Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ዜና መዋዕል 29 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የቀረበ ልዩ ልዩ ስጦታ

1 ንጉሥ ዳዊት ለመላው ጉባኤ እንዲህ ሲል አስታወቀ፤ “እነሆ እግዚአብሔር የመረጠው ልጄ ሰሎሞን ገና ወጣትና የሥራ ልምድ የሌለው ነው፤ ይህ የሚሠራው ቤት፥ ቤተ መንግሥት ሳይሆን እግዚአብሔር አምላካችን የሚመለክበት ቤተ መቅደስ ስለ ሆነ መከናወን ያለበት ሥራ እጅግ ከባድ ነው።

2 የምችለውን ያኽል፥ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ የሚሆኑትን ዕቃዎች ወርቅ ለወርቅ ሥራ፥ ብር ለብር ሥራ፥ ነሐስ ለነሐስ ሥራ፥ ብረት ለብረት ሥራ፥ እንጨት ለእንጨት ሥራ መርግድና የተለያዩ ቀለማት ያላቸው በፈርጥ የሚገቡ ድንጋዮች፥ የከበረ ድንጋይና በየዐይነቱ ብዙ ዕብነ በረድ አዘጋጅቼአለሁ።

3 ከእነዚህ ካዘጋጀኋቸው ነገሮች ሁሉ በላይ እኔ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ካለኝ ታላቅ ፍቅር የተነሣ ከራሴ ንብረት ብዙ ብርና ወርቅ ሰጥቼአለሁ፤

4 በዚህ መሠረት መቶ ሺህ ኪሎ የኦፊር ወርቅና ሁለት መቶ አርባ ሺህ ኪሎ የሚሆን ንጹሕ ብር የቤተ መቅደሱን ግንቦች ለማስጌጥና፥

5 የእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች ለሚሠሩአቸው ዕቃዎች መሥሪያ የሚውል ሰጥቼአለሁ፤ ከእናንተስ መካከል በፈቃዱ ለእግዚአብሔር በልግሥና የሚሰጥ ሌላ ማን አለ?”

6 ከዚህ በኋላ የጐሣ አለቆች፥ የየነገዱ መሪዎች፥ የሺህ አለቆችና የመቶ አለቆች የመንግሥት ባለሥልጣኖች በፈቃዳቸው ስጦታ ሰጡ።

7 ከመቶ ሰባ ሺህ ኪሎ የሚበልጥ ወርቅ፥ ከሦስት መቶ አርባ ሺህ ኪሎ በላይ የሚሆን ብር፥ ወደ ስድስት መቶ ኻያ ሺህ ኪሎ የሚጠጋ ነሐስና ከሦስት ሚሊዮን አራት መቶ ሺህ ኪሎ በላይ የሆነ ብረት በፈቃዳቸው ለመስጠት ወሰኑ፤

8 የከበረ ድንጋይ የነበራቸው ሁሉ የሌዋዊው የጌርሾን ጐሣ አባል የሆነው ይሒኤል ለሚያስተዳድረው ለቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት በስጦታ ስም አቀረቡ፤

9 ሕዝቡ በፈቃዳቸውና በሙሉ ልብ ሁሉ ለእግዚአብሔር ሰጡ፤ እጅግ ብዙ ሀብት ገቢ በመሆኑም ደስ አላቸው፤ ንጉሥ ዳዊትም ከመጠን በላይ ደስ ተሰኘ።


ዳዊት እግዚአብሔርን አመሰገነ

10 እዚያም በመላው ጉባኤ ፊት ንጉሥ ዳዊት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ እንዲህም አለ፦ “የቀድሞ አባታችን የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገንክ ሁን!

11 አንተ ታላቅና ኀያል ነህ፤ በክብር፥ በውበትና በግርማም የተሞላህ ነህ፤ በሰማይና በምድር ያለው ነገር ሁሉ የአንተ ነው፤ አንተ ከሁሉ በላይ ከፍ ያልክና በሁሉም ላይ ሥልጣን ያለህ ንጉሥ ነህ፤

12 ብልጽግናና ክብር ሁሉ የሚገኘው ከአንተ ነው፤ አንተ ሁሉን ትገዛለህ፤ ኀይልና ብርታት ያንተ ናቸው፤ የወደድከውንም ታላቅና ብርቱ ማድረግ ይቻልሃል።

13 አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ምስጋና እናቀርብልሃለን፤ ክቡር ስምህንም እናወድሳለን።

14 “ይህን ስጦታ በፈቃደኛነት መስጠት እንችል ዘንድ እኔ ማነኝ? ሕዝቤስ ማነው? ሁሉ ነገር ከአንተ የተቀበልነው ስጦታ ነው፤ እነሆ የአንተ የነበረውንም መልሰን ሰጥተንሃል፤

15 እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ቀድሞ አባቶቻችን እኛም በአንተ ፊት እንግዶችና መጻተኞች ነን፤ በምድር ላይ ያለው ዘመናችን ተስፋ የሌለው እንደ ጥላ ነው።

16 አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህን ሁሉ ሀብት የሰበሰብነው ለቅዱስ ስምህ ክብር ቤተ መቅደስ ለመሥራት ነው፤ ይሁን እንጂ ሁሉም የተገኘው ከአንተ ነው፤ ሁሉም የአንተ ነው፤

17 አንተ የሰውን ሁሉ ልብ ፈትነህ፥ ታማኝ በሆነ ሕዝብ እንደምትደሰት ዐውቃለሁ፤ ስለዚህም እኔ ይህን ሁሉ በፈቃዴ ለአንተ የሰጠሁት፥ በታማኝነትና በቅንነት ነው፤ ደግሞም እዚህ የተሰበሰበው ሕዝብህ ለአንተ ስጦታ በማቅረቡ፥ እጅግ መደሰቱን ተገንዝቤአለሁ፤

18 የቀድሞ አባቶቻችን የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህ ታላቅ ፍቅር በሕዝብህ በእስራኤላውያን ልብ ለዘለዓለም ጸንቶ እንዲኖር አድርግ፤ ዘወትርም ለአንተ ታማኞች እንዲሆኑ አድርጋቸው፤

19 አንተ የምታዘውን፥ ትእዛዞችህን ደንቦችህንና ድንጋጌዎችህን ሁሉ እንዲፈጽምና ይህን ሁሉ ዝግጅት ያደረግኹለትን ቤተ መቅደስ እንዲሠራ ለልጄ ለሰሎሞን ከሙሉ ልብ የመነጨ ፈቃደኛነትን ስጠው።”

20 ከዚህ በኋላ ዳዊት ሕዝቡን “አምላካችሁን እግዚአብሔርን አመስግኑ!” አለ፤ መላው ጉባኤም የቀድሞ አባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ወደ መሬት ለጥ ብለውም ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ ለንጉሡም ክብር ሰጡ።

21 በማግስቱ ብዙ እንስሶችን ዐርደው ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ፤ ከዚያም በኋላ ሕዝቡ እንዲመገቡ ሰጡአቸው፤ በተጨማሪም አንድ ሺህ ኰርማዎችን፥ አንድ ሺህ የበግ አውራዎችንና አንድ ሺህ የበግ ጥቦቶችን መሥዋዕት አድርገው በማረድ ሙሉ በሙሉ በመሠዊያው ላይ አቃጠሉአቸው፤ የወይን ጠጅ መባም አቀረቡ፤

22 ስለዚህ በዚያን ቀን በእግዚአብሔር ፊት እየበሉና እየጠጡ እጅግ ደስ ተሰኙ። ለሁለተኛ ጊዜም ሰሎሞን ንጉሥ መሆኑን አረጋገጡ፤ በእግዚአብሔር ስም ቀብተው ንጉሣቸው አደረጉት፤ ሳዶቅንም ቀብተው ካህናቸው አደረጉት፤

23 በዚህ ዐይነት ሰሎሞን በአባቱ እግር ተተክቶ እግዚአብሔር ባጸናው ዙፋን ላይ ተቀመጠ፤ እርሱም ሁሉ ነገር የተሳካለት ንጉሥ ሆነ፤ መላውም የእስራኤል ሕዝብ ታዘዙለት፤

24 ባለሥልጣኖችና ወታደሮች ሁሉ ሌሎቹ የዳዊት ልጆች እንኳ ሳይቀሩ ለንጉሥ ሰሎሞን ታማኝ ዜጎች እንደሚሆኑ ቃል ገቡ።

25 እግዚአብሔር በአገሪቱ ሕዝብ ሁሉ ፊት ሰሎሞንን ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከዚህ በፊት እስራኤልን ከገዛ ከማንኛውም ንጉሥ ይበልጥ የተከበረ እንዲሆንም አደረገው።


የዳዊት ዘመነ መንግሥት ታሪክ ባጭሩ

26 የእሴይ ልጅ ዳዊት መላው እስራኤልን ገዛ፤

27 የግዛቱም ዘመን አርባ ዓመት ሲሆን በኬብሮን ሰባት ዓመት፥ በኢየሩሳሌም ደግሞ ሠላሳ ሦስት ዓመት ገዛ፤

28 ብዙ ሀብትና ክብር ካገኘም በኋላ በዕድሜ እጅግ ሸምግሎ ሞተ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ሰሎሞን ነገሠ፤

29 ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለው የንጉሥ ዳዊት ታሪክ ሳሙኤል፥ ናታንና ጋድ ተብለው በሚጠሩት ሦስት ነቢያት በጻፉአቸው የታሪክ መጻሕፍት ተመዝግቦ ይገኛል፤

30 ዳዊት እንዴት እንዳስተዳደረ፥ ምን ያኽል ኀይል እንደ ነበረውና በእርሱ፥ በእስራኤልና በዙሪያ ባሉት ነገሥታት ላይ ስለ ደረሰባቸው ነገር ሁሉ በእነዚሁ መጻሕፍት ተመዝግቦ ይገኛል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告