1 ዜና መዋዕል 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየሮቤል ትውልድ 1 የያዕቆብ የበኲር ልጅ የሆነው የሮቤል ዘሮች ቀጥሎ የተመለከቱት ናቸው፤ (ሮቤል የአባቱን አልጋ ደፍሮ በማርከሱ የብኲርናውን መብት ስላጣ፥ ያ መብት ለዮሴፍ ተሰጥቶ ነበር፤ 2 ይሁን እንጂ ከሁሉም ይበልጥ ብርቱ የሆነና ለነገዶች ሁሉ መሪ የሚሆን ሰው የሚገኝበት የይሁዳ ነገድ ነበር፤) 3 ከያዕቆብ ልጆች በኲር የሆነው ሮቤል አራት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ሐኖክ፥ ፋሉ፥ ሔጽሮንና ካርሚ ተብለው የሚጠሩት ናቸው። 4-6 ከትውልድ እስከ ትውልድ የነበሩት የዮኤል ዘሮች ሸማዕያ፥ ጎግ፥ ሺምዒ፥ ሚካ፥ ረአያ፥ በዓልና፥ በኤራ ናቸው፤ የአሦራውያን ንጉሠ ነገሥት ቲግላት ፐሌሴር የጐሣ መሪ የነበረውን በኤራን ይዞ በምርኮኛነት ወሰደው። 7 የቤተሰብ ስም ዝርዝር ከሚገልጠው መዝገብ በተገኘው መሠረት የሮቤል ነገድ የጐሣ አለቆች የነበሩት ኢዩኤል፥ ዘካርያስና፥ 8 ከዩኤል ጐሣ የሼማዕ የልጅ ልጅ የዓዛዝ ልጅ የሆነው ቤላዕ ናቸው፤ ይህም ጐሣ ይኖር የነበረው በዓሮዔርና ከዚያም በስተሰሜን እስከ ነቦና እስከ ባዓልመዖን ባለው ግዛት ነበር፤ 9 እነርሱም በገለዓድ ምድር ብዙ የከብት መንጋ ስለ ነበራቸው በስተ ምሥራቅ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ተንጣልሎ ያለውን በረሓማ ምድር ሁሉ ያዙ። 10 በንጉሥ ሳኦል ዘመነ መንግሥት የሮቤል ነገድ በሀጋራውያን ላይ አደጋ ጥሎ ሁሉንም በጦርነት ፈጃቸው፤ በገለዓድም ምሥራቃዊ ክፍል ያለውን ርስታቸውን ይዞ የራሱ አደረገ። የጋድ ትውልድ 11 የጋድ ነገድ፥ የሮቤል ነገድ ከሚኖሩበት በስተ ሰሜን ባለው ምድር ይኖሩ ነበር፤ ይህም ምድር በባሳን ውስጥ ሲሆን በስተ ምሥራቅ እስከ ሳለካ ይደርሳል። 12 ኢዩኤል ከሁሉ ለሚበልጠው ጐሣ አባት ሲሆን፥ ሻፋም ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ለሚገኘው ጐሣ አባት ነው፤ ያዕናይና ሻፋጥ በበሳን ይኖሩ ለነበሩት ለሌሎች ጐሣዎች አባቶች ነበሩ፤ 13 የቀሩት የዚህ ነገድ አባሎች ሚካኤል፥ መሹላም፥ ሼባዕ፥ ዮራይ፥ ያዕካን፥ ዚዓና ዔቤር ተብለው በሚጠሩ ሰባት ጐሣዎች የተጠቃለሉ ነበሩ፤ 14 እነርሱም የሑሪ ልጅ የኢቢኃይል ዘሮች ሲሆኑ፥ የቀድሞ አባቶቻቸው አቢኃይል፥ ሑሪ፥ ያሮሐ፥ ገለዓድ፥ ሚካኤል፥ የሺሻይ፥ ያሕዶና ቡዝ ናቸው፤ 15 የጉኒ የልጅ ልጅ የዓብዲኤል ልጅ አሒ የእነዚህ ሁሉ ጐሣዎች አለቃ ነበር፤ 16 እነዚህም ሁሉ በባሳንና በገለዓድ ግዛቶች፥ በዚያም በሚገኙ ታናናሽ ከተሞች እንዲሁም በሳሮን ምድር የግጦሽ ቦታ ባለበት ስፍራ ሁሉ ይኖሩ ነበር። 17 ይህ የቤተሰብን ስም ዝርዝር የያዘ መዝገብ የተዘጋጀው በይሁዳ ንጉሥ ኢዮአታምና በእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ነበር። የምሥራቅ ነገዶች ሠራዊት 18 የሮቤል፥ የጋድና በስተ ምሥራቅ የሚገኘው የምናሴ ነገድ እኩሌታ በጋሻና በሰይፍ እንዲሁም በቀስት ውጊያ በደንብ የሠለጠኑ አርባ አራት ሺህ ሰባት መቶ ሥልሳ ወታደሮች ነበሩአቸው፤ 19 እነርሱም የሀጋራውያን ነገዶች በሆኑት በየጡር፥ በናፊሽና በኖዳብ ሕዝቦች ላይ አደጋ ለመጣል ዘመቱ። 20 እምነታቸውንም በእግዚአብሔር አድርገው እርሱ እንዲረዳቸው ተማጠኑት፤ እግዚአብሔርም ጸሎታቸውን ሰምቶ፥ በሀጋራውያንና በእነርሱም የጦር ጓደኞች ላይ ድልን አጐናጸፋቸው፤ 21 ከጠላትም እጅ ኀምሳ ሺህ ግመሎችን፥ ሁለት መቶ ኀምሳ ሺህ በጎችንና ሁለት ሺህ አህዮችን ማረኩ፤ እንዲሁም አንድ መቶ ሺህ ሰዎችን ምርኮኛ አድርገው ወሰዱ። 22 ጦርነቱ እግዚአብሔር የፈቀደው ስለ ነበረ፥ ከጠላት ወገን ብዙ ሰዎችን ገደሉ፤ እነርሱም ራሳቸው ተማርከው እስከ ተወሰዱበት ጊዜ ድረስ በምድሪቱ ላይ መኖራቸውን ቀጠሉ። በስተ ምሥራቅ ያለው የምናሴ ነገድ 23 በስተ ምሥራቅ ያለው የምናሴ ነገድ እኩሌታ በስተ ሰሜን እስከ ባዓልሔርሞን፤ እስከ ሠኒርና እስከ ሔርሞን ተራራ በሚደርሰው በባሳን ግዛት ውስጥ ይኖሩ ነበር፤ የሕዝባቸውም ቊጥሩ እየበዛ ሄደ፤ 24 የጐሣዎቻቸው አለቆች ዔፌር፥ ዩሽዒ፥ ኤሊኤል፥ ዓዝሪኤል፥ ኤርምያስ፥ ሆዳውያና ያሕዲኤል ናቸው፤ እነዚህ ሁሉ የታወቁ የጐሣ መሪዎችና ጀግኖች ወታደሮች ነበሩ። በምሥራቅ በኩል ያሉት የሁለት ተኩል ነገድ ሕዝብ ተማርከው ተወሰዱ 25 ሕዝቡ ለቀድሞ አባቶቹ አምላክ ታማኝ ሆኖ አልተገኘም፤ እንዲያውም እግዚአብሔርን ትቶ ከምድሪቱ ላይ ላስወገደለት ሕዝብ አማልክት ሰገደ። 26 ስለዚህ እግዚአብሔር ፑል ወይም ቲግላት ፐሌሴር ተብሎ የሚጠራውን የአሦርን ንጉሠ ነገሥት አነሣሥቶ ምድራቸውን እንዲወር አደረገ፤ በዚህ ዐይነት ቲግላት ፐሌሴር የሮቤልን፥ የጋድንና በምሥራቅ በኩል ያለውን የምናሴን ነገድ እኩሌታ ማርኮ በመውሰድ በሐላሕ፥ በሐቦርና በሃራ እንዲሁም በጎዛን ወንዝ ዳርቻ እንዲኖሩ አደረጋቸው እስከ ዛሬም ድረስ በዚያው ይገኛሉ። |