Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ዜና መዋዕል 28 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ዳዊት ስለ ቤተ መቅደሱ ሥራ የሰጠው መመሪያ

1 ንጉሥ ዳዊት የእስራኤል ባለ ሥልጣኖች በሙሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው እንዲሰበሰቡ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ስለዚህ የየነገዱ መሪዎች፥ የመንግሥቱን ሥራ የሚያካሂዱ ባለሥልጣኖች የሻአለቆችና የመቶ አለቆች፥ የንጉሡንና የወንዶች ልጆቹን ንብረትና የቀንድ ከብት ተቈጣጣሪዎች እንዲሁም የቤተ መንግሥት ባለሟሎች፥ ዝነኞችና ታዋቂ የሆኑ ጀግኖች ሰዎች በሙሉ በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ።

2 ሁሉም በተሰበሰቡ ጊዜ ዳዊት ተነሥቶ፥ እንዲህ አለ፦ “ወገኖቼ ሆይ፥ አድምጡኝ፤ ለአምላካችን የእግር ማሳረፊያ ይሆን ዘንድ የተቀደሰው ታቦት የሚያርፍበት ቤት ለመሥራት ፈልጌ ነበር፤ ለቤተ መቅደሱም ሕንጻ ማሠሪያ የሚሆነውን ዕቃ ሁሉ አዘጋጅቼአለሁ፤

3 ነገር ግን እኔ በጦርነት ብዙ ደም በማፍሰሴ ቤተ መቅደሱን እንድሠራለት እግዚአብሔር አልፈቀደልኝም፤

4 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፥ ይሁዳን በእስራኤል ላይ መሪ ነገድ አድርጎ መርጦታል፤ ከይሁዳም የእኔን ቤተሰብ፥ ከእኔም ቤተሰብ እኔን የእስራኤል ንጉሥ እንድሆን መረጠኝ፤ የእኔም ዘሮች ነገሥታት ሆነው እንደሚያስተዳድሩ ቃል ገብቶልኛል።

5 ለእኔም ብዙ ወንዶች ልጆችን ሰጠኝ፤ ነገር ግን የሚቀጥለው የእስራኤል ንጉሥ ይሆን ዘንድ የመረጠው ልጄን ሰሎሞንን ነው።”

6 እግዚአብሔርም “ ‘ቤተ መቅደሴንና አደባባዮቼን የሚሠራልኝ ልጅህ ሰሎሞን ነው፤ እርሱ እንደ ልጄ ይሆናል፤ እኔም እንደ አባት እሆነዋለሁ’ ብሎኛል።

7 ‘እርሱ አሁን በሚያደርገው ዐይነት ዘወትር ሕጎቼንና ትእዛዞቼን በጥንቃቄ የሚፈጽም ከሆነ፥ መንግሥቱን ለዘለዓለም አጸናለታለሁ’ ብሎአል።

8 “አሁንም ሕዝቤ ሆይ፥ በእግዚአብሔርና የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆነው በዚህ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት አምላካችን እግዚአብሔር ያዘዘንን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ትፈጽሙ ዘንድ ዐደራ እላችኋለሁ፤ ይህን ብታደርጉ ይህችን መልካም ምድር ለዘለቄታው ርስታችሁ ታደርጋላችሁ፤ ወደፊት ለሚመጡትም ለልጅ ልጆቻችሁ ማስተላለፍ ትችላላችሁ።”

9 ዳዊት ሰሎሞንንም እንዲህ አለው፤ “ልጄ ሆይ፥ የአባትህን አምላክ እንድታውቅ፥ በሙሉ ልብና በፈቃደኛ አእምሮ እንድታገለግለው ዐደራ እልሃለሁ፤ እርሱ ሐሳባችንንና ምኞታችንን ሁሉ ያውቃል፤ ወደ እርሱ ብትቀርብ እርሱም ወደ አንተ ይቀርባል፤ ብትተወው ግን እርሱም ለዘለዓለም ይተውሃል፤

10 ቤተ መቅደሱን ትሠራለት ዘንድ እግዚአብሔር አንተን እንደ መረጠህ አትዘንጋ፤ አሁንም በርትተህ በቈራጥነት ሥራው።”

11 ዳዊት ለልጁ ለሰሎሞን የቤተ መቅደሱን የዕቃ ግምጃ ቤቶቹን፥ በደርቡና በምድር ቤቱ የሚገኙትን ክፍሎችና ኃጢአት የሚሰረይበትን የቅድስተ ቅዱሳኑን አሠራር የሚገልጥ ዕቅድ ሰጠው።

12 ለአደባባዮቹና በዙሪያቸው ላሉት ክፍሎች፥ ለቤተ መቅደሱ ዕቃና ለእግዚአብሔር ለሚቀርቡ መባዎች የዕቃ ግምጃ ቤት በሐሳቡ የነበረውን ሁሉ የአሠራር ዕቅድ ጨምሮ ሰጠው።

13 እንዲሁም ዳዊት ስለ ካህናትና ሌዋውያን የተለያየ የሥራ ድርሻ፥ በቤተ መቅደሱ ስለሚከናወኑት ተግባሮችና እግዚአብሔርን ለማምለክ አገልግሎት መጠቀሚያ ለሆኑት ዕቃዎች ለሚደረገው እንክብካቤ ዕቅድ ለሰሎሞን ሰጠው።

14 ለተለያዩ የአገልግሎት ዐይነቶች መጠቀሚያ የሚሆኑትን ዕቃዎች መሥሪያ እንዲሆኑ የብሩንና የወርቁን መጠን በሚዛን ወሰነ።

15 ለያንዳንዱ መቅረዝና መብራት የሚሆን ወርቅ፥ እንዲሁም ለመቅረዙና ለመብራቱ የሚሆን ብር መዝኖ ሰጠው።

16 ለተቀደሰው ኅብስት ማስቀመጫ ለሚሆን ወርቁን፥ ለሌሎች ጠረጴዛዎች ማሠሪያ ብሩን መዝኖ ሰጠው።

17 እንዲሁም ሹካዎችን፥ ድስቶችንና ማንቆርቆሪያዎችን ለመሥራት ምን ያኽል ንጹሕ ወርቅና ሳሕኖቹንም ለመሥራት የሚያስፈልገውን ብርና ወርቅ መዝኖ ሰጠ፤

18 እንዲሁም ዕጣን የሚታጠንበትን መሠዊያና ክንፎቻቸውን ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት በላይ የዘረጉት ኪሩቤል የሚቀመጡበት ሠረገላ የሚሠሩበት ምን ያኽል ንጹሕ ወርቅ እንደሚያስፈልግ መመሪያ ሰጠ፤

19 ቀጥሎም ንጉሥ ዳዊት “ይህ ሁሉ እግዚአብሔር ራሱ በሥራ ላይ እንዳውለው በሰጠኝ መመሪያ መሠረት በጽሑፍ የሰጠኝ ዕቅድ ነው” አለ።

20 ንጉሥ ዳዊት ለልጁ ለሰሎሞንም እንዲህ አለ፤ “አይዞህ በርታ ሥራውንም በቶሎ ጀምር፤ ምንም ነገር አይግታህ፤ እኔ የማገለግለው እግዚአብሔር አምላክ ከአንተ ጋር ነው፤ ለቤተ መቅደሱ ሥራ ያለህን አገልግሎት እስክትፈጽም ድረስ ከአንተ አይለይም፤ አይተውህም፤ ከቶም አይጥልህም፤

21 በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያለውን አገልግሎት እንዲፈጽሙ ካህናትና ሌዋውያን ተመድበዋል፤ ልዩ ልዩ ችሎታ ያላቸው ሠራተኞች ይረዱሃል፤ ሕዝቡና መሪዎቻቸው ሁሉ ለአንተ ይታዘዛሉ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告