1 ዜና መዋዕል 26 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየቤተ መቅደሱ ዘብ ጠባቂዎች 1 የቤተ መቅደሱ ዘብ ጠባቂዎች የሆኑ ሌዋውያን የሥራ ምድብ እንደሚከተለው ነው፦ ከቆሬ ጐሣ ከአሳፍ ቤተሰብ የቆሬ ልጅ መሼሌምያ ነበር። 2 እርሱም ሰባት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም በዕድሜአቸው ተራ ዘካርያስ፥ ይዲዕኤል፥ ዘባድያ፥ ያትኒኤል፥ 3 ዔላም፥ የሆሐናንና ኤልየሆዔናይ ተብለው የሚጠሩት ናቸው። 4 ስምንት ወንዶች ልጆችን በመስጠት እግዚአብሔር የባረከው ዖቤድኤዶም የተባለም ሌላ ሰው ነበር፤ ልጆቹም በዕድሜአቸው ተራ ሸማዕያ፥ ይሆዛባድ፥ ዮአሕ፥ ሳካር፥ ናትናኤል፥ 5 ዓሚኤል፥ ይሳኮርና ፐዑልታይ ተብለው የሚጠሩት ናቸው። 6-7 የዖቤድኤዶም የበኲር ልጅ ሸማዕያ ስድስት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ዖትኒ፥ ረፋኤል፥ ዖቤድ፥ ኤልዛባድ ኤሊሁና ሰማክያ ተብለው የሚጠሩት ናቸው፤ እነርሱም ስለ ነበራቸው ታላቅ ችሎታ በጐሣቸው መሪዎች ነበሩ፤ በተለይ የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ከፍ ያለ ችሎታ ነበራቸው። 8 እነዚህ ሁሉ የዖቤድኤዶም ልጆች ነበሩ፦ እነርሱና ልጆቻቸው እንዲሁም ዘመዶቻቸው የሥራ ችሎታና ሥራውን የመሥራት ጥንካሬ ነበራቸው፤ የዖቤድኤዶም ልጆችና የልጅ ልጆች በጠቅላላው ሥልሳ ሁለት ነበሩ። 9 መሼሌምያም ችሎታ ያላቸው ዐሥራ ስምንት ልጆችና ቤተሰቦች ነበሩት። 10 ከመራሪ ጐሣ አራት ወንዶች ልጆች የነበሩት ሖሳ ተብሎ የሚጠራ ሰው ነበር፤ ልጆቹም፥ ምንም እንኳ የበኲር ልጅ ባይሆንም አባቱ መሪ ያደረገው ሺምሪ፥ 11 ሒልቂያ፥ ጠባልያና ዘካርያስ ተብለው የሚጠሩት ናቸው፤ ከሖሳ ቤተሰብ የቤተ መቅደስ ዘብ ጠባቂዎች የሆኑ በድምሩ ዐሥራ ሦስት አባላት ነበሩ። 12 የቤተ መቅደስ ዘብ ጠባቂዎች በየቤተሰቡ በቡድን ተከፍለው ነበር፤ እነርሱም ልክ እንደ ሌሎቹ ሌዋውያን በቤተ መቅደሱ ውስጥ አገልግሎት ነበራቸው፤ 13 ሽማግሌ ወይም ወጣት ሳይባል በእኩልነት እንደየቤተሰባቸው ለያንዳንዱ በር ጥበቃ ዕጣ ይጣል ነበር። 14 ሼሌምያ በምሥራቅ በኩል የሚገኘውን ቅጽር በር ለመጠበቅ ዕጣ ወጣለት፤ ዘወትር መልካም ምክር ይሰጥ የነበረው ልጁ ዘካርያስ ደግሞ በሰሜን በኩል የሚገኘውን ቅጽር በር ለመጠበቅ ዕጣ ወጣለት፤ 15 ለዖቤድኤዶም በደቡብ በኩል የሚገኘው ቅጽር በር ደረሰው፤ ልጆቹም የዕቃ ግምጃ ቤቶችን ለመጠበቅ ተመደቡ፤ 16 ለሹፒምና ለሖሳ በምዕራብ በኩል የሚገኘው ቅጽር በርና በላይኛው መንገድ በኩል የሚገኘው ሻሌኬት ተብሎ የሚጠራው ቅጽር በር ደረሳቸው፤ የዘብ ጥበቃው አገልግሎት በክፍለ ጊዜ የተመደበ ሆኖ ቅደም ተከተል ተራ የያዘ ነበር፤ 17 በየቀኑ በምሥራቅ በኩል ስድስት፥ በሰሜን አራት፥ በደቡብ አራት ዘብ ጠባቂዎች ይመደባሉ፤ እንዲሁም በየቀኑ አራት ዘብ ጠባቂዎች የዕቃ ግምጃ ቤቶቹን ለመጠበቅ ሲመደቡ፥ ከእነርሱ ሁለቱ አንዱን የዕቃ ግምጃ ቤት፥ ሁለቱ ደግሞ ሌላውን ይጠብቁ ነበር። 18 በምዕራብ በኩል መንገዱን ተጠግቶ በተሠራው አደባባይ አጠገብ አራት ዘብ ጠባቂዎች ሲመደቡ፥ ራሱን አደባባዩን የሚጠብቁ ሁለት ዘብ ጠባቂዎች ተመድበው ነበር። 19 እንግዲህ ለቆሬና ለመራሪ ጐሣዎች የተመደበላቸው የዘብ ጥበቃ አገልግሎት ይህ ነበር። ቀሪው የቤተ መቅደስ አገልግሎት 20 ከሌዋውያን መካከል አኪያ የቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤትና ለእግዚአብሔር መባ ሆነው የሚቀርቡት ዕቃዎች ለሚከማቹባቸው ቤቶች ኀላፊ ነበር፤ 21 ላደን ከጌርሾን ጐሣ የነበረ ሲሆን እርሱም የይሒኤል አባት ነበር፤ ከእርሱ ተወላጆች ብዙዎቹ በየወገናቸው የቤተሰብ አለቆች ነበሩ። 22 ዜታምና ኢዮኤል የተባሉት የይሒኤል ሌሎች ሁለት ልጆች የቤተ መቅደሱ ቤተ መዛግብትና የዕቃ ግምጃ ቤቶች ኀላፊዎች ነበሩ። 23 ለዓምራም፥ ለይጽሃር፥ ለኬብሮንና ለዑዚኤል ዘሮች የሥራ ድርሻ ተሰጥቶአቸው ነበር። 24 የሙሴ ልጅ የጌርሾም ጐሣ የሆነው ሸቡኤል ለቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት ኀላፊዎች ለሆኑት የበላይ ባለሥልጣን ነበር፤ 25 እርሱም በጌርሾም ወንድም በኤሊዔዘር በኩል ለሸሎሚት የሥጋ ዝምድና ነበረው፤ ኤሊዔዘር ረሐብያን ወለደ፤ ረሐብያም ይሻዕያን ወለደ፤ ይሻዕያ ዮራምን ወለደ፤ ዮራምም ዚክሪን ወለደ፤ ዚክሪም ሼሎሚትን ወለደ፤ 26 ሸሎሚትና ዘመዶቹ ንጉሥ ዳዊት የቤተሰብ አለቆች፥ የጐሣ ቡድን መሪዎችና የጦር መኰንኖች ለእግዚአብሔር የተለዩ አድርገው ላቀረቡአቸው ስጦታዎች ኀላፊዎች ነበሩ፤ 27 እነዚህ ኀላፊዎችም በጦርነት ጊዜ ከተገኘው ምርኮ ጥቂቱን ወስደው ለቤተ መቅደሱ ሥራ የተለየ እንዲሆን ያደርጉ ነበር። 28 ሸሎሚትና ዘመዶቹ ለቤተ መቅደስ ሥራ ለተለዩ ነገሮች ሁሉ፥ በነቢዩ ሳሙኤል፥ በንጉሥ ሳኦል፥ በኔር ልጅ አበኔርና በጸሩያ ልጅ ኢዮአብ ላቀረቡአቸው ስጦታዎች ጭምር ኀላፊዎች ነበሩ። የሌሎች ሌዋውያን የሥራ ድርሻ 29 ከይጽሃር ልጆች መካከል፥ ከናንያና ልጆቹ ከቤተ መቅደሱ ውጪ በመንግሥት ሥራ ሹማምንትና ዳኞች ሆነው ተሹመው ነበር። 30 ከኬብሮናውያን ወገን ሐሻብያና ወንድሞቹ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ከዮርዳኖስ በስተምዕራብ ባለው በእስራኤል አገር ለመንፈሳዊ ሥራና ለመንግሥት አገልግሎት ኀላፊዎች ሆነው ተመደቡ። 31 ከኬብሮናውያንም በቤተሰብ የትውልድ ምዝገባ መሠረት ይሪያ አለቃቸው ነበር፤ ዳዊት በነገሠ በአርባኛው ዓመት በመዝገቡ ውስጥ ፍለጋ ተደርጎ በገለዓድ ያዕዜር ችሎታ ያላቸው ኬብሮናውያን ተገኙ፤ 32 ንጉሥ ዳዊት ከእነዚያ ዘመዶች መካከል ምርጥ የሆኑ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ የቤተሰብ አለቆችን መረጠ፤ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ ማለትም በሮቤል፥ በጋድና በምናሴ ነገድ እኩሌታ ግዛቶች መንፈሳዊውንና ዓለማዊውን ጉዳይ ሁሉ የማስተዳደር ኀላፊነት ሰጣቸው። |