1 ዜና መዋዕል 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየይሳኮር ትውልድ 1 ይሳኮር አራት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ቶላዕ፥ ፉዋ፥ ያሹብና ሺምሮን ተብለው የሚጠሩት ናቸው። 2 ቶላዕ ስድስት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ዑዚ፥ ረፋያ፥ ይሪኤል፥ ያሕማይ፥ ዩብሳምና ሸሙኤል ተብለው የሚጠሩት ናቸው፤ እነርሱም የቶላዕ ጐሣ ቤተሰቦች አለቆችና ዝነኛ ወታደሮች ነበሩ፤ በንጉሥ ዳዊት ዘመነ መንግሥት የእነርሱ ዘሮች ብዛት ኻያ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ነበር። 3 ዑዚ፥ ዩዝራሕያ ተብሎ የሚጠራ አንድ ወንድ ልጅ ወለደ፤ ዩዝራሕያና የእርሱ አራት ወንዶች ልጆች ሚካኤል፥ አብድዩ፥ ዮኤልና ዩሺያ የቤተሰብ አለቆች ነበሩ። 4 እነርሱ ብዙ ሚስቶችና ብዙ ልጆች ስለ ነበሩአቸው ዘሮቻቸው ለወታደራዊ አገልግሎት የደረሱ ሠላሳ ስድስት ሺህ ወንዶች ማቅረብ ይችሉ ነበር። 5 ከይሳኮር ነገድ ቤተሰቦች ዕድሜአቸው ለወታደራዊ አገልግሎት የደረሰ ሰማኒያ ሰባት ሺህ ወንዶች መሆናቸው የትውልድ መዝገባቸው ያስረዳል። የብንያምና የዳን ትውልድ 6 ብንያም ሦስት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ቤላዕ፥ ቤኬርና ይዲዕኤል ተብለው የሚጠሩት ናቸው። 7 ቤላዕ አምስት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ኤጽቦን፥ ዑዚ፥ ዑዚኤል፥ ያሪሞትና ዒሪ ተብለው የሚጠሩት ናቸው፤ እነርሱም በጐሣዎቻቸው ውስጥ የቤተሰብ አለቆችና ዝነኛ ወታደሮች ነበሩ፤ ከእነርሱ ተወላጆች መካከል ዕድሜአቸው ለውትድርና አገልግሎት የደረሰ ኻያ ሁለት ሺህ ሠላሳ አራት ወንዶች ነበሩ። 8 ቤኬር ዘጠኝ ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ዘሚራ፥ ዮዓሽ፥ ኤሊዔዘር፥ ኤልዮዔናይ፥ ዖምሪ፥ ይሬሞት፥ አቢያ፥ ዐናቶትና ዓሌሜት ተብለው የሚጠሩ ናቸው። 9 ከተወላጆቻቸው ቤተሰቦች ዕድሜአቸው ለውትድርና አገልግሎት የደረሰ ኻያ ሺህ ሁለት መቶ ወንዶች መሆናቸው መዝገቡ ያስረዳል። 10 ይዲዕኤል፥ ቢልሃን ተብሎ የሚጠራ ወንድ ልጅ ወለደ፤ ቢልሃም ያዑሽ፥ ብንያም፥ ኤሁድ፥ ከናዕና፥ ዜታን፥ ታርሺሽና አሒሻሐር ተብለው የሚጠሩ ሰባት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ 11 እነርሱም በጐሣቸው ውስጥ የቤተሰብ አለቆችና ዝነኛ ወታደሮች ነበሩ፤ የትውልዳቸው ቤተሰቦች ዕድሜአቸው ለውትድርና አገልግሎት የደረሰ ዐሥራ ሰባት ሺህ ሁለት መቶ ወንዶች ነበሩአቸው። 12 ሹፊምና ሑፊምም የአሒር ልጆች ነበሩ፤ ሑሺምም የአሄር ልጅ ነበር። የንፍታሌም ትውልድ 13 ንፍታሌም አራት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ያሐጺኤል፥ ጉኒ፥ ዬጼርና ሻሉም ተብለው የሚጠሩት ናቸው፤ እነርሱም የቢልሃ ዘሮች ነበሩ። የምናሴ ትውልድ 14 ምናሴ ከሶርያዊት ቊባቱ አስሪኤልና ማኪር ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ ማኪርም ገለዓድን ወለደ፤ 15 ማኪር፥ ሑፊምና ሺፊም አንዳንድ ሴት እንዲያገቡ አደረገ፤ ማኪር ማዕካ ተብላ የምትጠራ እኅት ነበረችው፤ ጸሎፍሐድ ተብሎ የሚጠራው የማኪር ሁለተኛ ልጅ ሴቶች ልጆችን ብቻ ወለደ። 16 የማኪር ሚስት ማዕካ ፔሬሽና ሼሬሽ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደች፤ ጴሬሽ የሚል ስም ያወጣችለትም እርስዋ ናት። 17 ኡላም ደግሞ ባዳን ተብሎ የሚጠራ አንድ ልጅ ወለደ፤ እነዚህ ሁሉ የምናሴ የልጅ ልጅ የማኪር ልጅ የገለዓድ ዘሮች ናቸው። 18 የገለዓድ እኅት ሃሞሌኬት ሦስት ወንዶች ልጆችን ወለደች፤ እነርሱም ኢሾድ፥ አቢዔዜርና ማሕላ ተብለው የሚጠሩት ናቸው፤ 19 የሸሚዳዕም ልጆች አሕያን፥ ሼኬም፥ ሊቅሒና አኒዓም ነበሩ። የኤፍሬም ትውልድ 20 ኤፍሬም ሹቴላሕን ወለደ፤ ሹቴላሕም ቤሬድን ወለደ፤ ቤሬድ ታሐትን ወለደ፤ ታሐት ኤልዓዳን ወለደ፤ ኤልዓዳ ታሐትን ወለደ፤ 21 ታሐት ዛባድን ወለደ፤ ዛባድ ሹቴላሕን ወለደ፤ ኤፍሬም ከሹቴላሕ ሌላ ዔዜርና ኤልዓድ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም የጋት ነዋሪዎችን የቀንድ ከብቶች ሲሰርቁ ተይዘው ተገደሉ፤ 22 አባታቸው ኤፍሬም ብዙ ቀን አዝኖላቸው ስለ ነበር ወንድሞቹ ሊያጽናኑት መጡ፤ 23 ከዚህ በኋላ ኤፍሬም ከሚስቱ ጋር ግንኙነት አደረገ፤ እርስዋም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ በቤተሰባቸው ላይ በደረሰው መከራ ምክንያት በሪዓ የሚል ስም አወጣለት። 24 ኤፍሬም፥ ሼኢራ ተብላ የምትጠራ ሴት ልጅ ወለደ፤ እርስዋም የላይኛውንና የታችኛውን ቤትሖሮን፥ እንዲሁም ዑዜንሼኢራ ተብለው የሚጠሩትን ከተማዎች አሠራች። 25 ኤፍሬም፥ ሬፋሕ ተብሎ የሚጠራ ሌላ ወንድ ልጅ ወለደ፤ የሬፋሕም ዘሮች ሬሼፍ፥ ቴላሕ፥ ታሐን፥ 26 ላዕዳን፥ ዓሚሁድ፥ ኤሊሻማዕ፥ 27 ነዌና ኢያሱ ናቸው። 28 የኤፍሬም ዘሮች በሙሉ ወስደው የራሳቸው መኖሪያ ያደረጉት ግዛት ቤትኤልና በዙሪያዋ የሚገኙትን ታናናሽ ከተሞችን ሲሆን፥ በምሥራቅ በኩል እስከ ናዕራን፥ በምዕራብ እስከ ጌዜር፥ እንዲሁም በጌዜር ዙሪያ የሚገኙትን ታናናሽ ከተሞችን ያጠቃልል ነበር፤ እንዲሁም ሴኬምንና ዓያን በዙሪያቸው የሚገኙትንም ታናናሽ ከተሞች ይጨምራል። 29 የምናሴ ዘሮች ቤትሻንን፥ ታዕናክን፥ መጊዶንና ዶርን እንዲሁም በእነርሱ ዙሪያ የሚገኙትን ታናናሽ ከተሞች በቊጥጥራቸው ሥር አድርገው ነበር። እነዚህ ሁሉ የያዕቆብ ልጅ የዮሴፍ ዘሮች ይኖሩባቸው የነበሩ ስፍራዎች ናቸው። የአሴር ትውልድ 30 አሴር አራት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ይምና፥ ይሽዋ፥ ይሽዊና በሪዓ ተብለው የሚጠሩት ናቸው፤ እንዲሁም ሤራሕ ተብላ የምትጠራ አንዲት ሴት ልጅ ወለደ። 31 በሪዓም ሔቤርና ማልኪኤል ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ ማልኪኤል፥ ቢርዛዊ ተብሎ የሚጠራ ልጅ ወለደ። 32 ሔቤር ሦስት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ያፍሌጥ፥ ሾሜርና ሖታም ተብለው የሚጠሩት ናቸው፤ እንዲሁም ሹዓ ተብላ የምትጠራ አንዲት ሴት ልጅ ወለደ። 33 ያፍሌጥም ፓሳክ፥ ቢምሃልና ዓሽዋት ተብለው የሚጠሩ ሦስት ወንዶች ልጆችን ወለደ። 34 የያፍሌት ወንድም የሾሜርም አሒ፥ ሮህጋ፥ የሑባና አራም ተብለው የሚጠሩ ልጆችን ወለደ። 35 የያፍሌጥ ወንድም ሖታምም ጾፋሕ፥ ዩምናዕ፥ ሼሌሽና ዓማል ተብለው የሚጠሩ ወንዶች ልጆችን ወለደ። 36 የጾፋሕ ዘሮች ሱሐ፥ ሐርኔፌር፥ ሹዓል፥ ቤሪ፥ ዩምራ፥ 37 ቤጼር፥ ሆድ፥ ሻማ፥ ሺልሻ፥ ዩትራንና በኤራ ተብለው የሚጠሩት ናቸው። 38 የዬቴር ዘሮች ይፉኔ፥ ፒስፓና አራ ተብለው የሚጠሩት ናቸው፤ 39 የዑላ ዘሮች አራሕ፥ ሐኒኤልና ሪጽያ ተብለው የሚጠሩት ናቸው። 40 እነዚህ ሁሉ የአሴር ዘሮች ናቸው፤ እነርሱም የቤተሰብ አለቆች፥ ዝነኛ ጦረኞችና ምርጥ የሆኑ መሪዎች ነበሩ፤ የአሴር ዘሮች ለውትድርና አገልግሎት ብቁ የሆኑ ኻያ ስድስት ሺህ ወንዶች ነበሩአቸው። |