Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ዜና መዋዕል 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የይሁዳ የትውልድ ሐረግ

1 የይሁዳም ዘሮች ፋሬስ፥ ሔጽሮን፥ ካርሚ፥ ሑርና ሾባል ናቸው።

2 ሾባል ረአያን ወለደ፤ ረአያም ያሐትን ወለደ፤ ያሐትም በጾርዓ ለሚኖሩት ሕዝቦች የቀድሞ አባቶች የነበሩትን አሑማይንና ላሃድን ወለደ።

3-4 ሑር የካሌብና የኤፍራታ በኲር ልጅ ነው፤ ከእርሱ ልጆች መካከል በቤተልሔም የሰፈሩ አሉ፤ ሌሎቹም የሑር ልጆች ጰኑኤልና ዔዜር ናቸው፤ የኤታም ወንዶች ልጆች ኤይዝርኤል፥ ኢሻማ፥ ኤድባሽ፥ ጌዶርን የመሠረተው ፋኑኤልና ሑሻን የመሠረተው ኤጼር ሲሆኑ ሐጽሌልጶኒ የምትባል እኅት ነበረቻቸው።

5 የተቆዓን ከተማ የቈረቈረው አሽሑር፥ ሔላና ናዕራ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ሚስቶች ነበሩት፤

6 አሽሑርም ናዕራ ከተባለችው ሚስቱ አሑዛም፥ ሔፌር፥ ቴምኒና አሓሽታሪ ተብለው የሚጠሩ ወንዶች ልጆችን ወለደ፤

7 እንዲሁም ሔላ ከተባለችው ሚስቱ ጼሬት፥ ይጽሐርና፥ ኤትናንና ቆጽ ተብለው የሚጠሩ ወንዶች ልጆችን ወለደ።

8 ቆጽም ዓኑብና ጾቤባ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እንዲሁም ቆጽ የሃሩም ልጅ የአሐርሔል ዘሮች ለሆኑት ጐሣዎች የነገድ አባት ነው።

9 ከቤተሰቡ መካከል እጅግ የተከበረ ያዕቤጽ ተብሎ የሚጠራ አንድ ሰው ነበር፤ እናቱ እርሱን በወለደች ጊዜ ከባድ የምጥ ጣር ደርሶባት ስለ ነበር “ያዕቤጽ” የሚል ስም አወጣችለት፤

10 ያዕቤጽም “አምላኬ ሆይ፥ ባርከኝ፤ ሰፊ ምድርንም ስጠኝ፤ እጅህ ከእኔ ጋር ይሁን፤ ሥቃይ ሊያስከትልብኝ ከሚችል ከማንኛውም ክፉ ነገር ጠብቀኝ” በማለት ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የለመነውን ሰጠው።


ሌሎች ቤተሰቦች

11 የሹሐ ወንድም ከሉብ መሒር ተብሎ የሚጠራ አንድ ወንድ ልጅ ወለደ፤ መሒርም ኤሽቶንን ወለደ፤

12 ኤሽቶንም ቤትራፋ፥ ፋሴሐና ተሒና ተብለው የሚጠሩትን ሦስት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ ተሒናም ናሐሽ ተብላ የምትጠራውን ከተማ ቈረቈረ፤ የእነዚህም ዘሮች ሬካ ተብላ በምትጠራ አገር ይኖሩ ነበር።

13 ቀናዝም ዖትኒኤልና ሠራያ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ ዖትኒኤልም ሐታትና መዖኖታይ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤

14 መዖኖታይ ዖፍራን ወለደ። ሠራያም የእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች የሚኖሩባትን ጌሐራሺም ተብላ የምትጠራውን ከተማ የመሠረተው ኢዮአብን ወለደ፦

15 የይፉኔ ልጅ ካሌብም ዒሩ፥ ኤላና ናዓም ተብለው የሚጠሩ ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ ኤላም ቀናዝን ወለደ።

16 ይሃልኤልም ዚፍ፥ ዚፋ፥ ቲረያና አሳርኤል ተብለው የሚጠሩ ወንዶች ልጆችን ወለደ።

17-18 ዔዝራም ዬቴር፥ ሜሬድ፥ ዔፌርና ያሎን ተብለው የሚጠሩ ወንዶች ልጆችን ወለደ። ሜሬድም ቢትያ የተባለችውን የግብጽን ንጉሥ ልጅ አግብቶ ማርያም ተብላ የምትጠራውን ሴት ልጅና ሻማይና ዩሽባሕ ተብለው የሚጠሩትን ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ ዩሽባሕም ኤሽተሞዓ ተብላ የምትጠራውን ከተማ ቈረቈረ፤ ሜሬድም ከይሁዳ ነገድ አንዲት ሴት አግብቶ የገዶርን ከተማ የቈረቈረውን ዬሬድን፥ የሶኮን ከተማ የቈረቈረውን ሔቤርንና፥ የዛኖሐን ከተማ የቈረቈረውን የቂቲኤልን ወለደ።

19 ሆድያም የናሐምን እኅት አገባ፤ የእነርሱም ዘሮች በቀዒላ ከተማ ይኖሩ ለነበሩት ለጋርሚ ጐሣዎችና በኤሽተሞዓ ከተማ ይኖሩ ለነበሩት ለማዕካት ጐሣዎች አባቶች ሆኑ።

20 ሺሞንም አምኖን፥ ሪና፥ ቤንሐናንና ቲሎን ተብለው የሚጠሩ ወንዶች ልጆችን ወለደ። ዩሽዒም ዞሔትና ቤንዞሔት ተብለው የሚጠሩትን ወንዶች ልጆች ወለደ።


የሼላ ትውልድ

21 ሼላ ከይሁዳ ወንዶች ልጆች አንዱ ሲሆን ዘሮቹም የሌካን ከተማ የቈረቈረው ዔር፥ የማሬሻን ከተማ የቈረቈረው ላዕዳ፥ የቤት አሽቤዓ ከተማ ነዋሪዎች የሆኑት የበፍታ ጨርቅ ሠሪዎች ጐሣ፥

22 ዮቂምና በኮዜባ ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ ሞአባውያን ሴቶችን አግብተው በቤተልሔም ሰፍረው የነበሩት ኢዮአስና ሳራፍ ናቸው፤ (ይህ የቤተሰብ መዝገብ ጥንታዊ ነው፤)

23 እነርሱም የቤተ መንግሥት ሸክላ ሠራተኞች ሆነው ነጣዒምና ገዴራ ተብለው በሚጠሩ ከተሞች ይኖሩ ነበር።


የስምዖን ትውልድ

24 ስምዖን፥ ነሙኤል፥ ያሚን፥ ያሪብ፥ ዜራሕና ሻኡል ተብለው የሚጠሩ ወንዶች ልጆችን ወለደ፤

25 ሻኡልም፥ ሻሉምን ወለደ፤ ሻሉምም ሚብሳምን ወለደ፤ ሚብሳምም ሚሽማዕን ወለደ፤

26 ሚሽማዕ ሔሙኤልን፥ ሐሙኤልም ዛኩርን፥ ዛኩር ሺምዒን ወለደ፤

27 ሺምዒ፥ ዐሥራ ስድስት ወንዶችና ስድስት ሴቶች ልጆችን ወለደ፤ ወንድሞቹ ግን ብዙ ልጆች አልወለዱም፤ ስለዚህም የስምዖን ነገድ የይሁዳን ነገድ ያኽል አልበዛም።

28 እስከ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ድረስ የስምዖን ዘሮች በሚከተሉት ከተሞች ይኖሩ ነበር፦ ቤርሳቤህ፥ ሞላዳ፥ ሐጻርሹዓል፥

29 ቢልሃ፥ ዔጼም፥ ቶላድ፥

30 በቱኤል፥ ሖርማ፥ ጺቅላግ፥

31 ቤትማርካቦት፥ ሖጻር ሱሲም፥ ቤትቢሪና ሻዕራይም፤

32 እንዲሁም ዔጣም፥ ዓይን፥ ሪሞን፥ ቶኬንና ዐሻን ተብለው በሚጠሩ በሌሎች አምስት ታናናሽ ከተሞችና፥

33 በአካባቢያቸው በሚገኙ መንደሮች ይኖሩ ነበር፤ ይህም እነርሱ የሚኖሩበት ስፍራ እስከ ባዕላት ከተማ ይዘልቅ ነበር። እንግዲህ የስምዖን ዘሮች ስለ ቤተሰቦቻቸውና ስለሚኖሩባቸው ስፍራዎች መዝግበው ያቈዩት ጽሑፍ ይህ ነበር።

34 የየጐሣ አለቆቻቸውም ከዚህ በታች የተመለከቱት ናቸው፦ መሾባብ፥ ያምሌክ፥ የአሜስያስ ልጅ ዮሻ፥

35 ዮኤል፥ የዮሺብያ ልጅ ኢዩ፥ (የሠራያ ልጅ ዮሺብያ፥ የአሰኤል ልጅ ሠራያ፥)

36 ኤልዮዔናይ፥ ያዕቆባ፥ የሾሐያ፥ ዐሳያ፥ ዐዲኤል፥ የሺሚኤል በናያ፥

37 የሺፍዒ ልጅ ዚዛ፥ የየዳያ የሺምሪና የሸማዕያ ዘር የሆነው የአሎን ልጅ ሺፍዒ።

38 የእነዚህም ቤተሰብ እየበዛ ሄደ፤

39 እስከ ገራር ድረስ ተሠራጩ፤ በሸለቆው በስተ ምሥራቅ በኩል ከተማይቱ በምትገኝበት ስፍራም በጎቻቸውን ያሰማሩ ነበር፤

40 በዚያም ጸጥታና ሰላም በሰፈነበት ገላጣማ አገር ለም የሆነ የግጦሽ ቦታ በብዛት አገኙ፤ ቀደም ሲል በዚያ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች ከካም ዘሮች ነበሩ።

41 በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት ከላይ የተጠቀሱት ሰዎች ወደ ገራር ሄደው በዚያ የሚኖሩትን ሰዎች ድንኳንና ጎጆ ሁሉ አፈራረሱ፤ የካምን ነገዶችና መዑናውያንንም ፈጽመው ፈጁአቸው ለበጎቻቸው ብዙ የግጦሽ ቦታ ስላገኙም ሕዝቡን አባረው ለዘለቄታው እዚያው መኖር ጀመሩ።

42 ከስምዖን ዘሮች አምስት መቶ የሚሆኑት ወደ ኤዶም ተራራ ሄዱ፤ እነርሱም ይመሩ የነበሩት በዩሽዒ ልጆች በፐላጥያ፥ በነዓርያ፥ በረፋያና በዑዚኤል ነበር፤

43 እነርሱም በዚያ ቀርተው የነበሩትን ዐማሌቃውያንን ፈጁ፤ ከዚያን ጊዜም አንሥቶ በዚያ መኖር ጀመሩ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告