ፤ እነዚህ ሁሉ በቤተ መቅደስ ውስጥ ለሚከናወነው ሥራ በቂ ችሎታ ያላቸው ነበሩ። በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ሌዋውያን 14-16 በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩት ሌዋውያን የሚከተሉት ናቸው፦ የሐሹብ ልጅ ሸማዕያ፤ የእርሱም የቀድሞ አባቶች ከመራሪ ጐሣዎች የነበሩት ዓዝሪቃምና ሐሻብያ ናቸው። ባቅባቃር፥ ሔሬሽና ጋላል፤ የሚካ ልጅ ማታንያ፤ የእርሱም የቀድሞ አባቶች ዚክሪና አሳፍ ናቸው። የሸማዕያ ልጅ አብድዩ የእርሱም የቀድሞ አባቶች ጋላልና ይዱታን ናቸው። የነጦፋ ከተማ ይዞታ በነበረው ግዛት ይኖር በነበረው የኤልቃና የልጅ ልጅ የአሳ ልጅ ቤሬክያ። በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ የቤተ መቅደስ ዘበኞች 17 በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ የቤተ መቅደስ ዘበኞች የሚከተሉት ናቸው፦ ሻሉም፥ ዓቁብ፥ ጣልሞን፥ አሒማንና ወንድሞቻቸው፤ የእነርሱም አለቃ ሻሉም ነበር፤ 18 እስከዚያን ጊዜ ድረስ በምሥራቅ በኩል በንጉሥ ቅጽር በር መግቢያ ተመድበው ነበር፤ እነርሱም ቀደም ሲል ወደ ሌዋውያን ሰፈር በሚያስገቡት ቅጽር በሮች ዘብ ይጠብቁ ነበር። 19 የኤቢያሳፍ የልጅ ልጅ የቆሬ ልጅ ሻሉም የቆሬ ጐሣ አባሎች ከሆኑት ከሌሎች ዘመዶቹ ጋር በመሆን የቀድሞ አባቶቻቸው የእግዚአብሔርን ሰፈር ይጠብቁ በነበረው ዐይነት እግዚአብሔር ወደሚመለክበት ድንኳን የሚያስገባውን በር ይጠብቁ ነበር። 20 ቀደም ሲል የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ እነርሱን ይቈጣጠር ነበር፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበር። 21 የመሼሌምያ ልጅ ዘካርያስ እግዚአብሔር ወደሚመለክበት ድንኳን በሚያስገባው በር ዘብ ጠባቂ ነበር። 22 መግቢያ በሮችንና ቅጽር በሮችን ለመጠበቅ የተመረጡ በአጠቃላይ ሁለት መቶ ዐሥራ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም በሚኖሩባቸው መንደሮች መሠረት ተቈጥረው ተመዘገቡ፤ የእነርሱን የቀድሞ አባቶች በዚህ ኀላፊነት የመደቡአቸው ንጉሥ ዳዊትና ነቢዩ ሳሙኤል ነበሩ። 23 እነርሱና ልጆቻቸው የእግዚአብሔር ቅጽር በሮችን መጠበቃቸውን ቀጠሉ። 24 በእያንዳንዱ አቅጣጫ ማለትም በሰሜን፥ በደቡብ፥ በምሥራቅና በምዕራብ በእያንዳንዱም ቅጽር በር ዘበኞች ነበሩ፤ 25 እነዚህን ዘበኞች በመንደሮቻቸው የሚኖሩ ዘመዶቻቸው በየሰባቱ ቀን ተራ እየገቡ መርዳት ነበረባቸው፤ 26 አራቱም ሌዋውያን የዘበኞች አለቆች ሲሆኑ እነርሱም ሙሉ ሥልጣን ያላቸው ነበሩ፤ እንዲሁም በቤተ መቅደሱ ላሉት ክፍሎችና በውስጣቸውም ለሚቀመጡ ዕቃዎች ኀላፊዎች ነበሩ። 27 ቤተ መቅደሱን የመጠበቅና በየማለዳው የቅጽር በሮችን የመክፈት ተግባር የእነርሱ በመሆኑ እነርሱ የሚያድሩት በቤተ መቅደሱ አካባቢ ነበር። ሌሎች ሌዋውያን 28 ሌሎቹ ሌዋውያን በአምልኮ ጊዜ መገልገያ ለሆኑ ንዋያተ ቅድሳት ኀላፊዎች ነበሩ፤ በአገልግሎት ላይ በሚውሉበት ጊዜ እየቈጠሩ አውጥተው፥ አገልግሎታቸው ሲያበቃም እየቈጠሩ መልሰው ያስቀምጡአቸው ነበር። 29 ከእነርሱም አንዳዶች ደግሞ ለሌሎቹ ንዋያተ ቅድሳት፥ ለዱቄቱ፥ ለወይን ጠጁ፥ ለወይራ ዘይቱ፥ ለዕጣንና ለልዩ ልዩ ቅመማቅመም ሁሉ ኀላፊዎች ነበሩ፤ 30 ከካህናቱም ወገኖች አንዳንዶቹ ቅመማቅመሙን የማዋሐዱን ኀላፊነት ወሰዱ። 31 ከቆሬ ጐሣ የሻሉም የበኲር ልጅ የሆነው ማቲትያ የመባውን ኅብስት የማዘጋጀት ኀላፊነት ነበረው፤ 32 የቀዓት ጐሣ አባሎች አንዳንዶቹ ለቤተ መቅደስ የሚሆን ኅብስት በየሰንበቱ የማዘጋጀት ኀላፊነት ነበረባቸው። 33 ሌሎች የሌዋውያን ቤተሰቦች አለቆች መዘምራን ነበሩ፤ እነርሱ ሌት ተቀን የማገልገል ኀላፊነት ስለ ነበረባቸው ከሌሎች አገልግሎቶች ነጻ በመሆን በቤተ መቅደሱ ቅጽር ግቢ በተዘጋጁላቸው ክፍሎች ውስጥ ይኖሩ ነበር። 34 እነዚህ ሁሉ የሌዋውያን ቤተሰቦች አለቆች ነበሩ፤ በየነገዳቸው ዝርዝር መሠረት መሪዎች ሆነው በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር። የንጉሥ ሳኦል የቀድሞ አባቶችና ዘሮች ( 1ዜ.መ. 8፥29-38 ) 35 ይዒኤል የገባዖንን ከተማ ቈርቊሮ በዚያው ኖረ፤ ሚስቱ ማዕካ ተብላ የምትጠራ ስትሆን፥ 36 የበኲር ልጁም ዓብዶን ይባል ነበር፤ ሌሎቹ የእርሱ ወንዶች ልጆች ጹር፥ ቂሽ፥ ባዓል፥ ኔር፥ ናዳብ፥ 37 ገዶር፥ አሕዮ፥ ዘካርያስና የሺምዓ አባት ሚቅሎት ተብለው የሚጠሩት ናቸው፤ 38 ሚቅሎት የሺምዓም አባት ነው እነርሱም በሌሎቹ በወንድሞቻቸው አቅራቢያ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር። 39 ኔር ቂስን ወለደ፤ ቂስ ንጉሥ ሳኦልን ወለደ፤ ሳኦልም ዮናታን፥ ማልኪሹዓ፥ አቢናዳብና ኤሽባዓል ተብለው የሚጠሩትን ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ 40 ዮናታንም መሪባዓልን ወለደ፤ መሪባዓልም ሚካን ወለደ፤ 41 ሚካም ፒቶን፥ ሜሌክ፥ ታሬዓና አሐዝ ተብለው የሚጠሩትን ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ 42 አሐዝም ያዕራን ወለደ፤ ያዕራም ዓሌሜት፥ ዓዝማዌትና ዚምሪ ተብለው የሚጠሩትን ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ ዚምሪም ሞጻን ወለደ፤ 43 ሞጻም ቢንዓን ወለደ፤ ቢንዓም ረፋያን ወለደ፤ ረፋያም ኤልዓሳን ወለደ፤ ኤልዓሳም አጼልን ወለደ። 44 አጼልም ዓዝሪቃም፥ ቦከሩ፥ እስማኤል፥ ሸዓርያ፥ አብድዩና ሐናን ተብለው የሚጠሩትን ስድስት ወንዶች ልጆችን ወለደ። |